Back to Front Page

የኮ/ል ዓብይ አስገራሚው የሹመት አሰጣጥአጀንዳ ማስቀየር ወይስ የትልቁ እቅድ አካል ነው? ክፍል ሦስት

 

 

የኮ/ል ዓብይ አስገራሚው የሹመት አሰጣጥ

አጀንዳ ማስቀየር ወይስ የትልቁ እቅድ አካል ነው?

 

ክፍል ሦስት

 

ዑስማን ሙሉዓለም 7-15-19

ከሓራ ገበያ

 

በክፍል ሁለት ኮ/ል ዓብይ አህመድ ስልጣን ከያዙ ጀምሮ ውሳኔ አሰጣጣቸው በተለይም የሹመት ውሳኔያቸው ባህርይ ምን እንደሆነ ለማብራራት ሞክርያለሁ። በዚህ የመጨረሻ ፅሁፌ ኮ/ል ዓብይ በመከላከያና ድህንነት የሚመሩ ባለስልጣን ሲሾሙ አሁንም ተመሳሳይና የተለመደውን ስህተት ፈፅመዋል።

 

አሁንም ጠቅለል አድርጎ ሲታይ የሹመት አሰጣጥ ውሳኔያቸው ጥናት ላይ ያልተመሰረተ፣ ችኩልነትና ጥድፍያ የተሞላበት፣ ብጥልቀት ታስቦበት ያልተፈፀመ፣ የተለመደውን የኢህአዴግ ኮሚታዊ አሰራር ያልተከተለ፣ የሌሎች ተሳትፎ ገለል ያደረገ፣ የአንድ ሰው ውሳኔ ብቻ መሆኑ፣ ተራ መስፈርትም ያላሟላና ሰዎችን በብቃት አወዳድሮ የተፈፀመ ሹመት እንዳልሆነ በመግለፅ መደምደም ይቻላል። ዘርዘር ባለመልኩ ደሞ እንደሚከተለው እንየው፡፡

 

የክልል አመራሮች በመሀል ከተማ በሚሰሩበት መስርያ ቤት ሆን ተብሎ በጥይት ተገደሉ። ይህን ሁኔታ ለማጣራትና ለመቆጣጠር ጥረት እያደረጉ የነበሩት የኢትዮጵያ መከላከያ ኤታማዦር ሹም በመኖርያ ቤታቸው እያሉ ምሽት ላይ በተመሳሳይ ቀን በወቅቱ አብራቸው የነበሩ ጡረተኛ ወዳጃቸው ጭምር በጥይት ተገደሉ። ትልቅ ቀውስ ተፈጠረ።

Videos From Around The World

 

የፌደራል መንግስት ይሁን የክልሉ መንግስት ሁኔታው በጣም አሳሳቢ ነው ብለው ያዩት አልነበረም። ያደረጉት ነገር ቢኖር ተጣድፈው ሚድያ ላይ ቀርበው ያልተጣሩ መረጃዎች፣ ትንታኔዎችና ፍረጃዎች አሰሙ። መፈንቅለ መንግስት ነው አሉ። መፈንቅለ መንግስቱም ወዲያውኑ ከሽፏል አሉ። የቀብር ስነስርዓት፣ የሐዘን ቀንና ባንዴራ ዝቅ እንዲል አደረጉ። የሩጫው አላማ ነገሮችንና ሀቅን ማዳፈን፣ መሸፋፈንና እንደ አንድ የተነጠለ ክስተትና አጋጣሚ ተደርጎ እንዲታይ ማድረግ ነበር። ገፅታቸው እንዳይበላሽ ተጨንቀው ተንቀሳቀሱ። ሁኔታው በቁጥጥር ውስጥ ውሏል። አገር ተረጋግቷል። የተፈፀመው ወንጀል እየተጣራ ነው። ፌደራል ፖሊስ መርማሪ ቡዱን አደራጅቶ ማጣራት ጀምሯል። ነገሮች በተለመደው መንገድ እየሄዱ ነው። አዲስ ነገር የለም። አታጋግሉ፡፡ የሚል መልእክት በተዘዋዋሪ ተላለፈ። ኢንቴርኔትና ቴክስት አገልግሎቶች ጥርቅም አድርገው ዘግተው መንግስት ብቸኛ ዜና አቅራቢ አደረጉት። ጥያቄም አያስተናግድም። መግለጫ ከላይ ወደ ታች ብቻ ይንቆረቆራል። ቅጠረኞች እየቀረቡ ትንታኔ አስመስለው ያንኑን ደጋገሙት። ቀጥሎ ደግሞ ኮነሬሉ ተቻኩለው ሹመት ሰጡ።

 

ያጋጠመው ክስተት ብቻውም ቢሆን ትልቅ ቀውስ ነው። ሆኖም ግን አሁን የተከሰተው ቀውስ ከአንድ ዓመት በላይ ሲገጥመን ከቆየው ቀውሶች ጋር ተነጥሎ የሚታይ አይደለም። ቀውስ ደግሞ ማስተዳደር ይፈልጋል። ሽፋፍነህ ማለፍ አይቻልም። ቀውስን ከሸፋፈንከው ሌላ ቀውስ ይፈጥራል። ብሎም አገር ያፈርሳል።

 

በቀውስ ወቅት መደረግ ያለበት አስቸካይ የከፍተኛው አመራር ስብሰባ ተጠርቶ ሁኔታውን መመርመር፣ መገምገም፣ የችግሩን መንስኤ በግልፅ ማስቀመጥ፣ ጊዚያዊና ዘላቂ መፍትሔ ማስቀመጥ፣ ለህዝቡ ትክክለኛ መረጃ በየጊዜው መስጠት፣ ቀውሱ እስኪፈታ በጋራ በቅርበት እየተመካከሩ መምራትን ይጠይቅ ነበር። ይህ አልተደረገም። የኮ/ል ዓብይ መንግስት ባህርይ ይህ የማድረግ አቅም ይሁን ብቃት የለውምና። ቀውሱን ለመሸፈን ጥረት ከማድረግ ውጭ ቀውሱን ለመፈታት ምንም ለማድረግ አልቻሉም። ቀውስን ከማሰተዳዳር ወደ ጥድፍያ ሹመት ነበር የሄዱት፡፡ ይህን ተጣድፎ የተፈፀመው አስገራሚው ሹመት ለምንና እንዴት እንደተፈፀመ እንደሚከተለው ተትንትናል፡፡

 

1ኛ) ጄነራል አደም በዘመነ ኢህአዴግ ደካማው ኤታማዦር ሹም ናቸው። ለምን?

ጄነራል አደም ተወዳድረው አይደለም ይህን ሹመት ያገኙት። ጄነራሉ በብዙ መስፈርት ከነበሩት ጄነራሎች ይቅርና አሁን በመከላከያ በስራ ካሉት ቢወዳደሩ ዝቅ ያለ ነጥብ ያገኛሉ። በዚህ ስልጣን እርከን ሹመት የሚሰጠው ሰው ውግያ መምራት ብቻ አይጠበቅበትም። ጦርነትን መርቶ ማሸነፍና ማስቀረትን ይጠበቅበታል። ይህን ለማድረግ ደግሞ ሠራዊትን የማደራጀትና የማዘጋጀት ሓላፊነት አለበት፡፡ ስለሆነም የጠላት ዝርዝር ዕውቀትና የወደፊት የይሆናል ጦርነት በመተንበይ የጦር አዛዦችንና ሠራዊትን ማዘጋጀትና ማብቃትን ይጠይቃል። ጄነራል ፃድቃን፣ ጄነራል ሳሞራ፣ ጄነራል ሰዓረ፣ ጡረታ የወጡትም ጄነራል ገዛኢና ጄነራል አበባው ታደሰ ላይ ያነሷሃቸውን መስፈርቶች ከሞላ ጎደል ያሟሉና በተነፃፃሪ የሚጎድላቸውን ማሟላት የሚችሉ ነበሩ።

 

በስራ ካሉት ጄነራል መኮነኖች ውስጥ ይህን ነባር አመራሮቹ ያሟሉትን መስፈርት የሚያሟሉ አሉ። ከታችም ቀላል ቁጥር የማይባል ዕምቅ አቅም ያላቸው መኮነኖች አሉ። መከላከያችን በአካዳሚም በሙያም ብዙ አዛዦች ሲያፈራ ቆይቷል። ይህ ደግሞ ከሁሉም ብሔሮች ተመጣጣኝ አስተዋፅኦ ባለው መንገድ የተፈፀመ ነው። ይህም ሆኖ የነበረው ጉድለት የመልካም አስተዳደር ዕጦት ነበር። ይህ የመልካም አስተዳደር እጦት ማን? ምን አቅም/ብቃት አለው? ተብሎ እየተመዘነ እየታወቀ አልመጣም። ጄነራል አደም የሙሉ ጄነራልነት መዓርግ ሲስጣቸው ብዙ ሰው አልተቀበለውም። የሌሎችን የመዓርግ ዕድገት ተቀብሎ በሳቸው ላይ ተቃውሞ ነበር። ለምን ቢባል ከሳቸው በላይ መስፈርቱን የሚያሟሉ እያሉ ለእርሳቸው የሙሉ ጄነራልነት መዓርግ መሰጠቱ አግባብ አይደለም የሚል ነበር፡፡ ይህም ፍትሓዊ ያልሆነ የጄነራል ሳሞራና የሃይለማርያም የመልካም አስተጋደር ጉድለት መገለጫ ነው። ጄነራል አደም የአየር ሓይሉን ያዳከሙ ሰው እንዴት መዓርግ ያገኛሉ? ድሮ የነበራቸውን ስብእና ያጡና የመከላከያ ሠራዊት አባል ሆነው ደመቀ መኮንን ምረጡ እያሉ ያለስራቸው የሚፈተፍቱ ሰው በምን መለከያ መዓርጉ ይመለከታቸዋል? ከአየር ሓይል መምራት ውጭ የክ/ጦር እዝ መርተው የማያውቁት መኮነን በምን ብቃትና ልምድ ነው አሁን ደግሞ የአገራችን ኤታማዦር ሹም ሹመት የሚሰጣቸው? ጄነራል ብርሃኑ ጁላና ጄነራል ሞላ እያሉ ሌሎች የሉም ብዬ አይደለም ነገር ግን ቢያንስ ከሁለቱ አንዱ ለምን አልሆኑም ነው? ጄነራል ብርሃኑ ጁላ ለረዥም ጊዜ ክፍለጦር አዛዥ ሆነው የተዋጉና ያዋጉ፣ የስልጠና አዛዥ በመሆንም ሠራዊት በማሰልጠንና በማዘጋጀት ልምድ ያካበቱና በእዝ አዛዥነትም በባድመ ግምባር የማዕከላዊ እዝ አዛዥ በኃላም የምዕራባዊ ኢትዮጵያ እዝ አዛዥ ሁነው ያገለገሉና ልምድ ያላቸው በሠራዊቱም ተቀባይነት ያላቸው ናቸው። ሙሉ የጀነራልነት መዓርግ ካገኙ በኃላም ምክትል ኤታማዦር ሹም በመሆን ሲሰሩ ቆይተዋል። ውጊያ ብቻ ሳይሆን ጦርነትን መምራት የሚያስችል ብቃት ለመፍጠር ከጀነራል አደም በላይ በብዙ እጥፍ ዕምቅ አቅም አላቸው። ታድያ በምን ሂሳብ ነው እሳቸው ተዘለው ጄ/ል አደም የተመረጡት?

 

ጄነራል አደም ጠንካራነቱን ያስመሰከረውን የብሄራዊ ድህንነትና መረጃን መስርያቤት ከተረከቡ በኃላ በከፍተኛ ደረጃ በማፈራረሳቸውና ደከማና ሽባ በማድረጋቸው ቢያንስ ሊነሱ ካልሆነ ደግሞ እንደደንቡ ሊጠየቁ ሲገባ ወይም ራሳቸው ከስልጣኔ በገዛ ፍቃዴ ለቅቅያለሁ ይቅርታ ማለት ሲችሉ ሌላ ሹመት ለዛውም ከሳቸው በብዙ ዕጥፍ የሚበልጡ እያሉ እንዴት ይሆናል? ሌላው ሁሉ ይቅርና በቅርቡ በአማራ ክልል በከፍተኛ አመራሮች የተፈፀመው ግድያ በአዲስ አበባ በሁለት ጄነራሎች የተፈፀመው ግድያ ቀድመው ባለማወቃቸው መጠየቅ ሲገባቸው ጭራሽ ሹመት? እንዴት ነው ነገሩ? ወይስ በግድያው ሴራ ተሰማርተው ውጤት ስላስገኙ ሽልማትና ነገሩን ለመሸፋፈን የተደረገ ሹመትና ዕድገት ነው? ጄነራል አደም አስመራ የተመላለሱትና አዲስ አበባም ከኢሳያስ ድህንነቶች ከነ ከኮ/ል ፍፁም ጋር በህብረት በመስራታቸው ያገኙት ሹመት ነውን? ግልፅነት የጎደለው ሹመት ነው። የኮ/ል አብይ ሁሉም ውሳኔዎች ግልፅነት የጎደላቸው ናቸው። ይህኛው ግን ለየት ያለና ብዙ ጉድ የሚሸት ያለው ነው።

2ኛ) አቶ ደምመላሽ፣ ተጠርጣሪ ወንጀለኛን የድህንነትና መረጃ ሃላፊ ብሎ መሾም የሿሚውን ምንነት ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ኮ/ል አብይ በስልጣን ጥም አንጎላቸው የሳቱ መሪ ትክክለኛ ሹመት ሊሰጡ አይችሉም ብሎ ነገሩን ማሳጠር ይቻላል። በክፍል ሁለት ፅሁፌ ለማሳየት እንደሞከርኩት ኮ/ል አብይ ውሳኔ የሚወስኑትና ሹመት የሚስጡት ከህዝብና ከአገር ጥቅም አንፃር ሳይሆን ከግላቸው ጥቅምና ለስልጣናቸው ድህንነት ብቻ ነው። ከመጀመርያውኑ አቶ ደምመላሽን የድህንነት መስራያቤት ምክትል ሓላፊ አድርገው የሾምዋቸው እሳቸውና ለማ ቲም በአጠቃላይ ምን ወንጀል ፈፅመው ወደ ስልጣን እንደመጡ ጠንቅቆ የሚያቀውን መስራያቤት ገብተው የተጠናቀረባቸው መረጃዎችና ማስረጃዎችን እንዲያጠፋ፣ ቀንና ሌሊት ለህዝብና ለሀገር ድህንነት ሲለፉ የነበሩትን ቁልፍ ሰዎችን በሃሰት ወንጀል የመክሰስ፣ የማሳደድና ስም የማጥፋት ዘመቻ ማካሄድ ስራውን እንዲሰራሏቸው ነው። ይህን ሲሰሩ ደግሞ ህዝባችንና አገራችን እየታመሰች እንድትቆይ ዋጋ ተከፍሎበታል። በቅርቡም በስትራተጂክ አመራር የግድያ ጥቃት ሲፈፀም አቶ ደምመላሽ የት ነበሩ? የመረጃና ደህንነቱ ኦፕረሽናል ስራ በበላይነት እንዲሰሩ የስራ ድርሻ የተሰጣቸው አቶ ደምመላሽ ግድያውን ቀድመው ባለማወቃቸውና ባለማክሸፋቸው መጠየቅ ሲገባቸው ሹመት እንዴት ይሰጣቸዋል? ወይስ ሶማሊዎችን በአወድያና በገለምሶ ፖሊስ ጣብያ እንዳስጨፈጨፉት፣ የጌድዮን ህዝብ ከጉጂ በታጠቁ ሚሊሻቸው ገድለውና ቤታቸውን አቃጥለው እንዲፈናቀሉ በማድረጋቸው እንደተሾሙት፣ አሁንም በአመራሩ ግድያ ሴራ ሚና ስለነበራቸው ይሆን የተሾሙት? ወንጀለኛ መሾም በዘበነ አብይ ተለምዷል። ሽብርተኛው ብርሃኑ ነጋ መሾም፣ ማሞገስና የቅርብ አማካሪ ማድረግ፣ የደሴውን ሸክ ኑር መስጊድ በር ላይ የገደለውን ወንጀለኛ አቡበከርን መሾም፣ ከማል ገልቹን ሰራዊት አፍርሶ የከዳ ሰውን በክብር ተቀብሎ የኦሮሚያ የፀጥታ ባለስልጣን ማድረግ፣ አሳምነውን ተመሳሳይ ስልጣን መስጠት ጤነኛ አእምሮ ያለው መሪ እንደሌለን በግልፅ ያሳያል። በተጨባጭ ዶክተር አምባቸውንና የስራ ባለደረቦቻቸውን በጭካኔ የገደለ ሰውን በአደባባይ ጀግና ነው ማለት ምን ማለት ነው? ጤንነትን ያሳያል? አያሳይም። ተጠርጣሪንም ወንጀለኛንም መሾምም በምንም መንገድ ትክክል ሊሆን አይችልም። ሹመቱም የኮ/ል አብይን ጥቅምና ስልጣን ከማስጠበቅ አልፎ የኢትዮጵያ ህዝብና አገር ጥቅም የሚያስጠብቅ አይደለም። አቶ ደምመላሽ የኢትዮጵያውያን ሳይሆኑ የአብይ ደምመላሽ እንጂ የሌላ ሊሆኑ አይቻላቸውም። በሙያ በድህንነቱ መስራየቤት ከእስራት የተረፉ ከደምመላሽ የተሻለ ብቃትና ብልጫ ያላቸው አሉ። በብሄራዊ አስተዋፅኦም ያሟሉ ኦሮሞዎችም የሌሎች ብሄር አበላትም አሉ። ኮ/ል አብይ ምን አስጨነቃቸው፣ ሳያወዳድሩ ባለውለታቸውን መረጡ። አለቀ። አለቃ ሁሌ ትክክል ነው። በሳቸው የአመራር ፍልስፍና።

 

3ኛ) የጄነራል ሞላ ሹመት ለምን አስፈለገ? ማንን ለማስደሰት? ጄነራል ሞላ ራሳቸውን ለማስደሰት ወይስ ህወሓትን? ማስደሰት ወይስ ማጭበርበር? ያልነበረ መዋቅር በድንገት ፈጥረህ፣ ጄነራል ሰዓረ ያስጠናው ነበር። ለማለት? ከመቃብር ተነስቶ ማስተባበል አይችልምና ለመዋሸት ችግር የለውም ብለው ጄነራል ሞላ ምድር ጦር አዛዥ ሆነው ተሽመዋል ተባለ። ጄነራል አደም እንዴት ብሎ ነው በስንት ዕጥፍ የሚበልጡትን እነጄነራል ብርሃኑንና ሞላን የሚመራቸው? ወይስ ጄነራል ሞላ የትግራይ ሰው ስለሆኑ ብቃት እያላቸውም ምንም ማድረግ አልችልም ወይም ሙሉ ጄነራል ስላልሆኑም የሚጠይቀኝ የለም ብለው ነው? ለነገሩ ሞላን ሙሉ ጄኔራል ማዕርግ ሰጥተው ጄነራል ብርሃኑን ኤታማዦር ሹም አድርገው ጄነራል ሞላን ምክትል ኤታማዦር ማድረግ ይቀል ነበር። መከላከያ ሚኒስትር አቶ ለማ ኦሮሞ፣ ኤታማዦር ሹሙ ኦሮሞ ብለው እንደ ግንቦት ሰባት የብርሃኑ ነጋ ዘር ቆጣራ ካልገቡ በስተቀር ምንም ችግር የለበትም ባይ ነኝ። በአንድ ወቅት አቶ ስየ መከላከያ ሚኒስትር ጄኔራል ፃድቃን ኤታምዦር ሹም ሁነው ነበርና። የኦሮሞ የበላይነት እንዳንባል ከሆነ ለምን መከላከያ ሚኒስተር እንደሆኑ ምክንያቱ ያልታወቀውን የአቶ ለማ ሹመት ላይ ለውጥ ማድረግ ቢቀድም ይሻላል ነበር። መከላከያ የአገር ዳር ደንበርና የህዝብ ሉዕላዊነት ጠባቂ፣ የህገመንግስቱ የመጨረሻ ምሽግ ስለሆነ ብቃት ያለው ወታደራዊ አመራር የማግኘት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው። የጀነራል ሞላ ሹመት እሳቸውም ሌላም የሚደስትበት አይደለም። የሌለ መዋቅር አዛዥ መሆን ማንንም አያስደስትም። ተራ ማጭበርበር ነው። የምድር ጦር ቢመሰረትም ለጄነራል ሞላ አቅማቸውን የማይመጥን ሹመት ነው።

 

በአጠቃላይ ኮ/ል ዓብይ ምን አስቸኮላቸው? ያጠዳፋቸው ምክንያት ምንድነው? ፈጥኖ አጀንዳ ማስቀየርም አንድ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ነገሩን ለማስረሳት። ለምን ማስረሳት ፈለጉ? ምን ለመሸፈን ነው የሚጣደፉትና አጀንዳ ማስቀየር የሚፈልጉት? ይህ ብቻ ምክንያት አይመስለኝም። ከአጀንዳዬ እንዳያስወጣኝ እንጂ ኮ/ል አብይ ሌላ ያስፈራቸው ነገር አለ። በክልል አማራው ጥቃት ይሁን በጄነራሎቹ ጥቃት ንፁህ አይደሉም።

አንደኛ፡- ቢያንስ የአገሪቱንና የመሪዎቹን ድህንነት መጠበቅና ማስጠበቅ አልቻሉም። ቅድሚያ የራሳቸውን ድህንነትና ምቾት ማስጠበቅ ላይ ነው የተረባረቡት። በሪፓፕሊካን ጋርድ ታጠሩ፣ የቤተመንግስት ጥበቃቸው በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን አደረጉ፣ ከሳቸው በስተቀር ሁሉም ባለስልጣናት የሚጠረጠሩበትና የሚፈተሹበት አሰራር ፈጥረው ሲያበቁ የሌላውን ደህንነት ግን ጉዳያቸው አልነበረም።

 

ሁለተኛ፡- በሽብርተኝነት በፍርድቤት የተፈረደባቸውን ሰዎችን በፀጥታ መዋቅር የመመደብ አሰራር ፈጥረው መላ የአገሪትዋን ህዝቦችና መሪዎችን በየድህንነት አደጋ ውስጥ በማውደቃቸው ተጠያቂ ያደርጋቸዋል። ከማል ገልቹ፣ አሳምነው ፅጌ፣ ተፈራ ማሞ፣ አለበል፣ አበረ ሌሎችም በወንጀል የሚጠረጠሩ እንደ ደምመላሽና የፌደራል ፖሊስ ምክትል ፖሊስ አዛዥ በምን ሂሳብ ነው የአገር ፀጥታ አስከባሪና የህዝብ ደህንነት ጠባቂ የሚሆኑት? ይህ አሰራር ሁሉንም የለማ ቲም ያስጠይቃል። በተለይ ኮ/ል ዓብይ፣ አቶ ደመቀ መኮንን፣ አቶ ለማ መገርሳ፣ አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ያስጠይቃል።

 

ሦስተኛው፡- በጠቅላይ ሚኒስትሩ ኮ/ል ዓብይና በመከላከያ ከፍተኛ መኮነኖች መካከል በህገ መንግስቱ ጥበቃ ዙርያ ልዩነት እንደነበረ ይታወቃል። ጄነራል ብርሃኑ በቁጭትና በስሜት በሁለቱ የተገደሉት ጀነራል መኮነኖች ሽኝት ወቅት የተናገሩትን ንግግር መስማት በቂ ይመስለኛል። ኮ/ል ዓብይ መከላከያ ከዳር ደምበር ጥበቃ ውጭ ህገ መንግስት የመጠበቅ ሃላፊነት የለውም በሚል በቤተመንግስት ጉብኝት ወቅት ከአጀንዳ ውጭ መኮንኖችን ሰብስበው በንግግራቸው መሃል ጣል አድርገው የሰራዊቱን አመራር አስደንገጠውታል። በዚህ ልዩነት ጄነራል ሰዓረ ሰለባ ሆኖ ይሆን?

አራተኛው፡- ጉዳይ ሌላ ጊዜ ለብቻው ራሱን አስችዬ የምፅፈውና በዝርዝር የምገልፀው እንደሆነ ቃል ገብቼ ለአሁኑ ባጭሩ ልቀጥል። ጁሃር ስለ ኦሮማራ ስትራተጂ ሲገልፅ በግልፅ እንደተናገረው ህወሓትና ትግሬዎችን በማዳከምና ከፌደራል መንግስትና በጠቅላላው በኢትዮጵያ ፖለቲካ የነበራቸውን ሚና ዝቅ እንዲል ልካቸውን እንዲያቁ ካደረግን በኃላ ትላልቆቹ ክልሎች ኦሮሚያና አማራ ብዙ ህዝብ ያላቸው ወሳኙን ሚና ይጫወታሉ ብለን የተሳካ ስራና ውጤት አስመዝግበናል ብሎ ይገልፅና ያጋጠመውን ችግር ደግሞ ሳይደብቅ ያብራራል ከነመፍትሄው። ይህ ካሳካን በኃላ አማራዎቹ ግን ሌላ የብቻቸው ዕቅድ እንዳላቸው ደረስንበት። ህወሓትንና ትግሬዎችን በጋራ አንድ ላይ ሁነን ካዳከምን በኃላ ኦሮሞዎቹን በቀላሉ ከስልጣን አውርደን የቀድሞ ስልጣናችን እናስመልሳለን ብለው እያሰቡ እንደሆነ አወቀናል። መፍትሄም አበጅተናል። ሚዛን መጠበቅ አለብን። ሁለቱ አማራና ትግራይ በቀጣይ እንዲናቆሩ ማድረግ ነው ብሎ ነበር። የባህርዳሩና የአዲስ አበባው ጥቃት እንቆቅልሽ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ መግደል የቻሉ አይመስልም? የክልል አማራን አመራር በማዳከም የትግራይ አመራር ደግሞ እንዳያንሰራራ ሰዓረን በማጥፋት ሚዛን መጠበቅ የተባለው የጁሃር ስትራተጂ የተፈፅመ ይመስላል። እነኮ/ል ዓብይ ይህን ለመሸፈን ቀድሞ መፈንቅለ መንግስት ነበር ተባለ። ሁለቱ የባህርዳርና የአዲስ አበባው ተያያዥ ናቸው ተባለ። እንዴት እንደሆነ ሳያብራሩና ገና ምርመራ ሳይጀመር። ምን አጠደፋቸው? ምን ለመሸፈን? አስገራሚ የሆነ ሹመት ተሯርጥው በመስጠት ሁለቱን መስርያ ቤቶችን ደካማ ሰዎች እንዲመሯቸው አደረጉ። ትልቁ እቅድማ አለ! ሊጣራ የሚችለው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ሲጠየቁ ነው። እንዳይጠየቁ ፓርላማ ቀርበው የፌደራል ወገን ነኝ አሉ፣ ምርጫ ይደረጋል አሉ። ቀባጠሩ። የአምባቸው ደም የሰዓረ ደም እየጠራቸው ይሆን?

 

ቸር እንሰንብት።

 

ለተጨማሪ መረጃና አስተያየት osman.mulualem@yahoo.com ይጠቀሙ፡፡

Back to Front Page