Back to Front Page

የኮ/ል ዓብይ አስገራሚው የሹመት አሰጣጥክፍል ሁለት

የኮ/ል ዓብይ አስገራሚው የሹመት አሰጣጥ

አጀንዳ ማስቀየር ወይስ የትልቁ እቅድ አካል ነው?

ክፍል ሁለት

 

ዑስማን ሙሉዓለም  7-11-19

በክፍል አንድ ኮ/ል አብይ በመከላከያና በድህንነት መስሪያቤቶች በሰጡት ሹመት ተንተርሼ በተሻሚዎቹ ማንነት ላይ የተለያዩ የመረጃ ምንጮችን መሰረት በመዳረግ ወቅታዊ መረጃ አቅርቤ ነበር። ዛሬ ደግሞ ኮ/ል  አብይ ስልጣን ከያዙ ጀምሮ የሹመት አሰጣጣቸውን በተመለከተ ያለኝ መረጃና አስተያየት እንዲሚከተለው በዝርዝር ቀርባል፡፡ መልካም ንባብ!

 

ኮ/ል አብይ በዚህ ያለፈው አንድ አመት ውስጥ (የ13 የወሬ ወራት አለ ያ ሰው)  ለውጥና ሪፎርም ይላሉ፡፡ ይጋልባሉ እንጂ ፈረሱ የት እንደሚያደርሳቸው አይታወቅም፡፡  በጤናና በሰላም ወደ ማይታወቀው መዳረሻ ይደርሳሉ/አይደርሱም? እሳቸውም የሚያውቅት ነገር የለም። ሌላ ማንምም አያውቅም!

Videos From Around The World

እስካ አሁን ሁሉም የወሰድዋቸው እርምጃዎችና የወሰንዋቸው ውሳኔዎች ያልተጠኑ፣  ያልበሰሉና የሚመለከታቸው አካላት ያልተሳተፉባቸው ናቸው። በግላቸው ለብቻቸው ለወቅቱ ቀልብ ይስባል ወይም እንትናና እንትናን ያስደስታል ብለው ትልቅ ውሳኔ በድፍረት ይወስናሉ። የዛሬ ውሳኔዎች ነገ ላይ ምን ይፈጥራሉ?  ብለው ከመወሰናቸው በፊት ደጋግመው ሳያስቡበትና ሳያብሰላሰሉት በግልፍተኝነት በድንገት ይወስናሉ። እርምጃ ይወስዳሉ። አንዴ ከሆነም በኃላ መመለሱና ማረሙ ክብራቸውን የሚነካ ይመስላቸውና ስህተትን ከመቀበልና ከማስተካከል ይልቅ ትክክለኛነታቸውን ለማሳየት ሲዳክሩ ተጨማሪ ብዙ ስህተቶችና ጥፋቶች ይፈፅማሉ። ጥፋታቸውን ለመሸፈን ደግሞ ይዋሻሉ። መሪ ከዋሸ ደግሞ ተከታይ ነኝ የሚል ብዙ አሽቃባጭ ሰውም የእሳቸውን ገበና ለመሸፈን ይዋሻልም ያስዋሻልም። ሚድያውም በዛው ልክ ይከተላል። ለዚህ ማሳያ የሚከተሉት አብነቶች እንያቸው፡፡

በሰኔ 16ቱ የቦንብ ፍንዳታ ወቅት ሳያጣሩ ወሬ ሳይገድሉ ጎፈሬ የሆነ ነገር ተከሰተ፡፡ መቶ ሜትር በማያክል ርቀት ላይ ቦምብ ተወርውሮ ፈንድቶ ምን አደጋ ማድረሱ ሳይረጋገጥ፣ ፈፃሚው ማን? ለምን ዓላማ? እንደፈፀመው በፖሊስ ሳይጣራ ኮኔረሉ ዘለው 30 ደቂቃ በማይሞላ ግዜ ከነከኔቲራቸው ኢቲቪ ላይ ከች አሉ። ብዙ ሰው ሞተና ቆሰለ አሉም። ፈፃሚዎቹ እኔን ሊገድሉኝ በመቶ ሜትር ርቀት ላይ ሆነው ቦምብ ወርውረው ሳቱኝ፣ የመግደል ሙከራቸውም ከሸፈ አሉን። ደንግጠው የቀባጠሩት ነው እንዳንል ሰሙኑን ፓርላማ ቀርበው ስለ በእሳቸው ላይ የተሞከሩ ኩዴታዎች ሲዘረዝሩ ያሉትን ማጤን ይገባል። ከሰኔው አስራስድስቱ ጀምረው የኮማንዶ ወታደሮች ተሰብስበው ቤተመንግስት የመጡትን፣ የጤና ባለሙያዎች ማሕበር ጥያቄ፣ የመምህራን ጥያቄ፣ የሚድያ ዘመቻ፣ የወለጋ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ዘርዝረዋል፡፡  በቅርቡ ደግሞ አሳምነው ፅጌ በባህርዳርና በአዲስ አበባ ያደረሰው ጥቃት ሁሉም በኔ ላይ የተቃጣ ጥቃትና ስያሜውም ኩዴታ/መፈንቅለ መንግስት ነው አሉን። እሳቸው አንዴ ምክንያቱ ባልታወቀ ምክንያት መፈንቅለ መንግስት ስላሉ ብቻ የፌደራል ፖሊስ ሓላፊውም ምንም ሳይጣሩ፣ የሞተና ያልሞተ በአግባቡ ሳያውቁ፣ ሳይረዱ፣ ስሞች እያምታቱ በነበሩበት ወቅት፣ ገና ምርመራ ሳይጀምሩ፣ መረጃም ማስረጃም ሳይዙ ሚድያ ላይ ወጥተው መፈንቅለ መንግስት ሙከራ መካሄዱን ለማሳመን ዳከሩ። አለቃህን ተከተል መሆኑ ነው።

ኮ/ል አብይ የሹመት አሰጣጣቸውም ግብታዊነት፣ ችኩልነትና ጥናት ላይ ያልተመሰረተ ነው። ጊዜያዊ ስሜታዊነት የተጫጫነበትና አንዳንዴም ውለታ ውሎልኛል ብለውም አንዳንዴም ሳርፕራይዝ ላድርገው ወይም ላድርጋት ብለውም የሚወስኑት ነው። በጨረፍታ የሚያውቁትና አንዴ ሲተዋወቁት በእሳቸው አቀራረብና ሁኔታ ተደንቆ፣ ተመስጦ ያሞገሳቸውና እንዳንተ ፈጣን ሰው አይቼ አላውቅም ያላቸውን ሰው መቼም አይረሱትም። ይሾሙታል። ካልቻሉም በአደባባይ በሆነ ምክንያት አድርገው ይኩቡታል። በስማረጃ አስደግፌ ላብራራ።

ቴዲ አፍሮን የባህልና ቅርሶች ሚኒስትር ማድረግ ባይችሉም ብዙ ጊዜ መድረክ ላይ ወዳጃቸው መሆኑን ገልፀዋል። ቴዲዬ ብዙም ፊት ባይሰጣቸውም። ብዙ ሰው የሚወደውን ሰው እወደዋሎህ ለማለት አያፈሩም።  እሱን የምትወዱ እኔንም ውደዱኝ ነው መልእክቱ። ሌላም መልእክት አለው። በዘመነ ወያኔ ተበድለሃል፡፡ ታስረሃል፡፡ መጣሁልህ። ወያኔ እርር ድብን በሉ። ቴዲ ወዳጄ ነው ምን ትፈጥራላቹ? ነገር ነው፡፡ የልጆች ብሽሽቅ የሚመስል ካለ መብሰል የሚመነጭ እርምጃ ነው።

በተመሳሳይ ፀረ ሕገ-መንግስት ወንጀል ፈፅማ፣ ተከሳ፣ ማስረጃ ቀርቦ፣ ተከራክራ፣ በፍርድቤት ተረጋግጦ ብይን ተወስኖባት፣ ማረሚያ ቤት ቆይታና በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ይቅርታ አግኝታ የተለቀቀችውን ብርቱካን ሜደቅሳ ምርጫ ቦርድ ሓላፊ ማድረግ ምን ይባላል?  እውነት ብርቱካን ገለልተኛ ናት? ሕገ-መንግስቱ ላይ እምነት አላት? በፊት በፈፀመችው ወንጀልስ ተፀፅታ ታርማለች? ሹመቱ ሲታሰብ የተነሱት ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት ተካሂዶባቸዋል?  በተጨማሪ ሌሎች ሰዎች ታጥተው ነው?  ወይስ ብርቱካን ብልጫ አግኝታ ከሌሎች ልቃ መስፈርቱን አሟልታ ነው? የሚሉ ጥያቄዎች መመለስ ይገባቸው ነበር፡፡ ነገር ግን እውነቱን እንንጋገር ከተባለ ኮ/ል አብይ ብርቱካን ሜደቅሳን የምርጫ ቦርዱ ሓላፊ ሲያደርጉ ሁለት ግቦች ለማሳካት ነው። አንድ በፈረንጆች ይሞገሳሉ። ተሞግሰዋልም። ሁለት ወያኔ የከሰሳትን በመሾም ወያኔን ያሳጡ ይመስላቸዋል።

ሌላው ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሹመት ነው፡፡  ወርቅነህ ገበዮህን አንስተው በለውጥ/ነውጥ መሃል በሳቸው ፈንታ ውጭ ጉዳይን ያህል መስርያቤት አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን መሾም በትክክል የሚያስብ ጭንቅላት የወሰነው ውሳኔ ነው?  ገዱ አንዳርጋቸው ሳይበላሹ ቀደም ባሉ ዓመታት በተግባር በአማራ ክልል ጥሩ ስራ ሰርተዋል። ከወርቅነህ ገበየሁም ማወዳደሩ አይገባም፡፡ ወርቅነህ መስርያቤት ከመቀያየር የትም ሄደው የሰሩ ስለ መሆናቸው አሻራቸው አይገኝም። ከማውደልደል በስተቀር። ይሁን እንጂ በውጭ ጉዳይ ሰው ታጣ ቢባል እንኳን በቆማጣ ቤት አንድ ጣት ብር ቅናት ብዬ ወርቅነህን አንስቼ ገዱን አልሾምም። ታድያ ኮ/ል አብይ ገዱን የሾሙት በምን መስፈርት ነው? ከነማን አወዳድረው ነው ገዱ ብልጫ አግኝተው ለሹመቱ ያጭዋቸው? ኢትዮጵያ መካን ናት?  ገዱ ለውጭ ጉዳይ እንካንስ ሊሾሙ በእሳቸው ክልል አስተዳዳሪነት ዘመን ነው እኮ በቅማንት ላይ ዘር የማጥፋት ወንጀል ተፈፅሟል የሚል በሰብአዊ መብት ጠባቂ ምርመራ ተደርጎ፣ ሪፖርት ቀርቦ፣ ውሳኔ ሳይሰጥበት እንዲያውም ጭፍጨፋው ተጠናክሮ የቀጠለበት ሁኔታ የተፈጠረው። በተጨማሪም በመቶ ሺዎች በአማራ ክልል ነዋሪ የነበሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ ግድያ፣ እስራትና መፈናቀል በመፈፀሙ ገዱ መጠየቅ ሲገባቸው በምን መስፈርት ነው ለሹመት የሚታጩት? መስፈርቱ የኦሮ-ማራ የስራ ባልደረባዬ ሳልሾም ማንን እሾማለሁ! አይደለም ለማለት ይቻላል?

 

ሌሎች የቅርብ ሹመቶችም ስናይ ተመሳሳይ ነው፡፡ ተከሶ የነበረው ዳንኤል በቀለን የስብአዊ መብት ኮሚሽን ማድረግ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ ህይወታቸውን ያሳለፉት መዓዛ አሸናፊ የፍርድ ቤቶች አለቃ ማድረግ (ለወይዘሮዋ በግሌ ልዩ ክብር አለኝ ሹመታቸውን ብቻ ነው የምቃወመው) መስፈርቱ ምንድ ነው? ኮ/ል አብይ ከማን አወዳድረውና ከማን ጋር እየተወያዩ ነው ለሹመት የሚያቀርቧቸው? ምን ዓይነት ስርዓት ተከትሎ ነው ለሃላፊነት ሰውን የምታጨው?  የሚሉ ጥያቄዎች ሳይመለሱ ከፍተኛና ወሳኝ ያገሪቱ ቁልፍ የሓላፊነት ቦታዎች በአንድ ሰው ለዛውም ምንም ልምድ በሌላቸውና ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆናቸው ብቻ ይሾማሉ፡፡ ይሽራሉ። እንደ ህፃን ሁሉንም ያለ እውቀት ይነካካሉ። በነካኩ ቁጥር ግን ያልተገመተ ቀውስ ይፈጠራል።

በአጠቃላይ ኮ/ል  አብይ እያደረጉት ያሉትን ሁኔታ በመብረር ላይ ያለ አውሮፕላን ኮክፒት ውስጥ የገባ ህፃን የአውሮፕላኑን ቆልፎች በመነካካት ሊያስከትለው የሚችል አደጋ ብንገምት እውነትነቱን ያሳየናል።

በክፍል ሦስት ደግሞ በዚህ ፅሁፌ ተንተርሼ የሰሙንን የመከላከያና የድህንነት መስርያ ቤቱን የሚመሩ ሰዎችን ሹመት በተመለከተ ያለኝ ትንተና አቀርባለሁ። ቸር እንሰንብት።

 

ለተጨማሪ መረጃና አስተያየት osman.mulualem@yahoo.com ይጠቀሙ፡፡

ዑስማን ሙሉዓለም

ከሓራ ገበያ


Back to Front Page