Back to Front Page

በኢትዮጽያና በኤርትርያ መካከል እየተደረገ ያለ ቀርቶ፣ የተጀመረ የእርቅ ሂደትም የለም!

በኢትዮጽያና በኤርትርያ መካከል እየተደረገ ያለ ቀርቶ፣ የተጀመረ የእርቅ ሂደትም የለም!

 

Tsegazeab K.A.

10/21/2019        

 

እርቅ (Reconciliation) አስፈላጊነቱ ፥ ሁለት የተቃቃሩ ፣ የተጎዳዱ፣ የተቀያየሙ፣ የተበዳደሉ፣ ወይም ደግሞ ለመጎዳዳትና ለመጠፈፋፋት የሚሰሩ ሀይሎችና ወገኖችን ከእንድያ ያለ አሉታዊ ማህበረሰባዊ ግኑኝነት ወጥተው መቻቻልና መከባበር ላይ የተመሰርተ ማህበረሰባዊ መስተጋብርና ግንኙነት እንዲመሰርቱ ለማስቻል ነው።

እርግጥ ነው፥ በማህበረሰባዊ ሰላምና ደህንነት ተመራማሪዎችና ባለሞያዎች መሀከል እርቅ (Reconciliation) ምን ማለት እንደሆነ ካላቸው ስምምነት ይልቅ፣ ምን ማለት እንዳልሆነ ያላቸው ስምምነት ይበልጣል። በእርቅ (Reconciliation) ትርጉምና ምንነት ዙርያ ያለው ልዩነት የሚመነጨው፣ ከራሱ “እርቅ” (Reconciliation) ከሚለው ፅንሰሃሳብ ነው። እርቅ (Reconciliation) ሁለት አበይት ሃሳቦችን አንድላይ በውስጡ ጨፍልቆ ይዞ የሚገኝ ነው። ይሀውም ፥ እርቅ (Reconciliation) በአንድ በኩል ሂደት መሆኑ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ግብ መሆኑ ነው። ይህ የሂደትና የግብ በአንድ ፅንሰሃሳብ ላይ ተደራርበው መገኘት በዙርያው ምርምርና ጥናት በሚያካሄዱ ወገኖች ዘንድ አንድ ወጥ የሆነ ትርጉም እንዳይኖር አድርገዋል። ገሚሱ ሂደቱ ነው ወሳኝ ሲል፣ ሌላው ግቡ ነው ወሳኝ የሚል አተያይ እንዲያራምዱ ምክንያት ሆነዋል።

ይሁንና፥ በመሰረታዊ የእርቅ ማእቀፎች ላይ ሁሉም ባለሞያዎች የጋራ መግባባት አላቸው። ማንኛውም የእርቅ (Reconciliation) ጉዞ ስኬታማና ሙሉ ይሆን ዘንድ፣ በሶስት ማእቀፎች ዙርያ አመርቂ ስራዎች መሰራት አለባቸው፥ ይላሉ። እነሱም፣ Remembering, Changing, Continuening ብለው ይከፍሏቸዋል። ለማስታወስ ይረዳን ዘንድ “RCC” ብለን ልንይዘው እንችላለን። ማስታወስ፣ መለወጥና ማስቀጠል ልንላቸው እንችላለን።

Videos From Around The World

ማስታወስ (Remembering) ሲባል ምን ማለት ነው ያልን እንደሆነ ፤ ያለፈን የታሪክ ጠባሳና ቁስል በተመለከተ ታራቂ ወገኖች በጋራ እውቅና መሰጣጠት ማለት ነው። ሁለቱም ወገኖች በእያንዳንዳቸው ላይ የደረሰውን ጉዳት አንዱ በሌላው ጫማ ራሱን በማስገባት(Empathy) ባላንጣው ወይም ተቃራኒው ወገን ደረሰብኝ የሚለውን ጉዳት መገንዘብና እውቅና መስጠት ማለት ነው። እዚህ ላይ፤. . . ግን፣ ነገር ግን፣ ቢሆንም፣ ይሁንና ወዘተ የሚሉ አፍራሽ የሆኑ የደረሰዉን ጉዳት የሚያቃልሉና የሚያሳንሱ ተቀጥያዎች አስፈላጊ አይደሉም። ያለምንም ማስተባበያ ፣ ጉዳት ማቅለያ፣ ማስተዛዘኛ ቃላቶችና መደለያዎች ተቃራኒው ወገን የደረሰበትን ጉዳት ቆጥሮ እውቅና መስጠት፤ አንተ ላይ ደረሰብኝ የምትለውን በደልም እንዲሁ አስቆጥረህ በማቅረብ በደል መፈፀሙንና ስህተት መሰራቱን መቀበልና ሙሉ እውቅና መስጠት/መሰጣጠት ማለት ነው። ለምሳሌ ፥ ራሱን በራሱ ነፍጠኛ ነኝ ብሎ የሚጠራ አካል በነፍጠኞች ጉዳት ደረሰብኝ የሚል ወገን ጋር እርቅና አብሮ መኖር የሚፈልግ ከሆነ፣ ጉዳት ደረሰብኝ የሚለው ወገን የምያቀርበውን ስሞታ ያለምንም ቅድመ ሁኔታና ማመካኘት በደሉን እውቅና መስጠት ያስፈልጋል። ለበጎ ያሰብኩት ነው ፣ እንዲህና እንደዝያ ያለ ጥቅም አግኝተህበታል፣ የሚል የተፈፀመውን ተግባርና የደረሰውን በደል ተገቢ ለማስመሰል የሚደረጉ ሙከራዎች በሙሉ የእርቅ ሂደቱን በማደናቀፍ የመጨረሻው የእርቅ ግብ የሆነውን አብሮ የመኖር አላማ እውን እንዳይሆን ያደርጋል። እዚህ ላይ፥ የታሪክ መጥፎ ትውስታዎች ላይ የጋራ ስምምነት ለመፍጠር በሚደረግ ሂደት የሚፈፀም የተለመደ ስህተት፣ በዳይ የተባለው ወገን እንዲፀፅት ለማድረግ የሚደረግ ሙከራ ነው። ፀፀት በሁለት ወገኖች ለሚደረግ እርቅ ስኬት፣ የግድ መኖር ያለበት ግብኣት አይደለም። ፀፀት ከሌላ ወገን ለሚደረግ እርቅ ሳይሆን ፣ ከራስ ጋር ለሚደረግ እርቅ ነው ወሳኝ ግብኣት የሚሆነው። በአጠቃላይ “Mutual understanding of past suffering” የመጀመርያውና ወሳኙ የእርቅ (Reconciliation) ቅድመ ሁኔታ ነው። በዚህ ሰፊ ማእቀፍ ውስጥ የሁሉም ባለድርሻዎችና አጋር ሓይሎች ተሳትፎ ቁልፍ ነው።

ሁለተኛው ማእቀፍ፥ መለወጥ (Changing) ነው። መለወጥ ስንል፥ በታሪክ መጥፎ ትውስታዎችና የደረሱ ጉዳቶች ላይ የጋራ እውቅና ከተረጋገጠ በኋላ (መግባባት ግዴታ አይደለም)፣ ዋና ዋና የችግሩ ምንጭና ለተፈጠረው አሉታዊ ግኑኝነት መሰረት የሆኑትን የአመለካከትና የባህሪ ግድፈቶችን ነቅሶ በማውጣት፣ ለአብሮነትና የጋራ ጥቅም አስተዋፅኦ ማድረግ በሚችሉ አመለካከቶችና ባህሪዎች የሚተኩበት መንገድ መፍጠር ማለት ነው። በዚህ ማእቀፍ ውስጥ በሁለቱም ወገኖች የሚስተዋሉና የሚታዩ ለዘላቂ አብሮነትና የተስተካከለ ማህበራዊ ግንኙነቶች እንቅፋት የሆኑትን ተግባሮችና አሰራሮችን ማስቀረት ፣ አንዱ ለሌላው ስጋት የሚጋርጥበት አቅሞችን ማስቀረት ወይ ማመጣጠን የመሳሰሉትን ማካተት አለብት። ለምሳሌ፥ በህዝብ ለህዝብ ሰላማዊ ግንኙነት ደንቃራ የሚፈጥሩ የወስን፣ የግምሩክ፣ የህግ፣ የንግድ፣ የሰውና ንብረት እንቅስቃሴና ዝውውር ወዘተ የመሳሰሉትን በማስቀረት ለህዝብ የህዝብ ግኑኙነት አወንታዊ አስተዋፅኦ በሚያደርጉ አሰራሮችና ህጎች መተካት፤ በሁሉም ወገን የሚደረግ አሉታዊ የፕሮፖጋንዳና የስነልቦና ጦርነት ቀርቶ የእርስበርስ ግንኙነት በሚያጠናክሩ የሚድያና የህዝብ ግንኙነት ስራዎች መተካት፤ ወታደራዊ መፋጠጦችና ማለዘብና የአንዱ ሃይል ለሌላው ስጋት በማይሆንበት ደረጃ ማመጣጠን ከተቻለም የጋረ የፀጥታና ደህንነት ስራዎችን በጋራ ማከናወን የሚችሉበት ስርአት መዘርጋት ወዘተን ያጠቃልላል። ሲደመር “changing of destructive patterns of interaction between former enemies into constructive relationships, in attitudes and behavior” ተብሎ መቀመጥ ይችላል።

ሶስተኛው ማእቀፍ፥ ማስቀጠል (Continuening) ነው። ከላይ ያሉት ሁለት ማእቀፎች በዋናኛነት የእርቅ ሂደት እንጂ በራሳቸው የመጨረሻ የእርቅ ግብ አይደሉም። በማስታወስና በመለወጥ ላይ የተሳካ ወይም አመርቂ ስራ ከተሰራ ዋናው ቁምነገር የሚሆነው እርቁን ማስቀጠል ወይም ዘላቂ ሰላም (Sustainable peace) የማረጋገጥ ስራ ነው። ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጠው ሁለቱም የቀድሞ ባላንጣዎች የግድ ድብን ያለ አዲስ ፍቅር እንዲጀምሩ በማድረግ፣ በጋራ እውቅና የሰጡትን የታሪክ መጥፎ ትውስታዎችን እንዲረሱ በማስገደድ ወይም ደግሞ ሙሉና የማይሻር ይቅርታ አንዱ ለአንዱ እንዲሰጥ በማድረግ አይደለም። በሌላ አነጋገር “Reconciliation does not require forgetting, forgiving, or loving one another”። ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ መከናወን ያለበት ዋና ተግባር፣ እርቁ ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው የሚያስችል ስራዎችን ወደ መሬት ማውረድ ነው። የእርቁ ሂደት፥ ኢምንት አሉታዊ ተሳትፎ የነበራቸውን ጨምሮ እስከ ቀንደኛ ተሳታፊዎች የተካተቱበት መሆን አለበት። ሁሉንም ተዋንያን ያቀፈ (Inclusive) መሆን ብቻ ሳይሆን፣ ሁሉንም የማህበረሰብና የፖለቲካ አደረጃጀቶችና ዘርፎችን ያካተተ መሆን አለብት። ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥና የቀድሞ ባላንጣዎች የወደፊት የጋራ ግንኙነት ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ ከተፈለገ፤  እርቁ ማህበራዊ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖምያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ስነልቦናዊ፣ የፍትህና ምናልባትም ሀይማኖታዊ ጉዳዮችን ያካተተና በነዚህ ዙርያ የሚነሱ ጥያቄዎችን የተሟላና አጥጋቢ መልስ መስጠት አለበት። ይህ መሆን ሲችል ነው የእርቁን ዘላቂነት ማረጋገጥ የሚቻለው። በነዚህ ዙርያ መልስ መስጠት የሚችል የጋራ ኮሚቴዎችና የጥናት ቡድኖች በማቋቋም የተዘረዘሩትን ጉዳዮች በቀጣይነት መፍታት ያስፈልጋል። ማህበራዊ ትስስርን ወደ ነበረበት ለመመለስ በማህበረሰቡ የአከባቢ መሪዎች ደረጃ፣ የጥበብ ሰዎች ደረጃ፣ የሃይማኖት ሰዎች ደረጃ፣ የፖለቲካ መሪዎች ደረጃ የማቀራረብ ስራዎችን ማከናወን ይጠይቃል። በሁለቱም ወገን የሚነሱ የፍትህና የካሳ ጉዳዮችን ግልፅነት በተሞላበት መንገድና ቀጥተኛ ተጎጂዎችን ባሳተፍ መልኩ መፍትሄ ማበጀት ይጠይቃል። እነዚህን ተግባሮች እያከናወኑ፣ በተለይ ከእርቅ በኋላ ባሉት የመጀመርያ ጥቂት አመታት የጋራ ግጭት የመከላከልና ማስወገድ ስራ የሚሰራ ተቋም ማቋቋም አጋዥ ይሆናል። ሲጠቃለል ፥ እርቅን ለማስቀጠልና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ በመሪዎች በከፍተኛ ደረጃና በሙሁራንና የማህበረሰበቹ ኤሊቶች ደረጃ ከሚደረግ የእርቅ ሂደት ወርዶ በዝቅተኛ ደረጃ በሚገኙት የማህበረሰብ ክፍሎች (Grassroot level) ተግባራዊ መደረግ አለበት። ይህ ካልሆነ፥ እርቁ እያደረ እንደሚያመረቅዝ ቁስል በአንድም በሌላ መልኩ ማገርሸቱ አይቀርም።

 

እንግዲህ የኢትዮኤርትርያ የእርቅ ሂደትን በዚህ ሁሉም የመስኩ ባለሞያዎች በሚስማሙበት የRCC framework for reconciliation ማእቀፍ ስናየው በብዙ መልኩ እርቅ ተብሎ ለመጠራት የሚያስችል ሂደት የተከተለ እንዳልሆነ እንገነዘባለን።

 

ሲጀመር፥ የታሪክ መጥፎ ትውስታዎቻችንን የጋራ እውቅና የሰጠንበት ሁኔታ የለም። ሁሉም ተበዳይ እንጂ በድያሎህ የሚል የለም። ምናልባትም የአንድ ወገን ታሪክ እውቅና የተሰጠው ይመስላል። ይህ እርቅ ሊሆን አይችልም። የአሸናፊዎች ስምምነት ሊባል ይችል ይሆናል። የአመለካከትና የባህሪ ለውጥም አይታይም። በተለይ በአንደኛው ወገን (ኤርትርያ) በኩል የፕሮፓጋንዳና የህዝብ ግንኙነት ስራዎችን ለመለወጥ ፍላጎቱም ያለው አይመስልም። በአጠቃላይ የአለም አቀፍና ከባብያዊ ፖለቲካዊና ታሪካዊ ትርክቶችን ጨምሮ በሚድያዎቹ ሲያከናውናቸው የቆየውን የፕሮፖጋንዳና ስነልቦናዊ ጦርነት ማቆምና መለወጥ አይደለም፣ ተጠናክሮ የቀጠለበት ሁኔታ ነው ያለው። ሌላው ቀርቶ የወታደራዊና የፀጥታ ዝግጁነቱን እንኳ ሲታይ፣ በእርቅ ሂደት ውስጥ ያለ ሀይል አያስመስለውም።

 

የማስታወስና የመለወጥ ስራዎች በሂደት ያሉና በሚስጥራዊ ስምምነቶች እየተሰሩ ነው ብንል እንኳ፥ እርቁን ለማስቀጠል የሚያስችል ስራ ግን አንድም የለም። የእርቅ ሂደቱ አሳታፊ አይደለም። በከፍተኛ የመሪዎች ደረጃም ቢሆን አሳታፊ አይደለም። አሁን ግልፅ እየሆነ እንዳለው፣ ኢህአዴግ የህወሓትን ፍላጎቶችና ጥቅሞች ወክሎ ሊደራደር ይቅርና ፀረ ህወሓት ጥቅሞችን ወግኖ በእርቅ መድረኩ ሲሳተፍ እንደነበር መገመት ይቻላል።በቀጣይም ይህ የሚሆንበት እድል ዜሮ እንደሆነ ግልፅ ነው። በኢትዮጽያና ኤሬትራ መሃከል የሚደርግ ማንኛውም የእርቅ ሂደት፣ ህወሓትና የወከለው ህዝብ ፍላጎትና ጥቅሞች ከግምት ሳያስገባ የሚደረግበት አግባብ የእርቁን አስፈላጊነትና አላማ ጥርጣሬ ውስጥ የሚከት ነው። አንድን የእርቅ ሂደት ዘላቂ ለማድረግ የሚያስፈልገውን ወደ ዝቅተኛ የማህበረሰብ ደረጃ የወረደ የእርቅ ሂደት ቀርቶ፣ በከፍተኛና መካከለኛ መሪዎች ደረጃ እንኳ አሳታፊ ያልሆነ ሂደት ዘላቂ ሊሆን አይችልም። ና በግጭቱ ቀንደኛ ተሳታፊ ነበሩ የሚባሉ ባለድራሻዎችን ያላካተተ የእርቅ ሂደት ስለ ዘለቂነቱና ቀጣይነቱ መወያየትም አይቻልም። መወያያ አጀንዳ መሆን ያለበት የእርቅ ሂደቱ፣ እርቅ ነው መባል ያለበት ወይስ አይደለም የሚል ነው ።

 

በእኔ እይታ፣ ከላይ በተዘረዘሩት አለም አቀፍ የእርቅ ሂደት ማእቀፎችና መሰረታዊ ስነሃሳቦች ስንመዝነው፣ በኢትዮጽያና በኤርትርያ መካከል ፣ አይደለም በሂደት ላይ ያለ የተጀመረ የእርቅ ሂደትም የለም!። ከመጠርጠር በስተቀር፥ ያለው ሁኔታ ምን ሊባል እንደሚችልም አልገባኝም። 

 

 

 

Back to Front Page