Back to Front Page

ጠ/ሚ ዶ/ር አብዪ አሕመድ የበሉበት ድስት የሰበሩ ዕለት የሚከተለው መዘዝ ብዙ ነው

ጠ/ሚ ዶ/ር አብዪ አሕመድ የበሉበት ድስት የሰበሩ ዕለት የሚከተለው መዘዝ ብዙ ነው

(ለተከበሩ የአገራችን ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አሕመድ እና ቡድናቸው የተላከ አንገብጋቢ መልእክት)

***********************

የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አብይ አሕመድ፤ ሰሞኑ በማሕበራዊ ሚድያ እየተወሩ ካሉ በጣም በጣም አደገኛ እና አውዳሚ ተንኮሎች ምክንያት በማድረግ ይህን ጠ/ሚ ዶ/ር አብዪ አሕመድ የበሉበት ድስት የሰበሩ ዕለት የሚከተለው መዘዝ ብዙ ነው የሚል ርእስ ያለው መልእክት ስፅፍሎት ሀሳቦ ዳግም ይፈትሹታል ከሚል ተስፋ በመነሳት ነው፡፡ ማንኛውም ዜጋ የመሰለውን ሀሳብ የመግለፅ ህገመንግስታዊ መብት ተጠቅሜ በአገራዊ ሁኔታ መልእክት በመፃፌ ዜግነታዊ ግዴታዮን የመወጣት ስሜት ይሰማኛል፡፡

በአሁኑ ጊዜ የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አሕመድ የምርጫ ጊዜ እንዲራዘም፣ ከጥቂት ተቋዋሚ ሀይሎች ድብቅ ሴራ እያሴሩ እንደሆነ አፈትልከው ከወጡ መረጃዎች መረዳት ችያሎህ፡፡ የመንግስት ሚድያዎች የምርጫ ጊዜ ለማራዘም ከሚያቀርቡዋቸው ምክንያቶች ውስጥ የዝግጅት እና የባጀት ምክንያቶች ሲሆኑም ሲዘረዘሩም ዘመናዊና በቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ ግልፅነት እና ተጠያቂነት ባለው እንዲካሄድ ካስፈለገ፣ የቴክኖሎጂ ግዢዎች፣ የምርጫ መዋቅር እስከ ታች ማቋቋም፣ የህትመት ስራዎች እና መዋቅሩ ማሰልጠን ማብቃት እንዲሁም፣ በሚልዮኖች የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው መመለስ፣ ለዚህ የሚሆን ከፍተኛ ባጀት /ካለፈው ባጀት በ5-6 ዕጥፍ/ መመደብ የሚሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ነገሮች ደግሞ በአንድ ዓመት ተጠቃልለው የሚልቁ ስላልሆኑ ምርጫው መራዘም አለበት ይላሉ፡፡

የተከበሩ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አሕመድ

ስለምርጫ ጉዳይ ሲታሰብ ከዴሞክራሲና ነፃነት፣ ከአገር አንድነት እና እኩልነት፣ ከህዝብ ብልፅግናና ዕድገት ተጣምሮ ካልታየ ብዙ ትርጉም አይሰጥም፡፡

Videos From Around The World

እኔ ለዚች አገር አንድነትዋን፣ ሰላምዋን፣ ልማትዋን እና በአጠቃላይ የህዳሴ ጉዞዋን ማስቀጠል የሚችል ብቸኛው መንገድ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንገድ ነው የሚል ዕምነት አለኝ፡፡ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ፤ መስመሩን የሚቀበል ህዝብ እና መስመሩን መርቶ ለድል የሚያበቃ አገራዊ መሪ ድርጅት መኖር አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይሁን እና አሁን ተጨባጭ የአገራችን ሁኔታ ስገመግመው፤

ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር የሚቀበል ህዝብ በተመለከተ፡-

ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር በተጨባጭ መሬት ላይ በመውረዱ በርካታ የአገራችን ህዝቦች ኑሯቸውን የተቀየረ፣ ድህነት በአገራችን ባለፉት 28 ዓመታት ከግማሽ በላይ የቀነሰበት፣ የኢኮኖሚ ዕድገታችን ላለፉት 17 ዓመታት ድርብ አሀዝ ያደገበት እንደሆነና በርካታ የአለምአቀፍ ተቋማት የመሰከሩበት እንደሆነ ሁሉም የሚያየው የሰማው ጉዳይ ነው፡፡ ስለሆነም ይህን የሚቀበል ቀምሶ ያጣጣመ ህዝብ መኖሩ ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ የለኝም፡፡ ስለዚህ አፍን ሞልቶ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር የሚቀበል ህዝብ አለ ለማት እደፍራሎ፡፡

ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር መርቶ ለድል የሚያበቃ አገራዊ መሪ ድርጅት መኖር በተመለከተ፡-

ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር የሚከተል ብቸኛው የአገራችን ድርጅት ኢህአዴግ ነው የነበረው፡፡ በዚህም ጊዜ ባለፉት 28 ዓመታት በአጠቃላይ ስኬታማ ጉዞ ተጉዟል ቢባልም ባለፉት የቅርብ 4-5 ዓመታት ግን የመበስበስ አደጋ አጋጥሞት እንደ ወትሮው ከዚህ የዝቕጠት እና የመበስበስ አዘቅት ራሱን ማዳን ስላልቻለ፣ ኢህአዴግ የሚል ስም ይዞ ውስጡ ግን ኢህአዴግ ያልሆነ አገራዊ ግንባር ይዘን እንገኛለን፡፡ በ11ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ አዴፓ መስመሩ መቀየር አለበት ብሎ ይዞ እንደመጣ እና መጠናት አለበት ተብሎ በአብላጫ እንደተወሰነ በሚድያ ሰምተናል፡፡ ከዛ ቀጥሎ በተለይ ከአዴፓ የሚናፈሱ ፕሮፖጋንዳዎች ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ እንደከሰረ የሚገልፁ ናቸው፡፡ ከዚህ መረዳት የሚቻለው አሁን ኢህአዴግ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መመስመር ማራመድ ይቅር አራቱ እህት ድርጅቶች መደማመጥና መቻቻል ብሎም መግባባት የማይችሉበት ደረጃ ደርሰዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ስለዚ በአሁኑ ሰዓት ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር መርቶ ለድል የሚያበቃ አገራዊ ድርጅት የለም ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል፡፡

በክልል በኩል ሲታይ በትግራይ ክልል ህወሓት እና የተግራይ ህዝብ 99.99% ለማለት እደፍራሎህ በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንገድ መተማመን ተፈጥሯል፡፡ በሌሎች ክልሎች ግን አፉን ሞልቶ ስለ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር የሚናገር ፖለቲካዊ ድርጅት የሚናገር አለ ወይም የለም ለማለት አያስደፍርም፡፡

ስለዚ ስለ ምርጫ መራዘም እና አለመራዘም ህገመንግስቱ በሚፈቅደም መሰረት ቢራዘም ባይራዘም እንደ ትልቅ ነገር አልወስደውም፤ ብቻ ህገመንግስቱ መሰረት ያደረገ ይሁን ባይ ነኝ፡፡ ለምን ቢባል እንደ አንድ አብዮታዊ ዴሞክራት ወይም እንደ አንድ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚያምን ዜጋ የ2012 አገራዊ ምርጫ ቢራዘምም ባይራዘምም በዚህ ምርጫ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚከተል ብቸኛው ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ድርጅት ህወሓት ብቻ በመሆኑ፣ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር በሚቀጥሉት 5 ዓመታት አገራዊ መስመር ሆኖ እንደማይቀጥል የታወቀ ነው፡፡ ህወሓት በትግራይ ክልል ቢያሸንፍም በአገራዊ ሁኔታ ግን እንደ አጋር ሆኖ ነው የሚቀጥለው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ስለዚህ ይህ ምርጫ ቢራዘምም ባይራዘምም ለህወሓት እና ለትግራይ ህዝብ ብሎም ለኢትዮጵያ ህዝብ ምንም ትርጉም የለውም፡፡ መራዘሙና አለመራዘሙ ትርጉም የሚሰጠው ግን ከህወሓት ውጭ ላሉ ወይም ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንገድ ለማይቀበሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ትርጉም አለዉ፡፡ እነዚህ ድርጅቶች እርስ በርሳቸው ለመፎካከር መራዘም ወይም አለመራዘም ትርጉም አለው፡፡ ስለዚ የምርጫው መራዘም ወይም አለመራዘም ጉዳይ የአንዱን ፍላጎት ወይም የሌላውን ፍላጎት ለማሟላት አልሞ ሳይሆን ሕገመንግስቱን በሚፈቅደው መሰረት ቢፈፀም በጣም ተገቢነት አለው የሚል እምነት አለኝ፡፡

የተከበሩ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አሕመድ

በማህበራዊ ሚድያ የሚሰራጩ መረጃዎቹ እንደሚያሳዩት ግን የምርጫ ጊዜ መራዘም ምክንያት እላይ የተጠቀሱት ሳይሆን፤ ጠቅላይ ሚንስትር ከጥቂት ተቋዋሚዎች ጋር በመመሳጠር ሕገመንግስቱን ቀዳድዶ በምትኩ ጊዝያዊ ቻርተር እንዲኖር ለማድረግ በቂ ዝግጅት ለማድረግ ነው የሚል ነው፡፡ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ሕገመንግስቱ ባስቀመጠው አሰራር በስልጣን ላይ ተቀምጦ ሕገመንግስቱን መቅደድ ማለት ምግብ የበላበት ድስት ወይም ሰሃን እንደ መስበር ማለት ነው፣ መዘዙም በጣም አውዳሚ ነው የሚሆነው፡፡

ሕገ መንግስታችን የአብሮነታችን፣ የአንድነታችን፣ የመከባበራችን የኢትዮጵያዊነታችን ያስተሳሰረን ገመድ ነው፣ በአሁኑ ሰዓት ህገመንግስት ማፍረስ ማለት በአገር ላይ የተጠመደ ቦምብ ማፈንዳት ማለት ነው፡፡ ህገመንግስት እስካለ ድረስ ሁሉም የህግ የበላይነት አክብሮ መሄድ የግድ ነው፡፡ የተከበሩ ጠ/ሚ በአሁኑ ሰዓት እያራመዱት ያለ ነገር /የመደመር ፍልስፍና/ ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች ያመኑበት እና የተቀበሉት ነው ማለት ኣይቻልም፡፡ ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች ሊቀበሉት ይቅር፤ ጠ/ሚኒስትሩና ቡዱናቸው የመጡባቸው ክልሎችም ሳይቀር ስላልተቀበለው ሰላም እና መረጋጋት የታጣባቸው ቀንደኛ ክልሎች ሆኖዋል፡፡ ከዚህ መረዳት የሚቻለው አሁን በስልጣን ላይ ያለው ቡድን፣ አንድ ክልል እንደ ክልል፣ አንድ ህዝብ እንደ ህዝብ የሚደግፈው እና የሚቀበለው አመራር ነው ማለት አይቻልም፡፡

ግን ደግሞ በስልጣን ላይ ያለው ቡድን ህገመንግስቱ ባስቀመጠው መንገድ መጥቶ ስልጣን ስለያዘ ለቡድኑ ከፍተኛ ተቃውሞ አለው የሚባለው የትግራይ ክልል ወይም ደግሞ የትግራይ ህዝብም ቢሆን ለቡድኑ ታላቅ አክብሮት አለው፡፡ ሕገመንግስት መሰረት አድርጎ የሚሰጠው አመራርም ምንም ሳያቅማማም ይቀበለዋል፡፡ ምክንያቱ ሕገመንግስቱን እስከተከበረ ድረስ ያለውን ልዩነት ኣቻችሎ፣ ተቀብሎ የመኖር ግዴታ ሕገመንግስቱ ስለጣለብን ነው፡፡ የህግ የበላይነት፣ ሕገመንግስታዊነት የሚባለው እንዲህ ነው፡፡

የተከበሩ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አሕመድ

ማንም ከፍተኛ ባለስልጣን ጠ/ሚ ጨምሮ፣ ሕገ መንግስት ጥሶ አመራር መስጠት ግን አይችልም፡፡ አገር መምራት ይቅር አንድ እርምጃም መራመድ አይችልም፡፡ ሕገመንግስት ተጣሰ ማለት በቃ ጠቅላይ ሚንስትር እንደ ማንኛውም ተራ ሰው ሆነ ማለት ነው፡፡ ሕገመንግስት ተቀዳደደ ማለት ጠ/ሚ በማንኛውም የአገር ወይም የህዝብ ጉዳይ እንደ ማንኛውም ዜጋ አስተያየት ከመስጠት ውጭ አመራር መስጠት አይችልም ማለት ነው፡፡ አንድ ሻምበል/ሻለቃ ሙሉ አጃቢ ሊኖረው ቀርቶ አንድም ወታደር ሊጠብቀው አይችልም፡፡ ጠቕላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አሕመድ ሕገመንግስቱ የጣሱና የቀዳደዱ ዕለት ጠ/ሚኒስተርነትም አብሮ ተቀዳደደ ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ጠ/ሚሩ በቃ በቤተሰብ-ህግ ቤተሰባቸው ብቻ ነው መምራት የሚችሉት፡፡ ይህ ህገመንግስት በከፍተኛ የህዝቦች መስዋእትነት የተገኘ፣ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በህዝቦች ተሳትፎ የፀደቀ እንደመሆኑ መጠን በአንድ ግለሰብ ወይም በአንድ ቡድን /ለምሳሌ ኦሮማራ/ በጀብደኝነት ሊፈርስ/ሊቀዳደድ አይችልም፡፡

ሕገመንግስቱ የተቀደደ ዕለት ኢትዮጵያ የምትባል አገር አትኖርም፣ የውጭ ጣልቃ ገብነት በሩ ተበርግዶ ይከፈታል፣ ጠ/ሚ ማንንም የመንግስት መዋቅር መምራት አይችልም፤ መምራት አልቻለም ማለት ደግሞ 9 ክልሎች የየራሳቸው መንግስት ይዞ በየመንገዳቸው ይሄዳሉ ማለት ነው፡፡ እያንዳንዱ ክልሎች ከፈለጉት የውጭ መንግስት ግንኝነት ይፈጥራሉ ማለት ነው፡፡ እያንዳንዱ ክልል የየክልላቸው የፀጥታ ሁኔታ ለመጠበቅ ሲባል ያልተመጣጠነ ሀይል ይኖራቸዋል ብሎም በድንበር እና በወሰን ሰበብ ወደ ግጭት ይገባሉ ማለት ነው፡፡ ትግራይ ክልል በወልቃይት እና በራያ ከአማራ ክልል ጋር ይጋጫል፤ አማራ ክልል ከአፋር ከኦሮሚያ፣ ከቤንሻንጉል ክልሎች በተመሳሳይ ምክንያት ወደ ግጭት ይገባል፣ ኦሮሚያ ክልል ከሶማሌ፣ ከአፋር፣ ከደቡብ ክልሎች፣ ጋምቤላ ክልል፣ ከደቡብ እና ከቤንሻንጉል ክልሎች በአጠቃላይ ያየምንፈራም አርማጌዶን ይከሰታል ማለት ነው፡፡

ሕገመንግስቱ ከሌለ የሚያዝዝ ጠ/ሚ የለም፤ የሚታዘዝ መከላከያ የለም፣ የሚታዘዝ ደህንነት የለም፣ የሚታዘዝ የመንግስት መዋቅር የለም፣ የሚታዘዝ የህዝብ ሃብት አይኖርም ማለት ነው፡፡ ምክንያቱ እነዚህ የህዝብ እና የመንግስት ተቋማት የቆሙት፣ የሚተዳደሩት፣ የሚያዝዙትም የሚታዘዙት በህገመንግስቱ ብቻ በመሆኑ፡፡

የተከበሩ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አሕመድ

እርስዎ ምንም እንኳ ለአገራችን መሪ ለመሆን በህፃንነትዎ ትንቢት ስለተነገርዎና ትንቢትዎ ለመተግበር ከፍተኛ ተጋድሎ ያደረጉ ጠ/ሚ ቢሆኑም፣ እንደ አጼ ሀ/ስላሴ ስዩመ እግዚኣብሄር አይደሉም፣ ኢትዮጵያን ለመምራይ በመለኮታዊ ሀይል አይደለም የመጡት፡፡ እርስዎ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አሕመድ ወደ ስልጣን የመጡት በሕገመንግስቱ መሰረት ባስቀመጠው አሰራር ሕገመንግስቱን ኣክብረው እና ተከትለው ነው ስልጣን ላይ የተቀመጡ፡፡ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አሕመድ ወደ ስልጣን የመጡት በሕገመንግስቱ መሰረት በኢህአዴግ ምክርቤት 108 ለ 59 ድምፅ አሸንፈው ነው፡፡ ስለዚህ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አሕመድ የበሉበት ሰሀን ይሰብራሉ ወይም ሕገመንግስቱ ይቀዳድዳሉ የሚል አስተያየት ምክንያታዊ ሊሆን አይችልም፡፡ ጠ/ሚ ሕገመንግስቱን ቀዳድደው ጣሉት ማለት ስልጣናቸውም ጭምር ቀዳድደው ጣሉት፣ ኢትዮጵያም በዘጠኝ ሰነጣጥቀው በታተንዋት ማለት ስለሆነ፡፡ ሴራው እውነት እርስዎ እውን ካደረጉት የኢትዮጵያ ዕጣፈንታ በጎበዝ አለቃ መመራት ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ኢትዮጵያ ልክ እንደ ሶማሊያ በ1980ዎች የነበረ የእርስ በርስ ዕልቂት ታስተናግዳለች ማለት ነው፡፡

የተከበሩ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አሕመድ

ህገመንግስት መቀየር አለበት የሚል እምነት እንኳ ቢኖርዎት፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ብቻ ሲሆን አገራችን አንድነቷን፣ ሰላሟን፣ ልማትዋን አስጠብቃ ትቀጥላለች፡፡ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ማለት ደግሞ ህገመንግስቱ ባስቀመጠው መንገድ ብቻና ብቻ ነው፡፡ ሕገመንግስቱ ያስቀመጠው መንገድ ደግሞ በያንዳንዱ የክልል ምክር ቤት ቢያንስ ከ2/3 በላይ ድምፅ ሲገኝ እና በተወካዮች ምክርቤትም ቢያንስ ከ2/3ኛ ድምፅ በላይ ሲገኝ ብቻ ነው፡፡ ከሁለቱም አንዱ ካልተሟላ በቃ ሕገመንግስቱ ሊቀየር ወይም ሊሻሻል አይችልም፡፡ ለምሳሌ አንድ ክልል እንበል የትግራይ ክልል በሕገመንግስት የማሻሻያ ሃሳቦች ከቀረቡት 5 አንቀፆች ውስጥ 4ቱ ተቀብሎ አንዱ ካልተቀበለው እና ሌሎች ክልሎች 5ቱ ከተቀበሉት 4ቱ ተግባራዊ ሆኖው አንዱ ግን ተግባራዊ ሳይሆን በነባሩ ሕግ ይቀጥላል ማለት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ምናልባት መቀየር የፈለገው አካል ማድረግ የሚችለው ጊዜ ወስዶ ሀሳቡን አንሸራሽሩ በህዝብ ተቀባይነት እንዲኖረው ማድረግ እንጂ ማስገደድ አይችልም፡፡ ከዚህ ውጭ ለመሄድ መሞከር ግን በአገር እና በህዝብ ከፍተኛ ውድመት ማስከተል ማለት ነው፡፡ ከዚህ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ውጭ ለመሄድ ከተሞከረ፣ የትግራይ መንግስትና ህዝብ በሕገመንግስቱ አንቀፅ 39 የመገንጠል መብቱ ያረጋግጣል ማለት ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ወደ ጦርነት ተገባ ማለት ነው፡፡ ስለዚ የኢትዮጵያ ህዝቦች በከፍተኛ መስዋእት ያረጋገጡት ሕገመንግስት ቀዳድዶ መጣል ይቅር እና አንድ አንቀፅም ለመቀየር ሕገመንግስቱ ካስቀመጠው አሰራር ውጭ መሄድ ማለት ከፍተኛ ችግር መፍጠር ማለት እንደሆነ በደንብ እንዲገነዘቡልኝ እፈልጋሎህ፡፡

ስለዚ የተከበሩ የአገራችን ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አብይ አሕመድ፣ እየተከተሉት ያለውን ጠቅላላ ኣካሄድ፤ የሚወዱት እና የሚቀበሉት ዜጎች እንዳሉ ተቀብየ/አውቄ፣ በዛው ልክ እኔ ፀሀፊው ጨምሮ በሚሊዮኖች ዘንድ የሚጠሉት እና የማይቀበሉት እንዳሉ ላረጋግጥሎት እፈልጋሎ፡፡ ነገር ግን በትግርኛ ምእንቲ እዛ መጎጎ ትሕለፍ እዛ አንጭዋ እንደሚባለው ዕሬት ዕሬት ቢለንም ሕገመንግስቱ እስካከበሩ ድረስ፣ ለሕገመንግስቱ ብለን እናከብሮታለን፣ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ብለን እንቀበሎታለን፡፡ ሕገመንግስት የቀዳደዱት ዕለት ግን የኛ ብቻ ሳይሆን የማንም ኢትዮጵያዊ ጠ/ሚ እንዳልሆኑ ማወቅ አለቦት፡፡ ስለዚህ የታሰበው ሴራ እውነት ከሆነ አንዴ ሁሌቴ ብቻ ሳይሆን ሺ ጊዜ ወይም ከዛ በላይ ጊዜ ደጋግመው እንዲያስቡበት እጠይቃለሁ፡፡ ለምንወዳት ኢትዮጵያ አገራችን ሲሉ እንዳይሞክሩትም እማፀኖቷሎህ፡፡

በአሁኑ ሰዓት ህገመንግስት ማፍረስ ማለት በአገር ላይ የተጠመደ ቦምብ ማፈንዳት እና አገርን ብትንትንዋ ማውጣት ማለት ነው!!!

 

ህዳሴ ኢትዮጵያ

ግንቦት 24፣ 2011 ዓ.ም.

አስተያየት በ hidaseethiopia@yahoo.com and/or hidaseethiopiaa@gmail.com ማድረስ ይቻላል

 

 

Back to Front Page