Back to Front Page

አምስተኛው ሹክ በተመለከተ።

አምስተኛው ሹክ በተመለከተ።

ክፍል ሁለት

 

በሰንደቁ ያይላል

1/1/2012

 

በክፍል አንድ ፅሁፌ ፥ አምስተኛው ሹክ ላይ ተንተርሼ ያደርስኩላቹህ አስተያየት ጠቃሚና ኮርኳሪ አተያዮችና ሀሳቦች እንዳገኛቹህበት ተስፋ አደርጋሎህ። እነሆ ክፍል ሁለት ቀጠልኩኝ መልካም ንባብ።

በስብሰባው ላይ ሌሎች ክስተቶችም ታይተዋል። ምርጫን በተመለከተ ፣ ርእዮተ አለምን በተመለከት ፣ ህወሓትን ማድነቅን በተመለከተ ፣ surprise በሚባል መልኩ ተነስተዋል።

ሀ. ብሄራዊ ምርጫን በተመለከተ ፦ ምርጫን በተመለከተ ሲጀመር የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ይህንን አጀንዳ ይዞ የመወያየትና የመወሰን ስልጣን ማን ሰጠው የሚለው ነው?። በበኩሌ የሚመለከተው አጀንዳ አልመሰለኝም። ይሁናን አቶ በፈቃዱ የሰጡት መግለጫ ግን ኢህአዴግና መንግስት ዝግጅት እንዲጀምሩ ወስነናል የሚል ነው። ይህ ማለት ምርጫው ይካሄድም አይካሄድም እንደ ድርጅትና መንግስት መዘጋጀት አለብን ነው። ይህ ምርጫው መካሄድ አለበት ብለው ወጥረው ለያዙት ወገኖች እንደ ማስተዛዘኛ የቀረበ የግዜ መግዣ መከካለኛ አቋም ይመስለኛል። የሚካሄድ ቢሆን በሚመለከተው ተቋም ለሁሉም ተወዳዳሪዎች ዝግጅት እንዲጀምሩና ይህ ለክርክር እንደማይቀርብ መግለፅ ሲገባ በኢህአዴግ በኩል ብቻ ዝግጅት እንዲጀመር ወስነናል ማለቱ ፥ ያው መኩረን ነበር ለማለት ይመስላል።

እዚህ ላይ ከ4ኛው ዙር ብሄራዊ የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ጋር ተያይዞ የነበሩትን ክስተቶች ማየት ሁኔታውን ግልፅ ለማድረግ ይረዳል። ቆጠራው ለሁለት ግዝያቶች ተራዝመዋል። በ2011 እንዲካሄድ መርሀ ግብር ወጥቶለት የነበረው ስራ ዝግጅቱ እንዲቀጥል ትእዛዝ ተሰጥቶ ሁሉም ክልሎች ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዲገቡ ተደርገዋል። ለቆጠራው የምያስፍልግ በጅት ተመድበዋል ፣ አስፈላጊው ግብአቶች ዝግጁ ተደርገዋል ፣ ስልጠና በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ተሰጥተዋል። ይሁንና ሂደቱ እንዳይሳካ የሚፈልጉት ሀይሎች ወስጥ ውስጡን የተለያዩ አሻጥሮች በመስራት ዝግጁቱን አደናቅፈዋል። በስተመጨረሻም በ11ኛው ሰአት ቆጠራው እንዲሰረዝ ሆነዋል። ቆጠራው እንዲካሄድ ይፈልጉ የነበሩ ሀይሎች ፣ መርሀ ግብሩ ቢሰረዝ መውሰድ ያለባቸውን አቋም ማሰብያ ግዝያት እንኳ አላገኙም። ግዝያቸውን በዝግጅት በማሳለፍና ቆጠራው ስኬታማ የሚሆንበትን መንገድ በማሰብ ተጠምደው ቆይተዋል።

Videos From Around The World

ምርጫን በተመለከተ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ የወሰደው አቋም እንደ እኔ እይታ የብሄራዊ የህዝብና የቤቶች ቆጠራን አስመልክቶ ከተከተለውና ከወሰደው አቋም ጋር ተመሳሳይ ነው። ዝግጅቱ ይጀመር ፣ የውሸት እንዳይመስል በጀት ይለቀቅ ፣ ስልጠና ይሰጥ ወዘተ. . . ውስጥ ለውስጥ አድናቃፊ ስራዎች ተጠናክረው ይሰሩ ፤ በ11ኛው ሰአት ምርጫው እንዲራዘም ይደረጋል የሚል አቋም። ምርጫው በህገመንግስቱ መሰረትና በተያዘለት የግዜ ሰሌዳ እንዲካሄድ የሚፈልጉት የፖለቲካ ሀይሎች ፡ ግዜያቸውን በምርጫ ዝግጅት ተጠመደው እንዲያሳልፉ በማድረግ ምርጫው ቢራዘም ለሚለው የቢሆን እይታ ምንም አይነት ዝግጅት ወይም በቂ ዝግጅት ሳያደርጉ ድንገተኝነት መጎናፅፍ። የለውጥ ሀይሉ ፣ በምርጫ ዙርያ ሲያራምድ የነበረውን ምርጫው ይራዘም የሚል አቋም ፣ 20 እና 30 አመታት ያለምርጫ መቆየት ይቻላል ሲል ቆይቶ አሁን በሚገርም ሰርከስ ተጣጥፎ ምርጫው በሰአቱ እንዲካሄድ ወስነናል የሚለው ይህን ተማምኖ ይመስለኛል።

ይሁንና የህግ ባለሞያዎች ምርጫው ባይካሄድ ከባድና ለማስተናገድ የሚያስቸግር የቁቡልነትና የህጋዊነት ቀውስ እንደሚፈጥር ይናገራሉ። የምርጫው መራዘም ህገመንግስታዊ ስርአቱ በተዘዋዋሪና በትርጉም ሳይሆን በቀጥታ የሚያፈርስ ክስተት እንደሆነ እየገለፁ ነው። ጉዳዩን ውስብስብ የሚያደርገው ይህ ምርጫ የክልላዊ መንግስታት ህጋዊነትና ቁቡልነትንም ጭምር የሚመለክት በመሆኑ ነው። ህጋዊና እውቅና ያለው መንግስት ባለበትም ቢሆን አንዳንድ ክልሎች በጎበዝ አለቃ የሚተዳደሩበት ሁኔታ እየተፈጠረ ባለበት ወቅት ምርጫውን ማራዘም ህጋዊውን የመንግስት መዋቅር አፍርሶ ለጎበዝ አለቆች እውቅና የመስጠት ያክል ውጤት እንደሚኖረው እየገለፁ ይገኛሉ።

በኔ አተያይ ፥ ሀገሪትዋን አንጠልጥሎ ይዘዋት ያለው ብቸኛው ክር ህገመንግስታዊው ስርአት ይመስለኛል። በተለያዩ መንገዶች ቢሸራረፍም እንኳ ከነአካቴው የተበጠሰ ስላይደለ በእንፉቅቅም ቢሆን ወዴት እንደሆነ ባይታወቅም እየተራመድን ነው። ይህ ክር ሙሉ በሙሉ የተበጠሰ እለት ምን እንደሚፈጠር ለማወቅ አዳጋች ነው። የምርጫው መራዘም ሌላው ቀርቶ እየተሰባበረም ቢሆን እንደ ሙጃ ሀገሪትዋን አታብቆ ይዞ እየተጓዘ ያለው የመከላከያ ተቋም ቅቡልነት መቀመቅ የሚያወርድ ነው የሚሆነው። መከላከያው በግለሰብ ሊታዘዝ አይችልም። ጠ/ሩ ህገመንግስታዊ ስልጣናቸው ከ1 አመት በኋላ ያበቃል። ከዛ በኋል የሚያዙት የግል ሰራዊት ከሌላቸው በስተቀር የኢትዮጽያ መከላከያ ሰራዊትን የሚያዙበት ምንም አይነት ህጋዊ መንገድ ሊኖር አይችልም። ቢያንስ በሁሉም የኢትዮጽያ የፖለቲካ ሀይሎች ተቀባይነትን የሚያጎናፅፍ መንገድ ሊኖራቸው አይችልም። በእርግጥ ጠ/ሚሩ ይህንን በመረዳት በመከላከያው ከፍተኛ ስራ እየሰሩ አንደሆነ ማሳያዎች አሉ። የታማኝና ቅልብ ሰራዊት ግንባታው ይሳካላቸዋል ወይስ አይሳካላቸውም አብረን ለማየት ያብቃን።

ለ. ርእዮተ አለምን በተመለከት ፥- እንዴት ነው ነገሩ?! ኢህአዴግ ልማታዊ ዴሞክራስያዊ መንግስት መስመሬ ነው የሚለው በምን ስሌት ነው?። የሀገሪትዋ ፖለቲካዊና ኢኮኖምያዊ ፖሊሲዎች በውጭ መንግስታት እየተዘወሩ ባለበት ሁኔታ ይህ መስመር እንዴት ሊኖር ይችላል። ሜጋ ፕሮጀክቶቸ የጠላት የልማት እቅዶች ይመስል እየታጠፉና እየተሰረዙ ባለበት ሁኔታ ልማታዊነት እንዴት ይኖራል?። የተጀመሩትን ፕሮጀክቶች መሰርዝስ እሺ ይሁን (የምያቀርቡትን ሰንካላና የጥላቻ ምክንያቶች እንቀበል) ፤ የሀገሪቱን አንጡራ ሀብቶች በጨረታና በስጦታ ለመቸርቸር የተዘጋጀ መንግስት በየት በኩል ነው የልማታዊና ዴሞክራስያዊ መንግስት አስተሳሰብ አራማጅ ነኝ ለማለት የሚችለው?። ለመሆኑ እነ አቶ ቧያለው በስብሰባው ነበሩ?። በአደባባይ በህዝብ ሚድያ ቀርበው የከሰረ ሀሳብ ነው ሲሉ አልነበር እንዴ?። ይህ ዥዋዥዌ ሀገርን ዋጋ የሚያስከፍል ይመስልኛል። ምክንያቱም እምነትህና ተግባርህ ከተጣረሰብህ ሄዶ ሂዶ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ መግባትህ አይቀርም። የእኔነትና የማንነት ቀውስ ዋና መነሻው የተግባርና የሀሳብ መጣረስ ነው። ኢህአዴግ ፥ ኢህአዴግ የሚያሰኙትን ሀሳቦችና ተግባሮች በግልፅ አስምሮ እስካልተንቀሳቀሰ ድረስ አመራሩ ፣ አባሉ ፣ ህዝቡና ብሎም ሀገሪትዋ መውጫ የሌለው የእኔነትና የማንነት ቀውስ ውስጥ መነከርዋ አይቀርም። የሀሳብና የተግባር አንድነት አለመኖር ትክክለኛው የድርጅት ቀውስ መገለጫ ነው። ኢህአዴግ ቀውስ ውስጥ ነው ያለው። ስለሆነም ኢህአዴግ የልማታዊና ዴሞክራስያዊ መንግስት ተከታይ ነኝ የሚል ከሆነ ፣ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በተለይም የህዳሴያችን ተምሳሌት የሆነውን የህዳሴ ግድብና ሌሎችም ፕሮጀክቶችን ተረባርቦ ያስቀጥል። ለሽያጭ ያቀረባቸውን እንደ የኢትዮጽያ አየር መንገድ ፣ ቴሌ የመሳሰሉትን በመሰረዝ ወደ መስመሩ መግባቱን ያረጋግጥ ፣ አስገዳጅ ጨረታ ውስጥ ካልገባ።

ከላይ የተገለፀው ኢህአዴግ በተግባር ከልማታዊና ዴሞክራስያዊ መንግስት አስተሳሰብ እየወጣ ስለመሆኑ ውስን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሳያዎች ሆኖ ፥ በድርጅታዊና መንግስታዊ ስራዎች እየተካሄዱ ያሉት ክንውኖችም ልማታዊነትም ሆነ ዴሞክራስያዊነት የሚስተዋልባቸው አካሄዶች አይደሉም። በስልጣን ክፍፍል ፣ በሹመት አሰጣጥ ፣ የውጭ ግኑኝነት ፖሊሲ ፣ እነዚህ ሁሉ የሚያሳዩት ኢህአዴግ ከልማታዊና ዴሞክራስያዊ መንግስት አስተሳሰብ እጅግ እርቆ እንደሄደ ነው። ህወሓት ልዩነታችን የመስመር ልዩነት እንጂ ፕሮሲጀራል አይደለም ሲልም እነዚህን ሁነቶች በማየት ነው። በግላጭ በጠራራ ፀሀይ ልማታዊና ዴሞክራስያዊ መስመሩን እንክትክት እያደረግክ ፣ ስለ ዴሞክራስያዊ ማእከላዊነት በጠባብ አደራሽ ውስጥ መከራከሩ ፋይዳ ቢስ ነው።

ሐ. ህወሓትን ማድነቅን በተመለከተ - ይህ አላስፈላጊ የነበረ አድናቆት ይመስለኛል። ህወሓትን መሆን እየተቻለ ማድነቅ ምን አመጣው?። በግልፅ ፣ በአሽሙር ፣ በሽርደዳ ፣ በሾርኔ ቁም ስቅሉን ስታሳየው የነበረውን ድርጅት አይንህን በጨው አጥበህ ማድነቅ ወደ ተግባራዊ አክብሮት እስካልተለወጠ ድረስ ለማንም የሚፈይደው ነገር ያለ አይመስለኝም። ያውም ቤት ዘግተህ መደናነቅ ያው ነፋስ ነው። ልባዊ ከሆነ ፣ ተሞክሮ መውሰድና በተለይ በህወሓት እየተደረግ ያለው የማጠልሸት ፕሮፖጋንዳ መጀመርያ ሂደቱ እንዲቆም ማድረግ በሁለተኝነትም የደረሱትን ጉዳቶች ማስተካከል ነው ተገቢው የአድኖቆት መግለጫ። ሀገር እንዳትፈርስ ከሚል አርቆ አሳቢነት ስልጣንን በሰፌድ አድርጎ አሳልፎ የሰጠን አካል ፣ እንደ ሀገር አፍራሽ ሲብጠለጠል ሀይ ማለት ያልፈለገና ያልቻለ ሀይል ብዝግ ስብሰባ አድናቆቱን ቢገልፅ መጠራጠሩን ወደከፍ ያለ ደረጃ የሚያስድግ እንጂ መተማመንን የሚፍጥር ሊሆን አይችልም።

በዚህ በጠባብ አደራሽ ተከናውኖ የስበሰባው ይዘት በአውላላ ሜዳ ላይ በተዘረገፈው የ ኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ሌሎች አስደማሚና ግራ የሚያጋቡ ያልተለመዱ አስተሳሰቦችና ንግግሮች ተቀንቅነውበታል። 

መንግስት መንግስት ነው። የፈለገውን ማድረግ ይችላል። ኮ/ል መንግስቱ መቶ ሃያ የለውጥ ሃዋርያ ሲያስቸግሩት የሚገደለውን ገድሎ ሌላውን ጥግ አስይዞ ይህችን አገር ቀጥ አድርጎ መርቷታል። አያስፈልግም እንጂ እዚህ ስብሰባ ጠርቻቹሁ ወታደሮች ጠርቼ ልገድላቹሁ እችላለሁ። ቤቱ ግማሹ አጉረመረመ። ግማሹ ይስቃል። በመሃልም እንዴት እንደዚህ ትላለህ ያሉም አሉ። ሊቀመንበሩ ቀጥለውም መርዝ በውሃ አድርጌ ልጨርሳቹህ እችላለሁ አሉ። ግን ምንም አያስፈልግም አሉ ተመልሰው። ውይይት ይሻላል አሉ።ስለ ጎረቤት አገሮች መሪዎች ያለው።

ይህ ንግግር ፥ የሚይስገለፍጥ ንግግር አይመስለኝም። ከተሰብሳቢዎቹ መሀል ይህ ንግግር ያሳቃቸው ሰዎች በመኖራቸው በጣም አስደንግጦኛል። ቀልድ አይደለም። ጠ/ሚሩን በቃላቸው መውሰድ የማይችል ኢትዮጽያዊ መኖሩ ያስገርማል። ሁሉንም እንደቀልድ ጣል ያደርጓቸው ሀሳቦችን አከናውነዋል። በተለይ ለየት ያሉን ያልተለመዱ ሀሳቦቻቸውን በትጋት ፈፅመዋል። ለጓዳቸው አንደርጋቸው ፅጌ ኢህአዴግን አፈርሰዋሎህ አሉት ፥ ኢህአዴግ ገደል አፋፍ አደረሱት። የሁሉም ክልሎች ፕሬዝዳቶች ይቀየራሉ አሉን ፥ ከትግራይ በስተቀር በሁሉም ክልሎች በሚባል ሁኔታ ምስሌነዎቻቸውን አስቀመጡ። ለግብፁ ፕሪዝዳንት አል ሲሲ ወላሂ የህዳሴ ግድቡ ያለርስዎ ፈቃድ አይሰራም ብለው ቃል ገቡ ፥ ግድቡ ቆመ ፣ ዋና ስራ አስኪያጁ አደባባይ ላይ በግፍ ተገድሎ ተገኘ። መከላከያው ሪፎርም ይደረጋል አሉ ፥ አደረጉት። የወሰንና የማንነት ኮምሽን አቋቁማሎህ አሎ ፥ ቀልዳቸው መሆን አለበት እንጂ ይህ ፀረ ህገ መንግስት ኮምሽን ማቋቋም አይችሉም ስንል ሄዱበት። ፕሪዝዳንታዊ ስርአት ነው የሚበጀን አሉን ፣ የህግና የአዋጅ ማስተካከያ እንኳ ሳይደረግ በትግባር ንጉስ ሆነው ቁጭ አሉ። ሜቲክን መፍረስ ያለበት ተቋም ነው አሉን ፣ አፈረሱት። እንደ ዋዛ ጣል ያደርጉዋቸውን ሀሳቦች በሙሉ አድርገውታል። ምኑ ነው የምያስቀው?። አያደርጉትም አይባልም። እሳቸውም ያሉት አስፈላጊ አይደለም ነው እንጂ አላደርገውም አላሉም። ይህ ማለት አስፈላጊ መስሎ የተሰማቸው ግዜ ፣ ወይም ተቀባይነታቸው የተሟጠጠ ግዜ እንደ ሃ/ማርያም ደሳለኝ መልቀቅያ አስገብተው መሰናበት ሳይሆን የሚጠረገውን ጠርገው ለመደላደል ወደኋላ እንደማይሉ። ይህ ንግግራቸው በተጨማሪም ዋና መልእክቱ ስራ አስፈፃሚውን ለማሸማቀቅ ታስቦ ጣል የተደረግ አስተያየት ይመስለኛል። አብዛኛው የስራ አስፈፃሚው አባል የስቸው ግርፍ ነው። የሳቁትም እነሱ ሳይሆኑ አይቀሩም። የግል ወታደር አስልጥኖ ራሱን የሚያስጠብቅና ፣ በነዚህ ቅልብ ዘቦች ባለስላጣናትና ታላላቅ ሰዎች አውላላ ሜዳ በሚረሸኑበት ገዜ ይህ ንግግራቸው ቀልድ ሊሆን አይችልም። ለዚህም ነው በተለይ የትግራይ ህዝብ የስራ አስፈፃሚ ስብሰባ አለ በተባለ ቁጥር በስብሰባው ይተላለፋሉ ከሚባሉት ውሳኔዎች በላይ ተሳታፊዎቹ በሰላም ይመለሳሉ ወይስ አይመለሱም የሚለው ጥያቄ የሚያስጨንቀው።

በአከባቢያችንና በዙርያችን ስላሉት መንግስታት የተናገሩት የማጣጣልና የማናናቅ አስተያየት የጠቅላይ ሚንስትሩ ግራንዲየስ የስነልቦና ውቅር ከማሳያት አልፎ ሀገርን ዋጋ የሚያስከፍል ሊሆን ይችላል። ትንሽ ሀገር ማለት ምን ማለት ነው?። ሳዳም ሁሴን ኩዌት ትንሽ ሀገር ነች በሚል የፈፀመው ወረራ ፣ ኢራቅ የምትባል ሀገርን ፍርስርስዋ አውጥቶ ህዝቦችዋን ለአሳር ለመከራ ዳርግዋታል። ሁሉም ሀገሮች በመጠንና በህዝብ ብዛት ትንሽም ይሁኑ ትልቅ ፣ በአለም አቀፈ ህግ መሰርት እውቅና ያላቸው ሉእላዊ መንግስታትና ሀገሮች ናቸው። ተገቢውን ክብርና እውቅና በመስጠት ነው የምላሹን ክብርና ጥሩ ግኑኝነት ማጠናከር የሚቻለው።

በመጨረሻም ፥ የኤርትራው ኢሳያስ አፈወርቂን አንስተው እብድ ነው ምን እንደሚያስብ አይታወቅም። ከሱ ጋር መስራት አስቸጋሪ ነው አሉ። እንፈራረም ብለው እሺ እያለ እያገተተው ነው አሉ። ካቢኔውን ሰብስቦ አያቅም። ምን እንደሚያስብ መገመት አይቻልም። ኤርትራ ውስጥ ለውስጥ ሰራዊቷን እያዘጋጀች ነው። ክረምቱ ሲያልቅ ወረራ ፈፅሞ ወደ ጦርነት ሊከተን ይችላል ፥ ይላሉ። ይህን ንግግራቸው ሆን ብለው ህወሓትን ለማደናበርና የሚቀርብባቸውን ከመስመር የወጣ ግንኙነት ለማድበስበስ የተናገሩት ይመስለኛል። በትክክል እምነታቸው እንደዛ ከሆነ ፣ ለምን ትግራይ ካለው ሰራዊት እንዲያውም ሜካናይዝድ ክፍለጦር ልቀንስ ሊወስድ ነው የሚባለው ታድያ እንዴት ሊሆን ይችላል? ለምንስ ከበፊቱ ወረራ ተምረው ዝግጅት ሲደረግ አናይም? ኢትዮጽያ የተወረረችው እኮ እንደ እሳቸው ኢሳያስን እናውቀዋለን ሊወረን አይችልም ብለው በቂ ዝግጅት ማድረጉን እንደ ብክነት ስለቆጠሩት ነው። አንዲት ሀገር ሁለቴ መሳሳትን መፍቀድ የለባትም። ኢሳያስ ከዚህ በላይ የተሻለ ጊዜ አላገኝም ብሎ ሊያደርገው ይችላል ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው። ይሁንና መጠርጠር ብቻ ሳይሆን ፣ ቢያንስ መረጃዎች በሚያሳዩት ልክና የኋላ ታሪክን ታሳቢ በማድረግ ተገቢው ዝግጅት ማድረግ ከአንድ መንግስት የሚጠበቅ ነው። በተጨባጭ በመሬት እየታየ ያለው ሁኔታ ግን የተጋላቢጦሽ ነው። ነው ወይስ ወረራውን ይሁን ብለዋል?። ከኢሳያስ ጋር በቅንጅት እየተሰራ ያለ የጋራ ፕሮጀክት ይሆን እንዴ?። ጥያቄዎቹ ተገቢ ቢሆንም በግሌ የሀገሬ መሪ እነዚህን ቢሆኖችን ልቤ ሞልቼ አያደርገውም ለማለት ባለመቻሌ አዝኛሎህ። ግን እንዴት ለዚህ በቃን?።


Back to Front Page