Back to Front Page

ቋሚና ግልፅ ማንነት የቱ ነው?

ቋሚና ግልፅ ማንነት የቱ ነው?

ዮሃንስ አበራ (ዶር) 6-2-19

ፍረጃ ወይንም በኢንግሊዝኛ ታክሶኖሚ ትክክለኛ ያልሆነ ሳይንስ ነው። ትክክለኛ ሳይንስ የሚባለው አንድና አንድ ስንደምር ሁለት መምጣቱ የሚያረርጋግጥልን ነው። በርግጥ ማህበራዊ ሳይንስ በምንለው አንድና አንድ ሶስት ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ አለ፣ ሳይንሱን የሚመራው ስሜትና አመለካከት ስለሆነ። በፍረጃ ወይንም ታክሶኖሚ የእንስሳትና እፀዋትን አይነት እየለየን በምድብ ስንከፋፍል ትልቅ ፈተና የሚሆንብን የእንስሳትና የእፀዋት አይነቶች የሚያመሳስሏቸውም የሚያለያይዋቸውም ባህርያት ስላሉዋቸው ነው። ስለዚህ በተለያዩ ምድቦች ለመመደብ በአንድ በተወሰነ ደረጃ ላይ ባለ ምድብ ምን ያህል ተመሳሳይነት እንደሚወስዱና ምን ያህል ልዩነት እንደሚያስተናግዱ ለመሰን እጅግ ፈታኝ ነው።  እፀዋትና እንሰሳትን ለየብቻ በ"ኪንግደም" ለመመደብ ቀላል የሚሆነው ልዩነታቸው በጣም ብዙና ግልፅ በመሆኑ፣ የሚያመሳስላቸውም አነስተኛና ጉልህ ያልሆነ በመሆኑ ነው። የምደባው ፈተና እየተወሳሰበ የሚሄደው ከዚህ ወደታች ባሉ ምድቦች ነው። አጋዘንንና ነብርን ለመለየት ቀለል ያለ ቢሆንም የነብር ዘሮች ለይቶ ይህ ታይገር ነው፣ ይህ አነር ነው፣ ይህ አቦ ሸማኔ ነው፣ ይህ ጃጓር ነው ብሎ ለመለየት ከተመሳሳይነታቸው መብዛትና ከልዩነቶቻቸው ማነስ የተነሳ ቀርቦ የመመርመር ስራ ያስፈልጋል። የባክቴርያ አይነቶችን የመለየለቱ ስራ የተራቀቀ ቴክኖሎጂ ካልተጠቀምን የሚሳካ አደለም። ተፈጥሮ እርስ በርስ የተወሳሰበች ስለሆነ ድንበር የሚባለው የሰው ልጅ ማህበራዊ ፅንሰሃሳብ እንጂ ተፈጥሯዊ አይደለም።

በስነህይወት ሳይንስ የሰው ልጅ ከእንስሳት ኪንግደም የተመደበ ቢሆንም፣ በየደረጃ ምድቡ ወርዶ ውርዶ በመጨረሻው ምድብ ላይ ለብቻው "ሆሞ ሳፕየንስ ሳፕየንስ" ተብሎ ተመድቧል። ይህ ምድብ የሰው ልጆች 95 ከመቶ ዘረመላቸው (ዲ. ኤን. ኤ) አንድ አይነት ነው በሚለው የጄኔቲክስ ምርምር ውጤት ላይ የተመሰረተ ነው። ይህ ማለት የሰው ልጅ 95 ከመቶ ዘሩ አንድ ነው። የዘር ልዩነት እያልን የሰማይ ስባሪ የምናሳክለው ልዩነት ቀሪው አምስት ከመቶው ብቻ የያዘውን ነው። ይህ አምስት ከመቶ የተመደበው ቀላል ለሆኑት የቆዳ ቀለም፣ የፀጉር ልስላሴ ወይንም መከርደድ፣ ለከንፈርና አፍንጫ መጠንና ቅርፅ፣ ለቁመትና አጠቃላይ የሰውነት አቋም ነው።

Videos From Around The World

የባህል የሃይማኖትና የቋንቋ ልዩነቶች እትብት ከተቆረጠ በኋላ ከቤተሰብና ህብረተሰብ የምንቀበላቸው ስለሆኑ ለነሱ የተመደበ ዘረመል የለም።  የትውልድ ቦታም ቢሆን ሰውን ለያይቶ ለመመደብ የሚያበቃ ተፈጥሯዊ መመዘኛ አይደለም። እኔ ሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ ስፈጠር ሁለት የልጅ ልጆቼ ሰሜን አሜሪካ ውስጥ ተፈጠሩ። ሰው የተፈጠረበት ቦታ ዘሩን የሚወስን ከሆነ እነዚ ውድ የልጅ ልጆቼ የኔ ዘር አይደሉም ወደሚል ዘግናኝ ድምዳሜ ያደርሰናል። አንድ ሰሞን በቴሌቪዥን "መርጠህ ነው የተወለድከው?" ይባልና "እኔ መርጬ አልተወለድኩም" የሚል መልስ በመስጠት ከሚገባው በላይና በሌለ መመዘኛ የምንለጥጠውን ዘር ልዩነት ዋጋ ቢስነት ለማሳየት የተሞከረው ሙከራ የሚደነቅ ነው።  ለቆዳ ቀለም ከተመደበችው አንድ ከመቶ እንኳ ለማትሞላው የዘረመል ልዩነት ሲደረግ የነበረውና አሁንም ያለው አድልዎና ግፍ የሚያመለክተው የሰው ልጅ ምን ያህል ልዩነትን የማግዘፍ አባዜ የተጠናወተው የእንስሳ ዘር እንደሆነ ነው። ይህ አባባሌ ሃይማኖትን ሊነካ አይገባም። የሰው ልጅ የአዳም እንጂ የእንስሳ ዘር አለመሆኑ አምናለሁ። ችግሩ የተማረ ሰው ሁለት ምላስ ስላለው ነው፦ አንዱ የሃይማኖት አንዱ የሳይንስ።

ለሃይማኖት ልዩነት የተሰጠ የዘረመል "ነጥብ" የለም። ሰው ወደ የተወሰነ ሃይማኖት እምነት የሚከተል ቤተሰብ ወይንም ህብረተሰብ ይወለዳል እንጂ ፅንስ ላይ እንደ ጉበትና ኩላሊት ሆኖ የሚፈጠር ሃይማኖት የለም። ካደገ በኋላ ሃይማኖትን መቀየር የተለመደ ነው። ዘር ተወርሶ ከርዳዳ ሆኖ የተፈጠረውን ፀጉር ከተወለዱ በኋላ ላዛ ለማድረግ የሚቻለው የህንድ ኮረዶችን ፀጉር ገዝቶ ከከርዳዳው ላይ በመቀጠል ብቻ ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ የ"ዘር" ልዩነትና የሚያስከትለው ውዝግብ ብዙ ክፍለ ዘመናት ያስቆጠረ ቢሆንም እንዳለፉት 50 አመታት፣ በተለይም እንዳለንበት ሦስት አመታት የገነነበት ወቅት የለም። በአሁኑ ጊዜ የምንተነፍሰው አየርም ሳይቀር እሱ ሳይሆን አይቀርም። ለመግቢያ ያህል ህብረተሰቡ በተለምዶ የሚጠቀምበትን ቃል ተጠቀምኩ እንጂ ቀደም ብየ እንደገለፅኩት ኢትዮጵያ ውስጥ የዘር ልዩነት የለም። ያለው የቀለምና የቁመና ልዩነትም እንኳንና ለጥል፣ ለድብድብና ለመገዳደል ለመኮራረፍም አያበቃም። በርግጥ በአመዛኙ ልዩነት የሚታየው የጄኔቲክ ሳይንስ ባላካተታቸው ሰው ሰራሽ በሆኑ ልዩነቶች ነው። ሰው ስራሽ ልዩነቶቹ በሃብት ልዩነት፣ በባህል ልዩነት፣ በቋንቋ ልዩነት፣ በራስ ወይንም በወላጆች የትውልድ አካባቢ ልዩነት፣ በባህል ልዩነት፣ በታሪክ ተጋሪነት ልዩነት፣ እንዲሁም በሃይማኖት ልዩነት ሊሆኑ ይችላሉ።

እነዚህን ሰው ሰራሽ ልዩነቶች ባንዴ አንዱን ብቻ በመውሰድ እንደ የምድብ መመዘኛ ካልተጠቀምንባቸው በስተቀር ከአንድ በላይ ስንወስድ የድንበር ችግር እንደሚያጋጥም ግልፅ ነው። እንኳንና የተውሳሰበው የሰው ልጅ ማህበረሰብ ቀርቶ በደመነፍስ ከሚኖረው ከእንስሳትና እፀዋት አለምም ምድባ ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ ቀደም ብየ ገልጫለሁ። ለምሳሌ ሃይማኖትን እንደ አንድ መመዘኛ ወስደን ግለሰቦችን ብንመድብ ሙስሊምና ክርስትያን ብለን ልንከፍላቸው እንችላለን። ይህ ቀላል ስራ ነው ምክንያቱም ሙስሊሞች የነብዩ መሃመድ ክርስትያኖች ደግሞ የእየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ናቸው። ድንበሩ በግልፅ የተሰመረ ነው። በርግጥ የሚጋሯቸው ነብያትና አስተምህሮዎች እንዳሉ አይካድም።  ሙስሊሞች ሱኒና ሺዓ ክርስትያኖችም ፕሮቴስታንት ካቶሊክ ኦርቶዶክስ የሚል የአስተምህሮ ልዩነት አላቸው። እነዚህ ልዩነቶች ግን ድንበሩን የማደብዘዝ አቅም የላቸውም። ክርስትያኖች አንድ መፅሃፍ ቅዱስ ሙስሊሞች አንድ ቁርአን አላቸው። መከራችን የሚባዛው ከሃይማኖት ላይ ሌላ የምድብ መመዘኛ ስንጨምርበት ነው። ለምሳሌ ከሃይማኖት ላይ ቋንቋን ብንጨምርበት ምደባችን ተደራራቢና ድንበር አልባ ይሆናል። ሙስሊም ትግርንኛ፣ ክርስትያን ትግርኛ፤ ሙስሊም ኦሮሚኛ ፣ ክርስትያን ኦሮሚኛ፣ ሙስሊም አማርኛ፣ ክርስትያን አማርኛ፤ ወዘተ እያለ ይቀጥላል። ወደ ዝርዝር ከተገባም ኦርቶዶክስ ትግርኛ፣ ፕሮቴስታንት ትግርኛ እያሉ መመደብ ይቻላል። ይህ ግን ማንነትን ለመወሰንና ለዛ ምድብ ታማኝነትን ለማረጋገጥ አስቸጋሪ ነው። እንበል ክርስትያኖችንና ሙስሊሞችን የሚያጋጭ ነገር ቢከሰት አማርኛ ተናጋሪ ሙስሊምና ትግርኛ ተናጋሪ ሙስሊም፣ አማርኛ ተናጋሪ ክርስትያንና ትግርኛ ክርስትያን አንድ ወገን ይሆናሉ ወይስ ድንበራቸው በቋንቋ ተለይቶ የአማርኛ ሙስሊምና ትግርኛ ሙስሊም አይደጋገፉም?

የመኖሪያ ወይንም የትውልድ የአስተዳደር ክልል ብንወስድና ከቋንቋና ከባህል ጋር ብናገናኘው የማንነት አመዳደብ ላይ የሚሆነውን እንይ። የተለያየ ቋንቋ ያላቸው ለምሳሌ ኦሮሚኛ ተናጋሪ ሸዋና ወለጋ፣ ትግርኛ ተናጋሪ ትግራይ ውስጥ፣ አማርኛ ተናጋሪ አማራ ውስጥ ያለው ባህልና የአኗኗር ዘይቤ ግልፅ ልዩነት ማየት ይቸግራል። የሰላሌን ኦሮሚኛ ተናጋሪና የቡልጋን አማርኛ ተናጋሪን ህዝብ በየቋንቋቸው ሲናገሩ ካልሰማናቸው በሁለት የተለያየ የማንነት ምድብ ለመለየት ከባድ ነው። ይህ ለሱማሌና ለአፋርም ይሰራል፤ ለጎንደርና ለትግራይም ይሆናል። በባህልና አኗኗር ዘይቤ የአማራ ራያና የትግራይ ራያ ለመለየት ከቶ እንዴት ይቻላል በየቋንቋቸው መናገር እስካልጀመሩ ድረስ። የወልቃይትም ቢሆን እንደዚሁ ነው። ያም የኔ ያም የኔ የሚላቸው የማንነት መመዘኛዎቹ የቋንቋ፣ የባህል፣ የአስተዳደር ክልል ባለቤትነት የታሪክ ውዝግብ ለየብቻቸው ካልሆኑ ከተዋሃዱም ስለሚጠላለፉ ለትክክለኛ ድንበር ማበጃነት አይጠቅሙም። ለየብቻ ቢወሰዱም  የመመዘኛዎቹ መደራረብ ስለሚፈጠር የኔ ልክ ነው የሚል ውዝግብ ከመፍጠር የተለየ እርባና የለውም። መመዘኛዎቹ ለማንነት መለያና ለቡድን ታማኝነት ማረጋገጫ ጥቅም ላይ ሲውሉ እንደሁኔታውና እንደታሪክ አጋጣሚው ሊለያዩ ይችላሉ።

በአንዱ ዘመን ሃይማኖት ልዩነት ለምንነት ምድብ ወሳኝ ሲሆን የቋንቋና የትውልድ አካባቢ ልዩነት ዋጋ ሊያጣ ይችላል። በግራኝ ዘመን ክርስትያኑ በቋንቋና በትውልድ ቦታ ሳይለያይ በግራኝ የተመሩ ቋንቋና ትውልድ ቦታ ካልለዩት ሙስሊሞች ጋር ተዋግተዋል።  ይህ ማለት በቋንቋ ወይም በትውልድ ቦታ አንድ የሆኑ ግን በሃይማኖት የተለያዩት ተዋግተዋል ማለት ነው።  ሃይማኖትን ለማንነት መመደቢያ ወሳኝ መመዘኛ በማድረግ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች ቋንቋ፣ የትውልድ ክልልና ባህል ሳያግዳቸው፣ አክሱም ፅዮንን ለመሳለም የትግራይ ህዝብ እንግዳ ሆነው ይሰነብታሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የሃይማኖትና የባህል ልዩነት ሳይኖር  በቋንቋ ልዩነት ብቻ በልዩነት የተመዳደቡት ጎንደርና ትግራይ ለመተናነቅ አሰፍስፈው ከረሙ። ስለዚህ አንድ ዘር የሆኑት የሰው ልጆች ማህበራዊ ህይወት በፈጠራቸው መመዘኛዎች የማንነት ምድባቸውን ለመወሰን ሲጥሩ በአንድ ሳይሆን በብዙ የሚደራረቡ የሚጋጩ የማንነት ምድቦች ውስጥ ሆነው ራሳቸውን ያገኙታል።

በንጉሱና በደርግ ዘመን የማንነት ምድብ በቋንቋ ሳይሆን በሃይማኖትም ሳይሆን በወንዝ ሸለቆዎች ከማእከል ለአስተዳደር አመቺነትና በመሳፍንቱና መኳንንቱም የግል ግዛታቸው አድርገው ባካለልዋቸው ጠቅላይ ግዛቶች ወይም ክፍላተ ሃገር በሚባሉ የአስተዳደር አሃዶች ነበር። አንተ ማነህ ሲሉት እኔ በጌምድሬ ነኝ፣ ስሜነኛ ነኝ፣ ትግሬ ነኝ፣ ወሎየ ነኝ፣ ወለጌ ነኝ፣ እጆሌ ባሌ፣ ጎጃሜ ነኝ ይል ነበር። ከዛ ወረድ ያለ ሆኖ ግን ከትልቁ የከረረ ማንነትም ነበረ። እኔ ዳሞቴ ነኝ፣ እጆሌ ሰላሌ፣ እኔ የሃረር ልጅ ነኝ፣ እኔ የአድዋ ልጅ ነኝ፣ እኔ እንደርታ ነኝ ሲል ማንነቱ አንድ ክፍለሃገር ውስጥ ካለው "ሌላ" ህዝብም የተለየ እንደሆነ ያስባል። ይህ ማንነት እስከ ድብድብና ጦርነት ሲያዳርስ የኖረ ነው። ይህ ማንነት ግን ከህዝቡ የመነጨ ሳይሆን መንግስት ስሎ በሰጠው ካርታ ላይ ተመስርቶ በተገነባ መመዘኛ ነው። ይህ የሚያመለክተው ሰው የማንነት ቡድኑ በተለያዩ ጊዜያትና ሁኔታዎች ጎልተው በሚገኙ ተለዋዋጭ መመኛዎች ላይ የሚወሰን መሆኑ ነው።

መንግስት አስምሮ በሰጠው የአስተዳደር ድንበር መሰረት አድርጎ ማንነትን መገንባት በኢህአዲግ ዘመንም በተለየ ሁኔታ ቀጠለ። መመዘኛ የፈጠረው ህገ መንግስቱ ነው። በቅድሚያ የማንነት ማእቀፎች ሃይማኖት ሳይሆን፣ የትውልድ ስፍራ ሳይሆን፣ ባህል ሳይሆን ቋንቋ ብቻ ሆነ። በአንድ በኩል መመዘኛው ቋንቋ ሆኖ እያለና የህዝቡ ቁጥር ይነስም ይብዛም እኩል የአስተዳደር ደረጃ መስጠት ሲገባ መለያው ህዝብ ብዛት ይሁን፣ ስሜት ይሁን፣ የእድገት ደረጃ ይሁን፣ ግልፅ ያልተደረገ ብሄር ፣ ብሄረሰብና ህዝብ የሚል ምድብ ተፈጠረ። ይህ ምድብ የህገ መንግስቱ የመግቢያ አረፍተነገርም ሆኖ ተፅፏል፦ "እኛ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች" ይላል። በማንነት አከላለል ላይ ግን ይህ ባለሶስት ፈርጅ ማንነት በምን ሁኔታ ተግባር ላይ እንደዋለ አይታወቅም። ክልል የሆኑት ብሄሮች፣ ዞን የሆኑት ብሄረሰቦች፣ ልዩ ወረዳ የሆኑት ህዝቦች ናቸው እንዳይባል በመመዘኛዎቹ ላይ የተዛነፈ ነገር አለ። ሃረር ከተማ ክልል የሆነው ከሌላው (አማራ የሚበዛበት) ኗሪ ቁጥራቸው ያነሱትን ሃራሪዎች መሰረት በማድረግ ነው። ብሄርና ክልል ከተገናኙ በምን ሌላ መመዘኛ ነው ለዚህ አናሳ ህዝብ የብሄር ደረጃ የተሰጠው? ብሄረሰብና ዞን ከተገናኙስ በምን ሂሳብ ነው ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ ማህበራዊ አደረጃጀት ያለው፣ የከፍተኛ አስተዳደር ክልልነት ደረጃ ይዞ 70 አመት ያህል የቆየው፣ በታሪኩም የበሰለ መንግስታዊ ስርአት የነበረው፣ የህዝቡ ብዛትም ከጋምቤላ፣ ከአፋር፣ ከቤኒሻንጉልና ከሃረሪ ክልሎች የሚልቀው ሲዳማ ብሄር ሆኖ የክልል ደረጃ ያላገኘው?

ብሄር፣ ብሄረሰብና ህዝብ የተባሉት የማንነት ምድቦች ምንጫቸው ከሶሻሊስት መርሆ መሆኑ ይታወቃል። የሚለያዩትም በማህበረ-ኢኮኖሚ ወይንም 'የስርአተ-ማህበር' እድገት ደረጃቸው ነው። ብሄር (ኔሽን) የሚባለው ካፒታሊዝም ከፍተኛ እድገት ደረጃ ደርሶ የገበያ ኢኮኖሚ የብሄረሰብ ደረጃ ያላቸውና በከፊል ፊዩዳልና ከፊል ካፒታሊስት የሆኑትን ብዛት ያላቸው ማንነቶች አጥሮቻቸው ፈርሶ ስፋት ያለውና የዳበረ ማህበረሰብ ሲፈጠር ነው ይላል። ይህ እነ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ኢጣልያ፣ ስፓኝ፣ ወዘተ ብሄር ደረጃ ላይ የደረሱበትን ሁኔታ ያመለክታል። በኢትዮጵያ 'ዘብሄረ ቡልጋ'፣ 'ዘብሄረ ዘጌ' እያሉ ሲፅፉ የነበሩት ከዚህ ትንተና ውጪ ያለ ባህላዊ አባባል ነው። ምናልባትም ኔሽን የሚለው ቃል ከባህላችን አኳያ ብሄር በሚለው ቃል መተርጎሙ ትክክል አልሆነ ይሆናል። ብሄራዊ ትያትር፣ ብሄራዊ መዝሙር፣ ብሄራዊ ኮሚቴ ሲባል ባመዛኙ አገር አቀፍ ለማለት ስንጠቀምበት ከክልል ብሄርነት ጋር እየተምታታ መሆኑ እሙን ነው። ባህርዳር እያለሁ አንዱ የስራ ባልደረባየ ከክልሉ ያመጣውን ደብዳቤ ሳነብ 'ብሄራዊ ኮሚቴ ተቋቁሟል' ይላል። አገር አቀፍ ኮሚቴ እንዴት እዚህ ተቋቁመ ብየ ስጠይቅ የክልል ማለት የአማራ ማለት መሆኑ ተነገረኝ። ከዛ ቀኝ ጀምሮ የየትኛው እንደሆነ ሳልጠይቅ ብሄራዊ የሚለውን ቃል አላሳልፍም።

የደርግ ሶሻሊስት ካድሬዎች ማንነት በብሄረሰብ ብቻ እንዲወሰን አደረጉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ካፒታሊዝም በበቂ ሁኔታ ባለማደጉ በብሄር ደረጃ የሚመደብ የለም የሚል ክርክር ነበራቸው። በንጉሳዊው ዘመን ከጠቅላይ ግዛትና አውራጃ ጎን ለጎን የነበረው አንዱ  የማንነት ምደባ 'ጎሳ' የሚል ነበር። ብሄርህ ውይንም ብሄረሰብህ ሳይሆን የምን ጎሳ ነህ ተብሎ ሲጠየቅ ነበር። በሶሻሊስት ደርግ ዘመነ መንግስት 'ጎሳ' የሚለው የማንነት መግለጫ ክብረነክ ነው በሚል ስለተወሰደ ማንም እንዳይጠቀምበት ተደርጓል። ለዚህም ነው በዝቅተኛ ማህበረ-ኢኮኖሚ ደረጃ ያሉትን ጎሳ (ትራይብ) ብሎ ከመጥራት ደርግም ኢህአዲግም የተቆጠቡት። ደርግ የማህበረ- ኢኮኖሚ ደረጃ ሳይለይ ሁሉንም "'ብሄረሰቦች' ሲላቸው ኢህአዲግ ግን ደረጃ ለመለየት 'ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች' የሚል የማንነት ምድብ አወጣ። 'ህዝቦች' የሚለው የማንነት ምድብ ስያሜ ህዝብ ያልሆነ አለ ወይ የሚል ጥያቄ ያስከትላል። ኢህአዲግ ከደርግ በተለየ ብሄር የሚለውን ማንነት ለምን እንደተጠቀመበት ግልፅ አይደለም። የደርግ ካድሬዎች የሰጡትን ትንተና የሚያሸንፍ አዲስ ነገር አልመጣም። ደርግ ሲወርድ ካፒታሊዝም ድንገት አድጎ ብሄሮችን ፈጥሮ እንደሆነ ሁሉም አይቶታል። ከሰማንያ ሃምሳ ስድስቱ የተለያየ የማህበረ-ኢኮኖሚ እድገት ደረጃ ያላቸው ማንነቶች አንድ ላይ 'የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች' ተብለው አንድ ክልል ሲሆኑ የምንነት መለያ ድንበሩ በዘፈቀደ የመሆኑ ባህርያዊነት ማረጋገጫ ነው። የበለጠ የሚያረጋግጠውም አሁን ሁሉም እየተነሳ ክልል እንሁን እያለ የብሄር የማነት ደረጃ ለማግኘት የሚያደርገው ትግል ነው።

በኢትዮጵያ የግለሰቦችን ማንነት የሚወስነው ማነው፣ የሚወሰነውስ በምን መነሻ ነው? ወደሚባለው የጥያቄ መልስ ትንተና እናምራ። ማንነት መንግስት ይሰጣል፣ ሌሎች ግለሰቦች ይሰጣሉ፣ ሰውም ለራሱ ማንነትን ይሰጣል። በመንግስት የሚሰጠው ማንነት ለማንነት ባወጣው መመዘኛ መሠረት ነው። ባሁኒቷ አትዮጵያ የማንነት መመዘኛ ቋንቋ በሆነበት ትግርኛ ተናጋሪ ትግራዋይ፣ አፋን ኦሮሞ ተናጋሪ ኦሮሞ፣ አማርኛ ተናጋሪ አማራ መሆኑ ነው። እዚህ ላይ በርካታ ውስብስብ ጉዳዮች ማንሳት አስፈላጊ ነው።

እንደኛ/ ግለሰቡ ራሱ ቋንቋውን መናገሩ በቂ ይሆናል? የሚናገረው ቋንቋ ሁለተኛ ሶስተኛ ቋንቋው ቢሆንም ማንነቱን ያስገኝለታል? ወይንስ አባቱና እናቱም የቋንቋው ተናጋሪዎች መሆን አለባቸው? የወላጆችስ ስንት ትውልድ ወደኋላ መራቅ አለበት? እስከ አያት ነው? ቅድመ አያት ነው? በትግራይም፣ በሲዳማም፣ በኦሮሚያም ከሌላ አካባቢ ሄደው ልጆችና የልጅ ልጆች የወለዱ ቋንቋውን የለመዱ በምን የማንነት ምድብ ይመደባሉ? የሚለው ጥያቄ ተገቢ መልስ ሳያገኝ ለግለሰቦች ግብታዊ የማንነት ምደባ የተተወ ጉዳይ ሆኗል። ለዚህም ነው "ኦሮሞ አይደለህም፣ አማራ አይደለህም ስለዚህ ወደ አገርህ ሂድ" እየተባለ የሚባረረውና የሚገደለው የማንነት መመዘኛው ተጨባጭ ባለመሆኑ ግለሰቦች በህዝብ ስም የግል ስሜታቸው ማንፀባረቂያ ስለሚያደርጉት ነው። መንግስትም "እባካችሁ ተዋቸው ይኑሩበት፣ ርህራሄ ይኑራችሁ" ወይንም "ህገመንግስታዊ መብታቸው ነው" ብሎ ከመማፀን ያለፈ በዳዮችን የሚቀጣበት አቅምና ፍላጎትም የለውም። በጉጂ የኖሩ ጌዴዎች፣ በመተከልና ኦሮሚያ የኖሩ አማሮች፣ በጎንደር የኖሩ ትግራዮች የተፈፀመባቸው ድርጊት እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል።

ሁለተኛ/ ማንነት የሚወሰነው በአባት ወይስ በእናት ወይስ በሁለቱ? በሁለቱም ከሆነ የተለያየ ማንነት ካላቸው የተወለደ ሰው ማንነት የለውም እንደማለት ነው። ማንነት ከሌለውም መኖሪያ የለውም ማለት ነው። በአባት ብቻ ከሆነ እናትህ ኦሮሞ ብትሆንም ኦሮሞ አይደለህም ይባላል። በናት ብቻ ከሆነ ደግሞ ኦሮሞ አባት የወለደው ልጅ ኦሮሞ አይሆንም።  ይህ ያሳሰባቸው ሰዎች ናቸው መሰል አንድ ሰሞን "ቅይጥ ብሄረሰብ ፓርቲ" በሚል የተደራጁ ነበሩ። (አይዴንቲቲ ክራይሲስ)።  በግለሰብ እንጂ በቡድን ማንነት የማያስቡት እንደነ አሜሪካ ባሉ ህብረተሰቦች ይህ አይነት ጭንቀት የተለመደ አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ብሄር ከሌለህ ሰው እንዳልሆክ ትቆጠራለህ።

ማንነትን ለመወሰን በተለያየ ጊዜ በተካሄዱ የህዝብ ቆጠራዎች ላይ የተለያዩ ጥያቄዎች ተጠይቀዋል። አንዱ ላይ ከቤት የሚነገረው ቋንቋ ሲባል አዲስ አበባ ሁሉም አማራ ሆነ! በሌላ ጊዜ ደግሞ የናት ቋንቋ ሲባል የማንነት አሃዝ ሌላ ሆነ። አዲስ አበባ ተውልዶ አማርኛ የሚናገረው ሰው ትግራይ ሆና ትግርኛ በምትናገረው እናቱ ስም ተመዝግቦ ማንነቱ ትግራይ ይባላል። ያሁኑ ግን ከዛም የከፋ ነው። የበፊቶቹ እንኳ ትክክል ባይሆንም መመዘኛው ስለሚነገራቸው በቶሎ መልስ ይሰጣሉ። አሁን ግን የሚጠየቀው ግርር ያለ "ብሄርህ ምንድነው?" የሚል ጥያቄ ነው። መልሱን ሁሉም የሚያውቀውና ካፉ ተንጠልጥሎ የሚገኝ ይመስላቸዋል ጠያቂዎቹ። ብሄር ምን ማለት እንደሆነ ማወቅ እንኳን ለተራው ሰው ለተማረውም አስቸጋሪ ነው። ሰው ብሄርህ ምንድነው ሲባልም ብሄር ነኝ ብሄረሰብ ወይስ ህዝብ ብሎ ለመለየት ጭምርም ይቸገራል። በተለይ በዚህ ጉዳይ የተቸገሩት ለስራም ለኑሮም ከትውልድ ቦታቸው ርቀው ሌላ ክልል ሄደው ወልደው ያሳደጓቸው ልጆች ብሄራችሁ ምንድነው ሲባሉ የሚመልሱት መልስ እየጠፋቸው መሆኑ ነው። ጎንደርና ባህርዳር ከትግራይ ወላጆች የተገኙ ልጆች ብሄራቸው ሲጠየቁ አማራ ነን እንደሚሉና መዝጋቢዎቹ የወላጆቻቸውን ትውልድ ሲረዱ ብሄር ቀይረው እንደሚፅፋባቸውና ጭንቀት ውስጥ እንደሚከቷቸው እናውቃለን። በኦሮሚያ ግን ከሌላ አካባቢ የሄዱ ወላጆች ልጆቻቸውን በአማርኛ እንጂ ኦሮሚኛ እየተናገሩ እንዳያድጉ በማድረጋቸው ብሄር ሲጠየቁ ኦሮሞ ነኝ በማለት የጓደኞቻቸውን ማንነት መውሰዳቸው የተለመደ አይደለም። በደቡብም እንደዚሁ። ትግራይ ውስጥ ከአማራም ከኦሮሞም ወላጆች ያሏቸው የትግራይ ማንነት የመውሰዳቸው አጋጣሚ በጣም ሰፊ ነው።

መንግስት ባሰመረው ድንበር ማንነትን መወሰን ጎጃሜ ነኝ፣ ጎንደሬ ነኝ ሲባል የነበረው ማንነት አማራ ነኝ ወደሚለውና ከፍተኛ የፓለቲካ ሃይል ለመሆን በበቃው አዲስ ማንነት ተተክቷል። እንዲያውም ጎንደርም ሸዋም ለየብቻቸው ሆነው የፈፀሙት ታሪክ ሁሉ አንድ ላይ የአማራ ማንነት ይዘው እንደፈፀሙት እየተደረገ ታሪክ ተስተካክሎ እየተፃፈና እየተነገረ ይገኛል። "እኛ አማሮች ለ1000 አመት ኢትዮጵያን አስተዳድረናል" ሲባል አባባሉ እውነትነት ቢኖረውም አንድ ክልል ሆነው አንድ ንጉስ ሹመው ያከናወኑት እንደሆነ ማስመሰሉ ግን ታሪክን ማዛባት ነው።  ሸዋ ሲገዛ ጎንደርና ጎጃም ሲዋጋው፣ ጎንደር ሲገዛ ሌሎቹ ሊነጥቁት ሲሞክሩ፣ ጎጃም በሸዋ ላይ ሲያምፅ ጦር እንደሚላክበት በታሪክ መዛግብት ሰፍሯል።

አሁን በአዲሱ ካርታ መሠረት ኦሮሚያ ክልል በመፈጠሩ ከዚህ በፊት ወለጋ፣ ሸዋ፣ አርሲ፣ ሃረር ብለው ራሳቸውን የሚመድቡ ሁሉ አዲስ ካርታ አዲስ ማንነት ፈጥረዋል፦ "ኦሮሞ ነኝ የሚል"። ከዚህም የተነሳ ሃረር ላይ ያለ ኦሮሞ አጠገቡ ካለው ጉራጌ ይልቅ ወገን ያደረገው አምቦ ያለውን ኦሮሞን ነው። በተቃራኒው በአዲሱ የኢትዮጵያ ካርታ መሠረት ራሱን "እኔ ደቡብ ነኝ" የሚል በርካታ ቢሆንም አብዛኛው ግን የበፊት የማንነት ምድቡን እንደያዘ ነው። የክልል ጥያቄ ደቡብ ላይ የበረታውም ክልሉን እንደማንነት የተቀበለው ህዝብ ብዙ ስላልሆነ ነው። ትግራይ፣ ወሎና ሸዋ ነኝ ሲል የነበረው አሁን አፋር ሆኗል። በርግጥ አብዛኛው ህዝብ የቀድሞ የአውራጃና የጠቅላይ ግዛት/ክፍለሃገር ማንነቱን አልተወም። ውስጥ ለውስጥ አንዳንዴም በይፋ ሲንፀባረቅና የፓለቲካና የኢኮኖሚ ግድድር ይደረግበታል። ኦሮሞ ነኝ ቢባልም ወለጋው ለወለጋ፣ አርሲው ለአርሲ የማድላቱ ነገር የአደባባይ ምስጢር ነው። በአማራውም በትግራይም እንዲሁ። አዲሱ ካርታ ያመጣው ማንነት የበፊቱን ማንነት ሳያጠፋ በሱ ላይ በመደረቡ ነገሮችን አወሳስቧል። በትግራይ ማንነት ስር ያለውና የላቀ ጉልበት ያለው አድዋነት፣ እንደርታነት፣ ራያነት፣ ተንቤንነት ከላይ ያለው ማንነት ሳይገታው ውዝግብ የመፍጠር አቅም አለው። በአማራ ክልል የስልጣን ሽሚያ ላይ የድሮ ጠቅላይ ግዛት/ክፍለሃገር የነበሩት ያሁን ዞኖች ያላቸው ሚና ቀላል አይደለም። የድሮ የጠቅላይ ግዛት/ክፍለሃገር ደረጃ ማንነትና የአሁኑ የክልል ማንነት ተደራርበው በመገኘታቸው እንደየ አመቺነቱ እያፈራረቁ የሚመዘዙ መሳርያዎች ሆነዋል። በአዲሱ ካርታ ወልቃይትና ራያ የትግራይ ማንነት እንዲይዙ ይጠበቃል። አማራ ክልል የእነዚህ አካባቢዎች ማንነት አማራ እንጂ ትግራይ አይደለም ይላል። አማራ ክልል እየጠየቀ ያለው ራሱ የተፈጠረበትና ቋንቋ መመዘኛ ያደረገውን የማንነት አከላለል ሽሮ ነው። መመዘኛው ከተሻረ አማራ ክልል ወደ አራት ክፍላተሃገር ይከፈላል እንደበፊቱ። ትግራይም ወልቃይትንና ራያን ማስረከብ ካለበት የሚያስረክበው ለቀድሞዎቹ ወሎና ጎንደር እንጂ ለአማራ ክልል አይሆንም። አማራ ክልል ከቤኒሻንጉል በኩል ያለው ጥያቄ ትክክል ነው ከተባለ በጎጃምነት እንጂ በአማራነት የሚጠየቅ ሊሆን አይችልም። ኢትዮጵያ ውስጥ የመንግስትን ወይንም የየአካባቢው ገዢዎች የአስተዳደር አከላለል በተቀየረ ቁጥር የማንነት አመዳደብም አብሮ ሲቀየር ኖሯል።

ሦስትኛ/ ሌላው እንደሚመድባቸው ብቻ ሳይሆን ሰዎች የኔ ማንነት ነው ብለው የሚያምኑበት አመለካከትም አላቸው። ይህ የግል ምደባ ከመንግስት ወይንም ከሌላ ግለሰብ ወይንም ቡድን ከሚሰጥ ምደባ አንዳንድ ጊዜ ሲመሳሰሉ አንዳንዴም ይለያያሉ። ለምሳሌ መንግስት አማራ ነህ ብሎ ያካለለው ወይንም ሌላ ግለሰብ አማራ ነህ ብሎ የመደበው ሰው ራሱን እንደ ኦሮሞ ወይንም ትግራይ አድርጎ ሊቆጥር ይችላል። ትግራይ ነህ የተባለውም እንዲሁ። ግለሰብ ለራሱ የሚሰጠው ማንነት አንድ ቋሚ ማንነት ሳይሆን እንደየሁኔታው የሚቀየር ማንነት ነው። ይህ ሰው የሰው ዘር ከመሆኑ ውጪ ያለው የማንነት ልዩነት ድንበሩ ቋሚ እንዳልሆነ ይህ ጉልህ ማረጋገጫ ነው። እኔ ማንነቴ ኢትዮጵያዊነቴ ነው ይልና ሌላው ኢትዮጵያዊ ማንነቱን ባለማስቀደሙ ሲኮንንና በከሃዲነት ሲከስ የቆየው ሁሉ አሁን ይህ ማንነት የፓለቲካ ፋይዳው ዜሮ መሆኑን በመመልከት ወይንም እያስጠቃኝ ነው በሚል ስሜት ኢትዮጵያዊ ማንነቱን አራግፎ አማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ወዘተ የሆነው ቁጥር ስፍር የለውም። በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያዊነት ነው የኔ ግንባር ቀደም ማንነት የሚል ሰው እንደዋልያ ቁጥሩ እየተመናመነ ነው። አብዛኛው ህዝብ ቋሚና ግልፅ ድንበር ያለውን ኢትዮጵያዊ ማንነት እየተወ በየጊዜው የሚቀያየረውና ግልፅ ያልሆነ ድንበር ያላቸውን ማንነቶችን እየወሰደ ሲፋጭና ሲጋጭ ይገኛል። በርግጠኝነት መናገር የሚቻለው አሁን ሌላ አዲስ አከላለል መንግስት በድፍረት ቢያውጅ ህዝቡ የበፊቶቹ ሳይጠፉ በአዲሱ ካርታ ማንነቱን እንደሚወስን ነው። ለዚህ ነው መንግስት ያመጣው ማንነት ለሃገሪቱ አደጋ ከሆነ መንግስት ራሱ መቀየር ያለበት። ማንነቱ ተፈጥሯዊ ሳይሆን ሰው ሰራሽ በመሆኑ በመቀየሩ የሰው አጥንት አይፈለጥም አንጀት አይቆረጥም።

የማንነት ጥናት ሊቃውንት እንደሚሉት ግለሰብ ማንነቱን በራሱ የሚወስን ሲሆን የሚሆነው ምደባዊ (ካቴጎሪካል) ሳይሆን መስተጋብራዊ (ትራንዝአክሽናል) በሆነ መንገድ ነው። ምደባዊ የተባለው አንድ ሰው ጎንደሬ ነኝ ካለ በየትኛውም ሁኔታ በየትኛውም ስፍራ ጎንደሬ ነኝ ይላል። ልክ እንደ ሰሌዳ የተለጠፈበት ይሆናል ማለት ነው። መስተጋብራዊ ከሆነ ግን ማንነቱን የሚገልፀው አንዳለበት አገርና እንዳጋጠመው ሰው ማንነት ነው። ለምሳሌ ተስፋየ አሜሪካ ውስጥ ከላቲን አሜሪካ ከመጣ ሰውጋ ከተገናኘና ማንነቱን ከጠየቀው መልሱ "እኔ አፍሪካዊ ነኝ" የሚል ይሆናል። ካይሮ ላይ ከጋና ከመጣ ሰው ጋር ተገናኝቶ ማንነቱ ከተጠየቀ መልሱ መቸም አማራ ነኝ አይሆንም። ተስፋየ የሚለው "እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ" ነው። ተስፋየ ኢትዮጵያ ተመልሶ አዲስ አበባ ወይንም ሃዋሳ ላይ ከጋምቤላ ከመጣው ኦጁሉ ጋር ቢገናኝና ማንነቱን ቢጠይቀው ጎንደሬ ነኝ ሳይሆን "እኔ አማራ ነኝ"  ብሎ ይመልስለታል። እስካሁን ሶስት ማንነቶች አይተናል፣ እንቀጥል። ተስፋየ ባህር ዳር ሄዶ ከሌላ አማራ ጋር ሲገናኝ ለማንነቱ ጥያቄ የሚሰጠው መልስ አማራ ነኝ ሳይሆን "እኔ ጎንደሬ ነኝ" ነው። ተስፋየ ወደ አምስተኛው ማንነት ለመድረስ ጎንደር ከተማ መገኘት አለበት። ጎንደር ላይ ወገሬው ማነህ ብሎ ከጠየቀው "እኔ የኮራሁ ፋርጤ ነኝ" ይላል። እዚህ ላይ ይቁም እንጂ ወደ ታች የመውረድ እድልም አለ። ብዙ ሰዎች ማንነትና የሚያስከትለው ግጭት ወረዳ ድረስ ወርዷል እያሉ ነው። ይህ ድንበር አልባና የዘፈቀደ ማንነት የኢኮኖሚና የፓለቲካ ጥቅም የሚያስገኝላቸው ግለሰቦች ወይንም ቡድኖች እስካሉ ድረስ ቀበሌም ድረስ ሊያደርሱት ይችላሉ። መስተጋብራዊ የሆነው ማንነት ሊቃውንቱ ልክ እንደ ቀይ ሽንኩርት አድርገው ይወስዱታል። ከላይ ያለውን ስንልጠው ሌላ አለ፤ እንዲህ እያለ እስከመጨረሻዋ ድረስ ይላጣል።

ከዚህ በላይ የተተነተነው ቋሚና ግልፅ የሆነ ድንበር የሌለውና በየጊዜውና በየሁኔታው ሊቀያየር የሚችለው ማንነት ነው። ኢትዮጵያዊ ማንነት ቋሚና ግልፅ ድንበር አለው የምለው ኢትዮጵያዊነት ተፈጥሯዊ በመሆኑ አይደለም። ኢትዮጵያዊነትን ተፈጥሯዊ እንደሆነ ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶች አሉ። ኢትዮጵያን እግዚአብሄር በልዩ የፈጠራት እንደሆነች ከመስበክ ጀምሮ "ነብር ዥጉርጉርነቱን፣ ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊነቱን አይተውም" እስከማለት ይደረሳል። ኢትዮጵያዊ ማንነት ቋሚና ግልፅ ድንበር አለው የምለው በአለም ካርታ ላይ የሰፈረች፣ በዚህ ማንነቷ የተባበሩት መንግስታት ያወቃትና ያፀደቃት፣ ከጎረቤት አገሮች የሚለያት ግልፅ ድንበር ያላት አገር ስለሆነች ነው። ማን ኢትዮጵያዊ እንደሆነና ማንስ ኬንያዊ ማንነት እንዳለው የሚወሰነው እንዲሁ እንደዘመኑና እንደመስተጋብሩ እየተቀያየረ ሳይሆን ከድንበሩ ወዲህና ወድያ መገኘት ያለምንም መደበላለቅ ኢትዮጵያዊነትንና ኬንያዊነትን ያረጋግጣል። በርግጥ በአገር ደረጃ ያለ ማንነት የሚቀየርበት አጋጣሚ የለም ማለት አይደለም። ኢትዮጵያዊ የነበሩት ኤሪትርያዊ ሆነው፣ መልሰው ኢትዮጵያዊ ሆነው፣ እንደገና ኤሪትርያዊ ሆነዋል። እንዲህ አይነት ክስተቶች አልፎ አልፎ የሚፈጠሩ እንጂ ባህርያዊ አይደሉም። በዚህ ዘመን የአገራት ድንበር በአለም አቀፍ ህግጋት የተከበረ ስለሆነ በዚህ ዙሪያ የተገነባ ማንነት በተነፃፃሪ ዘላቂነት አለው።

በዋቢ ፅሁፎች የተደገፈው ተመሳሳይ ትንተና በ1987 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሶስዮሎጂ ትምህርት ክፍል ያሳተምኩት "Sociology and Ethnographic Bulletin" ላይ ያንብቡ። ርእሱ፦ "Ethnicity and ethnic groups፡ a literature review".

 

Back to Front Page