Back to Front Page

ለአዲስ አበባ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ለኢንጂነር ታከለ ኡማ

ለአዲስ አበባ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ለኢንጂነር ታከለ ኡማ፡-

ለዐድዋ ድል መዝክርነት የሚገነባው ማእከል ሁሉንም ኢትዮጵያዊ፣ አፍሪካውያን እና መላው ጥቁር ሕዝቦችን የነጻነት ተጋድሎ ታሪክ የሚወክል ይሁን!!

                           

በተረፈ ወርቁ 5-11-19

1.  ታሪካዊ መንደርደሪያ

‘‘The Adowa Victory provided practical expression to Ethiopianism: self-worth, dignity, unity, confidence, self-reliance, race pride, spirituality and freedom from colonialism.’’ ~ Nelson Rohillala Mandela

ዛሬ በነጻነት የምንኖርባት ውድ፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ በብዙ አባቶቻችንና እናቶቻችን - ጀግንነትና ከብረት የጠነከረ ወኔ፣ ቆራጥነትና ብርቱ መሥዋዕትነት በክብርና በኩራት የተረከብናት ባለ ታላቅ ታሪክ ባለቤት የኾነች ሀገር ናት፡፡

ከቅርብ የታሪካችን ዘመን ብንነሣ እንኳን ‹‹የቋራው አንበሳ›› ዐፄ ቴዎድሮስ ከደባርቅ እስከ መቅደላ ከግብጻውያን እና ከእንግሊዝ ጦር ጋር ተፋልመው፣ ዐፄ ዮሐንስ ከጉራዕ እስከ ጉንደትና መተማ ድረስ ዘልቀው  ከደርቡሾችና ከግብፃውያን ጋር ተናንቀውና አንገታቸውን ለሰይፍ ሰጥተው፣ ‹‹አፍሪካዊው ጀግና የጦር ጄኔራል›› የሚል ክብርን የተጎናጸፉት አሉላ አባ ነጋ በዶጋሊ ግንባር ከወራሪው ጣሊያን ሰራዊት ጋር በጀግንነት ተጋድለው፤

ዐፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱም ከአምባላጌ፣ መቀሌ እስከ ዐድዋ ግንባር ድረስ- ከበርካታ ውድ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ልጆቿ ያደረጉት የእምቢ ለነጻነቴ ተጋድሎና ያስመዘገቡት አንጸባራቂ ድል፣ የእነ ኮ/ል አብዲሳ አጋ ከኢትዮጵያ አልፎ እስከ ሮም ድረስ በተሰማው ጀግንነቱ የጻፉት ክቡር ታሪክ፣ የፋሽስት ጦር በአምስቱ አርበኝነት ዘመናቸው እረፍት የነሡት ‘‘የበጋው መብረቅ’’ በመባል የሚታወቁት ጀግናው አርበኛ እና የጦር መሪ፣ ሌፍተናት ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ አኩሪ ጀግንነት ገድል፤

Videos From Around The World

የእናት አርበኞቻችን እነ ሸዋረገድ ገድሌ፣ እነ ቡዝነሽ ከበደ… እልፍ የሚሆኑ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን አባቶቻችንና እናቶቻችን ለሀገራቸው ኢትዮጵያ ነጻነት፣ ልዑላዊነት እና አንድነት የከፈሉት መሥዋዕትነት፣ ዓለም ሁሉ በአድናቆት የሚመሰክርለት፣ ታሪክ በአድናቆት የከተበው እውነታ ነው፡፡ የታሪክ መዛግብት እንደሚመሰክሩትም፤ ይህ የአባቶቻችን የነጻት ተጋድሎ፣ ከብረት የጠነከረ አይበገሬነት፣ ወኔ እና ጀግንነት ሀገራችንን ኢትዮጵያን- ለአፍሪካ፣ ለአፍሪካ አሜሪካውያን፣ ለመላው ጥቁር ሕዝቦች እና እንዲሁም ነጻነታቸውን ለሚወዱና ለሚያከብሩ የሰው ልጆች ሁሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ - የነጻነት ቀንዲል እና የሉዓላዊነት ትእምርት/Symbol እንድትሆን አድርገዋታል፡፡

ጀግኖች አባቶቻችን እና እናቶቻችን ለሀገራቸው ነጻነት ካደረጉት አያሌ ጦርነቶች መካከል ደግሞ፤ የዐድዋን ጦር ግንባርን እና ድሉን ታሪክ በታላቅነቱ የሚያስታውሰው ነው፡፡ በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ አውሮፓውያን ይህችን የሺሕ ዘመናት የነጻነት ታሪክና የገናና ሥልጣኔ ባለቤት የሆነች ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ ያደረጉት ሙከራ ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ‘በዐድዋ ግንባር’ ሕልማቸውን ከንቱ አስቀርተውታል፡፡ ከዚህም የተነሣ፤ ባለውለታዎቻችን፣ ጀግኖቻችን በዓለም መድረክ ነጻነቷ፣ ታሪኳና ክብሯ የተጠበቀች ሉዓላዊ፣ ታላቅ ባለ ታሪክ ሀገርን- ኢትዮጵያን በታላቅ ክብር አስረክበውናል፡፡

 

2.  ዐድዋ የኢትዮጵያውያን አንድነት እና ነጻነት ሕያው ምስክር ነው!

በዐድዋ ተራሮች ላይ ከመቶ ዓመታት በፊት አባቶቻችን ሃይማኖት፣ ዘር፣ ቋንቋ ሣይሉ በአንድነት በመተባበር ያስመዘገቡትን ታላቁና ታሪካዊው የዐድዋ ድል- ለሁላችንም ኢትዮጵያውን የአንድነታችን ሕያው ምልክትና ብሔራዊ ኩራታችን ነው፡፡

ትናንትናት፣ ዛሬም፣ ነገም፣ ሁሌምና መቼም በዐድዋና በሶሎዳ፣ በእነዛ ሰማይን ጫፍ የነኩ በሚመስሉ በሰሜን ግዙፍ ተራሮች ማዶ ልቆና ገኖ የሚሰማ አንድ የነፃነት ደወል ድምፅ፣ የነፃነት ልዩ ውበት አለ፡፡ በጀግኖቻችን እልፍ የሕይወት መሥዋዕትነት- በደም የተቀደሰ፣ በደም የተዋበ፣ በደም ለዘመናት የጸና፣ የኃያላኑን የአውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎችን ሕልም ያመከነ፣ ጽኑ ክንዳቸውን የረታ፣ በምንምና በማንም ያልተበገረ፤ በሁላችንም ልብ ውስጥ ዘልቆ የሚሰማ ክቡር ሕያው የነፃነት ድ-ም-ፅ!!

ይህ የእናት አገር ኢትዮጵያ የጀግኖች ልጆቿ የነጻነት ተጋድሎ ከአድማስ አድማስ ያስተጋባ፣ አፍሪካን፣ መላው ጥቁር ሕዝቦችንና በአጠቃላይ ነፃነታቸውን የሚያፈቅሩ የሰው ልጆችን ሁሉ በአንድነት ያስተሳሰረ ውብ የነፃነት ልዩ ዜማ፣ የአንድነታችን ልዩ ቅኔ ነው፡፡ ዛሬ በኩራት የምንተነፍሰው ውብ የነጻነት አየር፣ በዓለም ፊት ደረታችንን ነፍተን የምንናገርለት አባቶቻችን የነጻነት ታሪክ ተጋድሎ፣ በደም የተገዛ፣ በደም የከበረ፣ በዋጋ የማይተመን የብዙዎች ክቡርና ውድ ሕይወት የተከፈለበት ነው፡፡ ተወዳጇ አርቲስት እጅጋየሁ/ጂጂ በዓድዋ ዜማዋ ላይ እንዲህ እንደተቀኘችው፣

‘‘የተሰጠኝ ሕይወት ዛሬ በነጻነት፣

ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት፡፡

ምስጋና ለእነርሱ ለዓድዋ ጀግኖች፣

ለዛሬ ነጻነት ላበቁኝ ወገኖች፡፡’’

በአንፃሩ ደግሞ አሳዛኙ ጉዳይ ይህ የሁላችን ኢትዮጵውያንና አፍሪካውያን የነጻነት ኩራት ምንጭ የሆነ ድል የልዩነታችን ማስመሪያ የታሪክ ክሥተት ከሆነ መሰነባበቱ ነው፡፡ የታሪክ ሊቃውንቱ “ታሪክ የትውልዶች መገናኛ ድልድይ ነው” ሲሉ ቢደመጥም፤ ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን ታሪክ የትውልዱ የልዩነት ማስመሪያ ቀይ ቀለም ነው፡፡ የዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ለዘውግ ፖለቲካ ማፋፋሚያ ዓይነተኛ ማገዶ ሆኗል፡፡ ላለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ታሪክ ለየዘውጉ (በ“ጨቋኝ” “ተጨቋኝ” ትርክት) ዘውጋዊ ንቃት መፍጠሪያነት እንጂ ከዚህ በተሻገረ መልኩ የአገራዊ ውህድ ህላዌ መጋቢና ደጋፊ ሆኖ ሲገለጽ አይስተዋልም፤ አልተስተዋለምም፡፡

የማንነት ፖለቲካን የታከከ የታሪክ ትርጓሜ ጐልቶ በሚታይበት ኢትዮጵያ፤ በአገር ግንባታ ሂደቶች የታዩ ክስተቶችን በተመለከተ የበረታ ፉክክርና ‘እኛ እና እናንተ እኮ’ መፈራረጅና ማግለል ይስተዋልበታል፡፡ አፍሪካውያንና ዓለም ሁሉ በአድናቆት የጻፉለት፣ የተናገሩለት፣ የዘመሩለት የዐድዋ ድላችንም ከዚሁ አክራሪ ብሔርተኞች የታሪክ ውዝግብና ሽሚያ ከመጠለፍ አልዳነም፡፡ ስለሆነም ይህ የሁላችን ኩራትና የነጻነታችን ትእምርት/Symbol የሆነ ድል ለመዘከር በፒያሳ የሚገነባው የዐድዋ ማእከል ሁላችንንም ኢትዮጵያውያንን በአንድነት መንፈስ የሚያስተሳስረን መሆን እንዳለበት ከወዲሁ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

ክቡር ኢንጂነር ታከለ ኡማ የዐድዋ ማእከል ዘር፣ ጎሳ፣ ሃይማኖት፣ ፆታ ሳይለይ ሁሉንም ኢትዮጵዊ በአንድነት የሚወከልበት፣ የቀደመው አኩሪ የጀግንነት ታሪካችን በፍቅር ቃል-ኪዳን የሚያስተሳስረን እንዲሆን ቢታሰብበት መልካም ነው፡፡

ከዚሁ ከላይ ካነሣሁት ሐሳብ ጋር በተያያዘም ባሳለፍነው ሳምንት የኪነ ሕንጻ ባለሙያ አርቴክት ዮሐንስ መኮንን የተባሉ ሰው በመዲናችን አዲስ አበባ ሊገነቡ ስለታሰቡት ታላላቅ ፕሮጀክቶች ባለሙያዎችን ለውይይት የሚጋብዝ መድረክ ‘በአዲስ አበባ ማእከል’ እንደሚደረግ በማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ አስፈርው ነበር፡፡ እኚሁ ባለሙያ ከውይይት በኋላ በገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍም፤ ‘‘በከተማችን ለመሥራት የታቀዱት እንደ ዐድዋ ማእከል ያሉ ታላቅ ፕሮጀክቶች ብዙ ወጪ የሚጠይቁ፣ የሚወክሉት ሐሳብ ግዙፍ፣ የትናንቱን ታሪክ፣ ዛሬን አስተሳሰብ እና የነገውን ተስፋ የሚወክሉ በመሆናቸው በመንግሥት/ጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በኩል ተገቢው ትኩረት እንዲሰጣቸው፤’’ ጠይቀዋል፡፡

አርክቴክት ዮሐንስ ጨምረውም፤ ‘‘እነዚህ ፕሮጀክቶች ትውልዱንና ሀገራዊ ታሪኮችን በሚወክል መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ እጅግ ከፍ ያለ ሀገራዊ ዕውቀትን/ክህሎትን እና ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ የሚጠይቁ በመሆናቸው ተግባራዊ ከመሆናቸው በፊት በሀገር አቀፍ ደረጃ ባለሙያዎችን ያሳተፈ ውይይት አስፈላጊ መሆኑን አሰምረውበታል፡፡      

አርክቴክት ዮሐንስ ያነሷቸው ሐሳቦች ሁላችንም የሚያስማማን ይመስለኛል፤ ስለሆነም የከተማዋ አስተዳደር የዐድዋ ድልን ለመዝከር ሊገነባ ያሰበው ማእከል- አንጋፋ የታሪክ ምሁራን፣ ሀገራዊ የኪነ ጥበብ ቅርሶቻችንና እሴቶቻቸውን በሚገባ የሚያውቁና የተረዱ፣ የሚያከብሩ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት፣ ሁላችንም የእኔ/የእኛ ነው ብለን የምንኮራበት ፕሮጀክት ይሆን ዘንድ ይገባዋል፡፡ ይህ ትልቅ ፕሮጀክት ሌሎች እኔ/እኛ ያልተወከልንበት ብለው የሚያኮርፉበት፣ ጥቂቶች ደግሞ ታሪክን በመሻማትና የታሪክ ሐቅን በመበረዝ/by Distorting History የግል ፍላጎታቸውን መሰሪ ዓላማቸውን የሚያስፈጽሙበት እንዳይሆን ከወዲሁ በአጽንኦት ሊታሰብበት ይገባል እላለሁ፡፡

 

3.  ዐድዋ ለአፍሪካውያን እና ለመላው ጥቁር ሕዝብ የነጻነት ፋና ነው!

የአፍሪካውያን፣ የጥቁር ሕዝቦች ታሪክ የሰው ዘር ታሪክ ነው፡፡ የሰው ዘር ምንጭ፣ ባለ ግዙፍ ታሪክና የገናና ሥልጣኔ ባለቤትና እምብርት ኾና የምትጠቀሰው አፍሪካ፣ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ያላት ስፍራ ደግሞ እጅግ ደማቅ፣ ታላቅና ግዙፍ ነው፡፡ ሺህ ዘመናትን በሚያስከነዳው የአኅጉሪቱ ታሪክ ውስጥ አፍሪካውያን እንደተቀሩት የዓለም ሕዝቦች ኹሉ በታሪካቸው አያሌ የብርሃንና የጨለማ ዘመናትን ዐይተዋል፣ አሳልፈዋል፡፡ በአፍሪካውያን ካለፉባቸው የጨለማ ዘመናት አስከፊ ታሪካቸው መካከልም ትልቁንና የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው ደግሞ የአኅጉሪቱ ሕዝቦች በባርነትና በቅኝ ግዛት ቀምበር ስር ወድቀው ያሳለፉት ይኸው አስከፊው የባርነትና ቅኝ ግዛት ዘመን ታሪካቸው ነው፡፡

መላው አፍሪካና ጥቁር ሕዝብ በባርነትና በቅኝ ግዛት ቀምበር ስር ወድቆ በሚማቅቅበት በዛ የአኅጉሪቱ የጨለማና የሰቆቃ ዘመን ታሪክ ውስጥ ጥቁር ሕዝቦችንና መላው የሰው ልጆችን ያስደመመ፣ ያስደነቀ፣ በደስታና በሐሴት ጮቤ ያስረገጠ የነጻነት ተጋድሎ ከምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር ከወደ ኢትዮጵያ ነበር የተሰማው፡፡ ነጻነታቸውን፣ ሉዓላዊነታቸውን፣ ሃይማኖታቸውንና ክብራቸውን የሚያፈቅሩ ሕዝቦች በአፍሪካ ምድር አዲስ የሆነ የአይበገሬነትና የነፃነት ተጋድሎ ሕያው ታሪክን በደማቸው ጻፉ፡፡

የነጻነትን ልዩ ውበትንና ታላቅነትን በዐድዋ ተራራ በደማቸው የጻፉ የቀደሙ አባቶቻችንና እናቶቻችን በአፍሪካ ምድር፣ በጥቁር ሕዝቦች ምድር- አጥንታቸውን ከስክሰው ነጻነት ለሰው ልጆች ከፈጣሪ ዘንድ የተቸረ የማይገሠሥ ጸጋ መኾኑን ዳግመኛ ለመላው ለዓለም አረጋገጡ፡፡ ነጻነታቸውን የሚያፈቅሩ ሕዝቦች የነጻነት ብርሃን ጎሕን በደማቸው ቀለምነት፣ በአጥንታቸው ብዕርነት በጻፉ፣ ባበሰሩ ኢትዮጵያውያን ሕዝቦች ለአፍሪካና ለጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ቀንዲል ተስፋ የሆነ ብርሃን ሸማም ተለኮሰ፡፡

ከጥንታዊቷና ከባለ ግዙፍ ታሪኳ የኢትዮጵያ ምድር የታየው ይህ የዐድዋው የነጻነት ጎሕ በመላው ዓለም የነጻነትን ብርሃን ፈነጠቀ፣ እምቢ ለነጻነቴ፣ እምቢ ለአገሬ፣ እምቢ ለክብሬ… የሚል ወኔንና መንፈስን ናኘ፡፡ በእርግጥም ዐድዋ ለአፍሪካ፣ ለጥቁር ሕዝቦችና በአጠቃላይም ነጻነታቸውን ለሚያፈቅሩ የሰው ልጆች ሁሉ የተበሰረ የነጻነት የምስራች ደወል ነበር፣ ነውም!!ድዋ የኢትዮጵያውያን ድል ብቻ አይደለም፤ የአፍሪካ፣ የመላው ጥቁር ሕዝብ እና ነጻነታቸውን የሚያፈቅሩ የሰው ልጆች ሁሉ የተቀዳጁት ታላቅ ድል ነው፡፡

ስለሆነም፤ ‘‘የአፍሪካ መዲና’’ ተብላ በምትጠራ በከተማችን አዲስ አበባ ሊገነባ የታሰበው የዐድዋ ማእከል ሁሉንም ኢትዮጵያዊ፣ አፍሪካውያን እና መላው ጥቁር ሕዝቦችን የነጻነት ተጋድሎ ታሪክን እና የነጻነት መንፈስን የሚወክል መሆን ይኖርበታል፡፡ በዚህ ረገድ መንግሥት ለዐድዋ ማእክል ግንባታ ኢትዮጵያውን፣ አፍሪካውያን እና አፍሪካ አሜሪካውያን የታሪክ ምሁራን፣ የቅርስ ጥናት ተመራማሪዎችን እና የኪነ ሕንጻ ባለሙያዎችን ተሳትፎ እንዲያደርጉ፣ ሐሳብ እንዲያቀርቡ መጋበዝ ያስፈልጋል፡፡

በተጨማሪም የዛሬዎቹ እና መጪው አፍሪካውያን ትውልዶች ዐድዋ- ‘የእኛም ድል ነው!’ ብለው እንዲኮሩበት ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ዐድዋን የመሰለ ታላቅ ድል፣ እንግሊዛዊው የታሪክ ጸሐፊ ጆርጅ በርክሌይ እንዳለውም፤ ‘‘የዓለም ታሪክ ለሁለት የከፈለና ኢትዮጵያውያንና መላው አፍሪካውንን በዓለም መድረክ በክብር ከፍ ያደረገን ይህን ታላቅ የታሪክ ክሥተት” ዐድዋን የአፍሪካውያን ሁሉ ኩራት እንዲሆን በማድረግ ረገድ መንግሥትም ሆነ በእኛ በኩል ይህ ነው የሚባል ሥራ ተሠርቷል ብሎ ለመናገር አያስደፍርም፡፡ በርካታ ሀገራት ትንሽዬ ታሪካቸውን አግዝፈውና አተልቀው የብሔራዊ ኩራታቸው ምንጭ፣ የአንድነታቸው ምልክት እና የቱሪስት መስህብ ሲያደረጉት እኛ ግን ታሪኮቻችንን፣ ቅርሳችንን የውዝግብና የግጭት መንሥዔ ከማድረግ ባለፈ የአንድነታችን ምልክት፣ የብሔራዊ ኩራታችን ምንጭ እና የቱሪስት መስህብ በማድረግ ረገድ እምብዛም አልተሳካልንም፡፡

ስለሆነም አዲስ አበባ ‘የአፍሪካ መዲና’ የሚለው ስያሜዋ በይበልጥ ትርጉም የሚሰጥ እንዲሆን ከተፈለገም እንደ ዐድዋ ያሉ የአፍሪካዊነት ወይም የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ተጋድሎ ኩራት የሆኑ ድንበር ተሻጋሪ ታሪካዊ ቅርሶቻችን ሌሎችም አፍሪካውያን ወንድሞቻችን በኩራት እንዲጋሯቸው ለማድረግ ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ በዚህ ረገድም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ዕውን ለማድረግ ያሰበው የዐድዋ ማእከል የመላው አፍሪካና የጥቁር ሕዝቦችን የነጻነት ተጋድሎ ታሪክ የሚዘክር እንዲሆን በብርቱ ሊታሰብበት ይገባል፡፡

ይህም ብቻ አይደለም አፍሪካውያን የነጻት ተጋድሎ የታሪክ ቅርስ፣ ክብር እና ኩራት የሆነው የዐድዋ ድል - በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽም መታሰቢያ ሊኖረው ይገባል፡፡ በኢትዮጵያውያን የረጅም ዘመን ነጻነት ወኔና ብርታት ሆኗቸው ዘረኛውን የአፓርታይድ ሥርዓትን ከሕዝባቸው ጫንቃ ላይ ለማውረድ በጽኑ ለታገሉት ለጀግናው ማንዴላ/ለማዲባ በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ መታሰቢያ እንዲሆንላቸው የወሠኑ የአፍሪካ አገራትና መሪዎች፣ እንዴት ለአፍሪካ አገራትና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ተጋድሎ ትልቅ ወኔንና መነሳሳት የፈጠረው ዐድዋ- በኅብረቱ አዳራሽ ቋሚ መታሰቢያ ወይም መዘክር እንዴት ሊነፈገው፣ ሊነፍጉት ቻሉ?! የእኛ ዝምታ ወይንስ…?! ይህንን ጥያቄ አጥብቀን፣ አብዝተን ልንጠይቅ ይገባናል እላለሁ፡፡

ስለሆነም መንግሥት፣ ነጻነቱን የሚያፈቅር፣ የሚያከብር ኢትዮጵያዊ ኹሉ እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ በታሪክ፣ በቅርስ፣ በባህልና በቱሪዝም ዘርፍ ላይ የሚሠሩና የተሰማሩ አካላትና ምሁራንም የበኩላቸው ጥረት በማድረግ ዐድዋን የመላው አፍሪካ፣ የጥቁር ሕዝቦችና ነጻነታቸውን የሚያፈቅሩ ሕዝቦች ኹሉ የነጻነት ዓምባና የቱሪስት መዳረሻ በማድረግ ረገድ የተቀናጀ ሥራ ለመሥራት ከመቼውም በላይ ጊዜው አሁን ይመስለኛል፡፡ የዐድዋ ማእክልም በዚህ የቁጭት መንፈስ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ፣ አፍሪካውያንና መላው ጥቁር ሕዝብ ታሪክ ክብርና ኩራት ሆኖ ሊገነባ ይገባዋል!!

በተጨማሪም ዓድዋ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ተጀምሮ የነበረውም እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባውም ለማንሳት እወዳለሁ፡፡ በመጨረሻም በዓድዋ ጀግኖቻችን መንፈስና ወኔ፣ ብርታትና ጽናት በዚህ ትውልድ የተጀመረው ጉዞ ዐድዋ አድማሱን አስፍቶ ሌሎች አፍሪካውያን ወንድሞቻችን እና ነጻነታቸው የሚከብሩ የሰው ልጆች ሁሉ በነጻነት ኩራትና ስሜት የሚሳተፉበት ጉዞ ሆኖ እንዲቀጥል በመንግሥትም ሆነ በእኛ ዘንድ ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ጽሑፌን የደቡብ አፍሪካ ቀድሞ ፕሬዚደንት ታቦ እምቤኪ በአንድ ወቅት ስለ ዐድዋ በተናገሩት አባባል ልደመድመው ወደድኹ፤ ‘‘Adowa Victory Made Africa a Victor, not a Victim!’’

ክብር ለዛሬ ነፃነት ላበቁን ለዐድዋ ጀግኖች አባቶቻችን እና እናቶቻችን ሁሉ!

Back to Front Page