Back to Front Page

የኢህአዴግ ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ቢጠራስ?

የኢህአዴግ ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ቢጠራስ?

·      አለሁምም የለሁምም የሚል ኢህአዴግን አንፈልግም!

ከብርሃኔ በርሄ 9-9-19

 

1.   ኢህአዴግ በእዉር ድንብር እየተጓዘ ነዉ። አለሁምም የለሁምም እያለን ተቸግረናል። በአሁኑ ጊዜ ኢህአዴግ በ 3 ዋና ዋና ክላስተሮች ተከፋፍሎ አበሳዉን እያየ ነዉ። በአንድ በኩል የኢህአዴግን ግንባርነት ማፍረስ የሚፈልጉ ሀይሎች ኢህአዴግ መኖሩን በማስመሰል በተግባር ግን መሰረቱን እየናዱት ነዉ። አሀዳዊ ኢህአዴግ ለማቋቋም። በሌላ በኩል ደግሞ ፌዴራሊስት ሀይሎች መሰሎቻቸዉን በማፈላለግ የጎንዮሽ ማደራጀት ስራዎች ዉስጥ ተጠምደዋል። በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ ቀድሙዉንም ኢህአዴግንና የኢህአዴግ ስልጣንን ለጥቅም እንጂ አምነዉበት ያልተቀላቀሉትና ስልጣን የተቀበሉት ሀይሎች ከዉስጥ ሆነዉ ኢህአዴግን በማተራመስ የተቃዋሚ ሀይሎች እሳት እንዲበላዉ እያደረጉት ነዉ። ከሶስቱም ሀይሎች ዉስጥ ሁለቱ ሀይሎች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ፌዴራላዊና ህገመንግስታዊ ስርአቱን በማፍረስ ላይ የተጠመዱ ስለመሆናቸዉ ምንም አያጠራጥርም። ካልደፈረሰ ስለማይጠራ የኢህአዴግ ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ ስብሰባ ጠርቶ ሁሉም በመሰለዉ መንገድ መሄድ የሚያስችለዉን ዉሳኔ ማሳለፍ ይኖርበታል።  ፌዴራላዊና ህገመንግስታዊ ስርአቱን በጋራ የሚያስቀጥል ኢህአዴግን እና እዉነተኛ አመራሮችን ይዞ መቀጠል ከፈለገም ተጨባጭ ሊሆን እንደሚችል ገምግሞ የቀድሞዉን ጠንካራ የኢህአዴግ ግንባር ማስቀጠል ይጠበቅበታል። የደፈረሰዉ ጠርቶ ሁሉም የመሰለዉን ቤት መምረጥ ይኖርበታል።

2.   በአስቸኳይ ስብሰባዉ አለመስማማት ቢኖርስ? ባይስማሙ ችግር የለዉም። ኢህአዴግ በራሱ በሶስት ሀይሎች ሊከፋፈል ይችላል። ፌዴራላዊና ህገመንግስታዊ ስርአቱን እንደዚሁም የኢህአዴግን ግንባርነት ወደ አሃዳዊነት  መቀየር የሚፈልጉ ሀይሎች አንድ ድርጅት ሆነዉ መቀጠል ይችላሉ። ይህን የማይቀበሉት ደግሞ ከኢህአዴግ ዉጭ ካሉት ፌዴራሊስት ሀይሎች ጋር አንድ  ግንባር አለያም ቅንጅት ፈጥረዉ ለምርጫ ዉድድር መቅረብ ይችላሉ። በሶስተኛ ደረጃ ከሌሎች ፌዴራሊስት ሀይሎችም ሆነ ከፀረ ህገመንግስታዊና ፌዴራሊስት ሀይሎች ጋር በአሀዳዊነትም ሆነ በቅንጅት መቀጠል የማይፈልጉ ሀይሎች ቢኖሩ በብሄራዊ አደረጃጀት በክልላቸዉ ብቻ የመወዳደርና ክልላቸዉን የማስተዳደር መብታቸዉን አስጠብቀዉ መቀጠል ይችላሉ። ይህ ጉዳይ በፍጥነት ሊለይለት ይገባል። ምክንያቱም በአዲሱ የምርጫ ህግ አንቀፅ 94 መሰረት(ረቂቁ ነዉ የተጠቀሰዉ) ህግመንግስታዊና ፌዴራላዊ ስርአቱን ማስቀጠል የሚፈልጉ ፌዴራሊስት ሀይሎች የምርጫ ጊዜዉ ከመድረሱ አስቀድሞ ቅንጅት ፈጥረዉ ማንነታቸዉን ለምርጫ ቦርድ ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል። በብሄራዊ ድርጅትነት ተነጥለዉ መቀጠል የሚፈልጉትም የጊዜ ገደቡ ከመጠናቀቁ በፊት ተመዝግበዉ እራሳቸዉን ለምርጫ የማዘጋጀት መብታቸዉን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል።

3.   አለሁምም የለሁምም የሚልን ኢህአዴግ አንፈልግም! እንዲለይለት እንፈልጋለን! ይለይለትና ሁሉም በመሰለዉ መስመር ተሰልፎ እራሱን ለምርጫ ያዘጋጅ! ይህን ለማድረግ ዝግጁ አለመሆን በ”ጊዜ የለም” እና “የምርጫ ጊዜዉ በመጠናቀቁ ኢህአዴግ ሀገር የመምራት ሌጅትሜሲ የለዉም” በሚል ሰበብ የሽግግር መንግስት በማቋቋም ፌዴራላዊና ህገመንግስታዊ ስርአቱን ለማፈራረስ ካለ ፍላጎት የሚመነጭ እንጂ ሌላ ምክንያት ሊኖረዉ አይችልም!  

አንተ ምንድን ነህ? ብትሉኝ ፌዴራላዊና ህገመንግስታዊ ስርአቱን ማስቀጠል ከሚፈልጉት እና የኢህአዴግን አሀዳዊ ፓርቲነት በፅናት ከሚቃወሙት የህወሓት አባላት አንዱ ነኝ!

 

Videos From Around The World

Back to Front Page