Back to Front Page


Share This Article!
Share
የትግራይ ህዝብ በጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አሕመድ መንግስት እምነት እያጣ ነው

የትግራይ ህዝብ በጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አሕመድ መንግስት እምነት እያጣ ነው

ከህዳሴ ኢትዮጵያ

ታሕሳስ 302011 ..

 

ትላንት የሑመራ ኦምሓጀር በር መከፈቱ የትግራይ ህዝብ በተለይ ደግሞ የምዕራባዊ ዞን ህዝብ የተሰማው ስሜት በጣም ከፍተኛ እና ደስታ የተሞላው ነበር፡፡ በተለይ የኢሳያስ መንግስት የዘላንበሳ እና የራማ በሮች በመዝጋቱ ምክንያት የኦምሓጀር በር በቅርብ ይከፍቷል ተብሎ የገመተ ማንም አልነበረም፡፡ ነገርግን በእየሱስ ክርስቶስ የልደት ቀን በኤርትራ ቴሌቪዥን መስኮት ስለ ድንበሩ መከፈት የቀጥታ ስርጭት ሲተላለፍ ብዙ የተደበላለቁ ስሜቶች ነበር በትግራይ ህዝብ የተንፀባረቀው፡፡ የተደበላለቀ ስሜት እንዲፈጠር ያደረጉት ነገሮች ድንበሩ መከፈቱ ሳይሆን ድንበሩ ለመክፈት በተገኙት ባለስልጣናት እና ድንገታዊ መሆን ነው፡፡ድንገታዊ መሆኑ ለበጎ ከሆነ ችግር የለውም በፈረንጆች ባህል ሳርፕራይዝ ነው፣የገና ስጦታ ነው ሊባል ይችላል፡፡

ነገር ግን እንዲህ ዓይነት አገራዊ ጉዳይ ሲፈፀም ቢያንስ ህዝቡም በቻለው መንገድ እንዲዘጋጅ፣ እንዲሳተፍ እና የደስታ ስሜቱን ፍቅሩን በባህሉ በወጉ እንዲገልፅ ለምን አስቀድሞ አልተነገረውም? የምዕራብ ትግራይ ህዝብ ስንት ጊዜ ዳስና ፍሪዳ ጥሎ በኢሳያስ መንግስት በጎ ፈቃድ ስላልታከለበት ስንት ጊዜ ነበር የከሰረው፣ የተሰረዘው፤ ስለዚ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ ድብቅ ሴራ ከሌለው ለምን ቢያንስ ለሑመራ ህዝብ እና ለክልሉ መንግስት አስቀድሞ እንዲዘጋጅ አልተነገረውም፣ ህዝቡ ኮ እንግዶቹ በደንብ ተዘጋጅቶ በኢትዮጵያውያን ባህል ቤት ያፈራውን አብልቶ አጠጥቶ የመጋበዝ ፍላጎት አለው፤ በተለይ ደግሞ ለ20 ዓመት ተዘግቶ ተዳምቶ የነበረ ወንድማማች ህዝብ በደንብ መጋበዝ ምን ችግር አለው? ስለ ድንበሩ መከፈት የሑመራ ህዝብ አመሻሽ ላይ ነበር "ነገ ድንበሩ ሊከፈት ነው" ተብሎ የተነገረው፡፡ በእርግጥ የትግራይ ህዝብ የድንበሩ መከፈት ሲወተውት እና ያለመታከት ሲጠይቀው የነበረ በመሆኑ መልስ ማግኘቱ መልካም ነው፡፡ነገርግን የኢሳያስ መንግስት ሊከፍት ይቅር እና የተከፈቱት የዘላንበሳ እና የራማ በሮች ዘጋቸው፡፡ /ር አብዪ ምናልባት ለምዕራብ ትግራይ ህዝብ የገና ስጦታ ሳርፕራይዝ ለማድረግ አስበው ያደረጉት ነው ሊባል ይችላል፣ ግን ህዝቡ በሩ በመከፈቱ ደስ ቢለውም በደንብ ተዘጋጅቶ ዳስ እና ፍሪዳ ጥሎ ቢቀበላቸው የበለጠ ደስታውን አይችለውም ነበር፡፡

Videos From Around The World

ሌላ ህዝቡን በጣም ያበሳጨው ነገር ቢኖር በዚህ በልደተ ክርስቶስ ቀን አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የሑመራ ኦምሓጀር ድንበር ለመክፈት መምጣታቸው ነበር፡፡ የምዕራብ ትግራይ ህዝብ ከመስቀል ዕለት መስከረም 162011 .. ጀምሮ ድንበሩ በር እንዲከፈት ብዙ ዝግጅቶች አድርጎ የኤርትራ መንግስትን ሲማፀን የነበረ ቢሆንም የኢሳያስ መንግስት ግን ድንበሩን መክፈት ትቶ ወደ አማራ ክልል ሽርጉድ ሲል ነበር የታየው፡፡ ህዝብ ለህዝብ ግንኝነት ገደብ አይደረግበት የሚል ጥያቄ ሲቀርብ፣ ለህዝብ ጥያቄ ደንታ የሌለው መሪ የኢትዮጵያ ህዝብ የሰራውን ልማት ለመመረቅ ሲሯሯጥ ህዝቡ ልብ አብዝቶ በትዕግስት ጠበቀው፡፡ ምክንያቱ የልማቱ ስራ በማየት በቁጭት ሰላም ያመጣል፣ የልማት ትብብር ያደርጋል ስለዚ በቶሎ በሮቹ ይከፍታል ተብሎ ይጠበቅ ነበር፡፡ ነገር ግን አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ከአማራ ክልል ሲመለሱ የተቀሩት ተዘግተው የነበሩ በሮች ሳይሆን የከፈቱት የተከፈቱትን የዛላንበሳና የራማ በሮች ነበር የዘጉት፡፡ ይህ ህዝቡን በጣም አስቆጭቶ የነበረ ሲሆን በትዕግስት እና በተስፋ ሲጠባበቅ ነበር፡፡ እግዚአብሄር የፈቀደው ጊዜ በመድረሱ በሩ ሲከፈት የሑመራ ከተማ ነዋሪ ደስታውን ወሰን አልነበረውም፡፡ ነገር ግን በአከፋፈት ስነስርዓት አቶ ገዱ መገኘታቸው ስሜቱን እንዲደበላለቅ አደረገው፡፡ ለምን? ምክንያቱ በዚህ ጊዜ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የሚመሩት የአማራ ክልል መንግስት የትግራይ ህዝብ ጠላቶች የሆኑትን የደርግ ርዝራዦችን በጎንደር እና በባህርዳር ሰብስቦ የትግራይን መሬት ቆርሶ ለመውሰድ አካኪ ዘራፍ ሲሉ ከማውገዝ ይልቅ ሲያበረታታቸው እና ለትጥቃቸው ህጋዊ ዕውቅና በመስጠት ወራሪ ሀይል እያሰባሰቡ አንድን እርምጃ አልወሰደም፡፡ ሌላ ቀርቶ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በትግራይ ክልል በኪራይ ሰብሳቢነት እና በመሬት ወረራ ወንጀል የሚጠየቁ፣ ከማይክሮ ፋይናንስ ብድር ወስደው በዕዳ የሚፈለጉ የትግራይ ሽፍቶችን በማሰባሰብ የወልቃይት አስመላሽ ኮሚቴ በሚል ስያሜ ማቋቋሙ ሳይበቃ፣ በትግራይ የሚፈለገው ቀንደኛ ሽፍታ ትግራይን ለመተንኮስ በማሰብ የሰሜን ጎንደር የፀጥታ ሓላፊ ኣድርጎ በመሾሙኣቶ ገዱ በትግራይ ህዝብ ከደርግ ተለይቶ የማይታይ እና በከፍተኛ ደረጃ የሚጠላ ባለስልጣን ሆኖዋል፡፡ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አሕመድ ይህን አያውቁትም ኑሮዋል? አይመስለኝም እንኳን ይህ ሌላም ያውቃሉ፣ የኢትዮጵያ ጠ/ሚ አይደሉም እንዴ

ታድያ ይህን እያወቁ ጠ/ሚ ዶ/ር አብዪ የሑመራ ኤርትራ በር ለመክፈት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ይዞ መምጣት ለምን አስፈለገ? ትግራይን ለመጨበጥ፣ የትግራይን ፋብሪካዎች ዘርፎ ለመውሰድ ለክልሉ መንግስት ጥያቄ በማቅረብ ላይ ያለው የአርበኞች እና የጉንበት 7 ታጣቂዎች ከነ ሙሉ ትጥቃቸው እዛው እየቀለበና እያሰማራ ያለው አቶ ገዱ ወደ ትግራይ ክልል መምጣቱ ለሰላም ሳይሆን ለስለላ ነው ብሎ ወጣቱ በጣም በጣም ነው የተቆጣው፡፡

ይህ ተግባር ዶ/ር አብይ አቶ ገዱን ይዞ መምጣት ለሰላም ሳይሆን ምንኛ በትግራይ ህዝብ ላይ ንቀት እንዳለው ያሳየ አስነዋሪ ተግባር ነው የሚል እምነት በአብዛኛው ህዝብ ነግሷል፡፡ ወጣቱ የተሰማውን ስሜት ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መግለፁ ችግር የለውም፣ ችግር የሚኖረው ስሜትህን አትገልፅም ብሎ ማፈን ነው፡፡ ማፈን ደግሞ ምን ዓይነት ጣጣ እንዳለው ባለፉት ሁለት እና ሶስት ዓመታት አይተነዋል፡፡ በዚህ የድንበር አከፋፈት ስነስርዓት ችግር ፈጣሪው የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር የአቶ ደጉ አንዳርጋቸው ቅሌት ነው፡፡ ትግራይን ለመቁረስ፣ የትግራይን ልማት ለማፈራረስ እና ለመዝረፍ የተዘጋጀ ቡድን እያስታጠቁ፣ ይህ ድብቅ ሴራበ21ኛው ክ/ዘ፣ በዘመነ ኢንፎርሜሽን አይታወቅም ብሎ በማሰብአቶ ገዱ በድፍረት የትግራይን መሬት መርገጣቸው፣ ለሰላም ያላቸው ቁርጠኝነት ሳይሆን ምንኛ በትግራይ ህዝብ በተለይ ደግሞ በምዕራብ ዞን ህዝብ ያላቸው ንቀት ማሳየታቸው ነው ችግሩ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ታሪካዊ ጠላቶች፣ አቶ ገዱ በሚመሩት አማራ ክልል ውስጥ ተወሽቀው ህዝብ ለህዝብ ግንኝነት እያሻከሩ፣ የትግራይ ህዝብ እና የአማራ ህዝብ የሚያደርገው የንግድ ግንኝነቶችን በመንጋ ፍትህ እንዲዘጋ እያደረጉ፤ የትግራይ ህዝብ ጠላቶች በአማራ ክልል ሆኖው ትግራይን ለመውረር በስንቅ እና በትጥቅ እየተዘጋጁ ባለበት ጊዜ አቶ ገዱ ወደ ሑመራ የሰላም ልዑክ ሆኖው ለማስመሰል መምጣታቸው እውነትም በጣም ያናድዳል፡፡

የትግራይ ህዝብ ለሰላም፣ ለፍትህ፣ ለዴሞክራሲ ብሎ ከፍተኛ መስዋእትነት በመክፈል አገራችን ኢትዮጵያ እዚህ ደረጃ እንድትደርስ የአንበሳ ድርሻ ነበረው፡፡ አሁንም በአገራችን የለውጥ አስፈላጊነት ከማንም በማያንስ መልኩ የደገፈ እና ለውጡ ካልመጣ በርካታ ህይወት የከፈለበትን ስርዓት ወደ ሗላ እንደሚመለስ ስለሚያውቅ ለውጡ ትክክለኛ መስመሩ ይዞ እንዲሄድ በከፍተኛ ትንቅንቅ ላይ ይገኛል፡፡ የለውጡ አስፈላጊነት እና አንገብጋቢነት ቢያምንበትም በአሁኑ ሰዓት ለውጡን ወደፊት ማራመድ የሚችል አመራር ባለማግኘቱ ግን በከፍተኛ ስጋት ውስጥ ይገኛል፡፡ የዚህ መገለጫዎችም የጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አሕመድ ንግግሮች፣ የተስፋ ቃሎች እና በተግባር እየሆነ ያለው የተለያዩ መሆን አንዱና ዋነኛው ምክንያት ነው፡፡ ዶ/ር አብይ ስለ ፍቅር፣ ስለ ሰላም፣ ስለ አንድነት፣ ስለ መቻቻል ሲሰብኩ ማን ደስ ያላለው አለ? ማንም አልነበረም፡፡ ዶ/ር አብይ በመጀመሪያ ስልጣን በያዙበት ጊዜ ከህዝብ ጋር ያደረጓቸው ግንኝነቶች በሙሉ ውጤታማ እና የህዝብ ድጋፍ የተቸሩባቸው ነበሩ፡፡ ከዛ ቦሗላ ግን ቃላት እና ንግግር ሌላ ተግባር ሌላ ሆኖ ሲታይ ህዝብ በመንግስት ላይ አመኔታ እያጣ መጥቷል፡፡ የጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አሕመድ የለውጥ ሂደት ሲታይ እስካሁን ድረስ ኢህአዴግ 27 ዓመት የፈጠረውን ስርዓት ሲያፈርሱ እንጂ ሲገነቡ አይታይም፡፡ የኢህአዴግ መዋቅር በፈረሰባቸው ክልሎች በሙሉ ህዝቡ ሰላም እና መረጋጋት አጥቶ በሲቃይ ይገኛል፡፡ ይህ የለውጥ ሂደት ከከሸፈ ኢትዮጵያ ወደ ማትወጣው ችግር ውስጥ እንደምትገባ የትግራይ ህዝብ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ለውጡ ተጨናግፎ እሚቆም ከሆነ ህዝብ ስላልፈለገው ሳይሆን አመራር በማጣቱ ነው፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ ኢህአዴግ መሽተት አለበት፡፡ ኢህአዴግ ለለውጥ አዲስ አይደለም፡፡ ብዙ ለውጦች መርቶ ለድል የበቃ ድርጅት ነው፡፡ አሁንም ለውጡ ከቲም-ለማ ወጥቶ ወደ ኢህአዴግ መሸጋገር አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ጎርፍ እያሳሳቀ ይወስዳል እንደሚባለው አደጋው እያሳሳቀ ወዳልተፈለገ እንደሚወስደን ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ይህ ደግሞ ጠ/ሚ ዶ/ር ኮነሬል አብይ አሕመድ የታሪክ ተወቃሽ እና የሊቀመንበር ኮነሬል መንግስቱ ሀይለማርያም ዕድል እንደሚገጥማቸው መገንዘቡ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ተወደደም ተጠላም የትግራይ ህዝብ ለዶ/ር አብይ መንግስት በጣም ነው የጠላው፡፡ ይህ ደግሞ የማስጠንቀቂያ አዘል ደወል ነው፡፡ ሰሚ ካለ ጊዜው እየረፈደ ነው፡፡

hidaseethiopia@yahoo.com ወይም hidaseethiopiaa@gmail.com

 

Back to Front Page