Back to Front Page


Share This Article!
Share
ሂሳብ የማወራረድ (የበቀል) ፖለቲካ!

ሂሳብ የማወራረድ (የበቀል) ፖለቲካ!

መልአከ ሰላም 1-06-19

ባለፉት ሦሥት ዓመታት በመንግስት መልፈስፈስ፣ ለወትሮ በጥንካሬው የምናውቀው ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ መፋዘዝ፣ በአገር ውስጥ እና የውጭ ባለሃብቶች ኢንቨስትመንትን እንዲሁም በማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ምክንያት በአገራችን በተፈጠረው አለመረጋጋት አገራችንን ወደማያባራ ብጥብጥ እንዳያስገባት በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገራት የምንኖር አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሲያስጨንቀን የነበረ ጉዳይ ነው፡፡

ዶክተር አብይ የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ሊቀመንበር እና የአገራችን ጠቅላይ ሚኒስቴር ተብለው በድርጅቱ ከተመረጡ በኃላ አንዣቦ የነበረው የጥፋት ዳመና ለጊዜውም ቢሆን ሲያስተላልፉዋቸው በነበሩ የአንድነት የሰላም እና የፍቅር መልእክቶች ለሦሥት ዓመት ስትናጥ የነበረችው አገር እፎይ ማለት ጀምራ ነበር፡፡ ይሁንና ይኼን የብዙዎቻችን ተስፋ አለምልሞ የነበረው የሰላም አየር ለመደፍረስ ግን ብዙ ጊዜ አልፈጀም፡፡ በአብዛኛው የአገራችን ክልሎች (በተለይ በኦሮምያ፣ በደቡብ ክልል፣ በአማራ እና በሶማሌ ክልሎች) ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝባችን በግጭት ምክንያት ከመኖርያ ቀየው ተፈናቀለ፣ በርካታ ዜጎችም መተኪያ የሌላት ህይወታቸውን አጡ። በአሁኑ ወቅት ወደ 3 ሚልዮን የሚጠጋ ህዝባችን ከቀየው ተፈናቅሏል። ኢትዮጵያ በውስጧ ያሉትን የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን ይዛ እንደ አገር ትቀጥላለች ወይ የሚል ጥያቄ መጠየቅ ከጀመረ ውሎ አድሯል። በየአካባቢው የጎበዝ አለቆች መብዛትና በብዙ አካባቢዎች የመንግስት የአስተዳደር እርከኖች ከጥቅም ውጭ እንዲሆኑ ተደርጓል። አንድ ክልል በሌላው ክልል ላይ በግላጭ ጦርነት ማወጅ ጀምሯል። በፌዴራል መንግስት የሚተዳደሩ አገር አቋራጭ መንገዶች ተዘግተዋል። በአገራችን ታሪክ ላይ መጥፎ ጠባሳ ትተው ያለፉ የደቦ ፍርዶችም ባለፉት ጥቂት ወራት አይተናል። ሌላም ሌላም። እነዚህ ኹነቶች ደምረን ስናይ ባለፉት 27 ዓመታት በጠንካራ ውስጣዊ ሰላም እና በእድገት ጎዳና ስትመራ በነበረችው ኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጽመዋል ብለን ለማመን ይከብዳል።

Videos From Around The World

በሚገርም ሁኔታ ግን እንደነዚህ አይነት ችግሮች ሲፈጠሩ አመራሮቻችን እየተከተሉ ያሉት አካሄድ ችግሮቹን የሚያረግብ ሳይሆን እሳት ላይ ጭድ የመጨመር ያህል ነው፡፡ በየቦታው ለሚፈጠሩ ችግሮች የተጠናና ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ከመሞከር ይልቅ ያረጀ ያፈጀ ፕሮፓጋንዳን በማስቀደም ህዝቡ የተፈናቀለው እና የሞተው በጸረ ሰላም እና ጸረ ለውጥ ሃይሎች ሴራ ነው እየተባለ ነው። በሽታውን የደበቀ መድሃኒት አይገኝለትም እንዲሉ ችግሩ እየተሻሻለ ከመሄድ ይልቅ ከቀን ወደቀን እየተባባሰ በመሄድ ላይ ይገኛል።

እዚህ ላይ የተወሰኑ መሰረታዊ ጥያቄዎችን ማንሳት የግድ ይላል። ጠቅላይ ሚኒስትራችን እና የሚመሩት መንግስት የአገራችንን የውስጠ ሰላም የመደፍረስ ሁኔታ ከቀን ወደቀን እየባሰበት እየሄደ መሆኑ ይገነዘባሉን? ከተገነዘቡስ ሁኔታውን ለማሻሻል ምን እየሰሩ ነው? ለመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ምንድን ነው የሚፈልጉት?

ከላይ እንደተጠቀሰው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ስልጣን በመጡባቸው የመጀመርያ ሁለት ወራት ከውስጥና ከውጭ ጥሩ የሚባል ተቀባይነት አግኝተው ነበር። ከኤርትራ ጋር የነበረውን ቀዝቃዛ ጦርነት እንዲቆም፣ በሁለቱ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ን ሲኖዶሶች መካከል የነበረውን ቅራኔ እንዲታረቅ ማድረጋቸው እንደዚሁም የህዝባችን ግማሽ የሆኑት ሴቶችን ወደ ሃላፊነት ቦታዎች ለማምጣት ባደረጉዋቸው ጥረቶችም ሊመሰገኑ ይገባቸዋል።

የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ በጥር ወር 2010 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ በህዝቡ ሲነሱ የነበሩትን ችግሮች ከመፍታት አኳያ በተለይ በአገራችን ዴሞክራሲን ከማስፋትና ከማጥለቅ አንጻር እስረኞች እንዲፈቱ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ከማስፋት አኳያ በተቃውሞ ጎራ ከተሰለፉት ኃይሎች ጋር በትብብር ለመሥራት የተላለፉት ውሳኔዎችን ተከትሎ የሰረቀውም፣ ሰው የገደለውም፣ በአገር ክህደት የታሰረውንም ጨምሮ በርካታ እስረኞች ተፈቱ። በተቃውሞ ጎራ የነበሩትም በነጻነት ወደ አገራቸው ገብተው በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ በተላለፈው ጥሪ መሰረት በውጭ አገሮች ይኖሩ የነበሩ በርካታ ተቃዋሚ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ወደ አገር ቤት ገቡ። በዚህ ጉዳይ ላይ ወደ ዝርዝር መግባት ባልፈልግም እንደኔ እምነት በእስረኞች አለቃቀቅም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ወደ አገር ቤት እንዲገቡ የተደረገው ህግን በመከተል ሳይሆን በስሜት በመገፋፋት የጨበጣ ሥራ ነው የተሰራው። ውሳኔው የተወሰነው በዋነኝነት ሰላም እና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የነበረ ቢሆንም ምንም አይነት የመጸጸት ስሜት ያላሳየን ሌባ እና የኢትዮጵያ ህዝቦች በአንድነት የመኖር መብትን በግላጭ የሚጋፉ ተቃዋሚ ነን ባዮች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በነጻነት እንዲዘዋወሩ ማድረግ በምን መስፈርት ሰላምና መልካም አስተዳደር እንደሚያሰፍን ግልጽ አልነበረም። በወቅቱ መንግስት የሚሰራቸው ሥራዎች ግልጽነት እንዲኖራቸው፣ የገዢው ፓርቲ ውሳኔ እና የአገሪቱን ህግ መሰረት አድርገው እንዲፈጸሙ የሚያሳስብ መግለጫ እስከማውጣት የደረሰ ክልልም ነበር።

በዚህ መልኩ የተጀመረው ያልተገራ አካሄድ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሥራ አስኪጅ ኢንጅንየር ስመኝ በቀለን እና የዳንጎቴ ሥራ አስኪያጅን ጨምሮ ሰዎች በጠራራ ጸሐይ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ይገደሉ ጀመር። የደቦ ፍርድ፣ ሰዎችን በዱላና በድንጋይ ቀጥቅጦ መግደል፣ ባደባባይ ዘቅዝቆ መስቀልን ጨምሮ ስርዓት አልበኝነት ተስፋፋ። የህገ ወጥ መሳርያዎች ዝውውርም አስደንጋጭ በሆነ መልኩ እየተስፋፋ ነው። ከአዲስ አበባ ወደ ክልሎች እና ከክልሎች ወደ ክልሎች የሚወስዱ ዋና ጎዳናዎች የጸጠታ ሁኔታቸው በጣም አስጊ መሆን ከጀመሩ ውለው አድረዋል። ከደሴ ወደ ትግራይ የሚወስደው የፌዴራል መንገድ ከተዘጋም በርካታ ወራት ተቆጥሯል። ክልሎች ከውስጥ እና ከውጭ በሚነሳባቸው ጫና ምክንያት ከትግራይ በስተቀር እያሰለሰ ግጭት የማይነሳበት ክልል የለም። በድንበር ሳይሆን በአገር ውስጥ ከተሞች እና በገጠር ቀበሌዎች ውስጥ የመከላከያ ሰራዊት በማዝመት የእርስ በርስ ጦርነት እስከመግጠምም ደርሰናል። በኢኮኖሚው ረገድ የአገሮች ለንግድና ኢንቨስትመንት አመቺነት በተመከተ የዓለም ባንክ Doing Business በሚል ለ190 አገሮች በሰጠው ደረጃ አገራችን እ.ኤ.አ. በ2008 ከነበራት የ109ኛ ደረጃ በ2018 ወደ 159ኛ ዝቅ ብላለች። በኮንስትራክሽን እና በሌሎች የንግድ ዘርፎች በአሁኑ ወቅት በአገራችን የሚታየው መቀዛቀዝም በግልጽ የሚታይ ነው። በወታደራዊ ኃይል አገራችን እስከ ቅርብ ጊዜ ከአፍሪካ 2ኛ ወይም 3ኛ ደረጃ ስትይዝ የነበረች ቢሆንም Global Fire Power እ.ኤ.አ. በ2018 ባወጣው የአፍሪካ አገሮች ደረጃ አገራችን ወደ 6ኛ ደረጃ ዝቅ ብላለች። እነዚህ ከፊት ለፊታችን የተጋረጡብን ፈተናዎች የአገር ህልውና የሚፈታተኑ አደጋዎች መሆናቸውን ለማረጋገጥ ጥናት ማጥናት አያስፈልግም። ጠቅላይ ሚኒስትራችን እና መንግስታቸውም እነዚህን እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ በማስገባት የአገራችንን ሁኔታ ከቀን ወደቀን ከድጡ ወደማጡ እየሄደ ስለመሆኑ ይስቱታል ብየ አላስብም።

ጠቅላይ ሚኒስትራችን የአገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ በአግባቡ የሚገነዘቡ ከሆነ ሁኔታውን ለማሻሻል የሚያግዙ ተግባራት ከማከናወን ይልቅ የበቀል በሚመስል የሂሳብ ማወራረድ ፖለቲካ መጠመድን ለምን መረጡ? አንባቢዎች እንደሚያስታውሱት ዶ/ር አብይ ለኢህአዴግ ሊቀመንበርነት በእጩነት ሲቀርቡ ዶ/ር አብይ ለኢህአዴግ ሊቀመንበርነት አይመጥኑም ብለው ከተከራከሩት የምክር ቤቱ አባላት መካከል አብዛኛዎቹ የህወሓት አባላት ነበሩ። ኢህአዴግ በለመደው አሰራር ተከራክሮ ዶ/ር አብይ ከተመረጡ በኃላ ግን ህወሓት የምርጫውን ውጤት በማክበር ሊቀመንበሩን ለመደገፍ የተቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ግልጽ አድርጎ ነበር። በርግጥም መጀመርያ አካባቢ የነበረው መተባበርና መመካከር ይህንኑ የሚያሳይ ነበር። በዚህ ወቅት ህወሓት በፌዴራል ደረጃ የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ እያበረከተ በዋነኝነት ግን በሚያስተዳድረው ክልል ትኩረት በማድረግ እንደሚሰራም አቅጣጫ አስቀመጠ። በኔ እምነት የህወሓት ውሳኔ በሁለት ምክንያት ወቅታዊ ነበር። በመጀመርያ የደርግን ስርዓት ለመጣል የትግራይ ህዝብ ወሳኝ ሚና የተጫወተ ቢሆንም ከአብራኩ የወጡት የህወሓት ታጋዮች ትኩረታቸው በክልሉ ላይ ስላልነበር ከህዝቡ ዘንድ ይነሳ የነበረውን ከፍተኛ ቅሬታ ዘግይቶም ቢሆን ምላሽ ለመስጠት ምቹ ጊዜ ስለነበር ነው። ሁለተኛው ምክንያት በአገራችን የተከሰቱ ችግሮች በህወሓት ምክንያት እንደተከሰቱ ተደርጎ ለ27 ዓመታት ሲቀርብ የነበረው ዘመቻ፣ ከዚህ ጋር በተያያዘም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሥራቸውን በአግባቡ እንዳይወጡ ነባር አመራሮች አደናቅፈውኛል የሚል ክስ ያቀርቡ ስለነበር አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርም ተመሳሳይ ክስ እንዳያቀርቡ፣ የተለየ ነገር ሳይደረግለት ዒላማ ለተደረገው የትግራይ ህዝብ ለመካስ አቅም ያለው የህወሓት አባል ወደ ክልሉ ተመልሶ እንዲሰራ ማድረጉ የግድ ስለነበር ውሳኔው ወቅታዊ ነበር። ሆኖም ግን ዶ/ር አብይ በህወሓት ላይ ዘመቻ ለመክፈት ጊዜ አልፈጀባቸውም። የጠቅላይ ሚኒስትሩን ምርጫ በጸጋ ተቀብሎ ክልሌን አለማለሁ ብሎ የመጫወቻ ሜዳውን ትቶ ለሄደ ፓርቲ እየተከተሉ አላስቆም አላስቀምጥ ማለት ሰላምና መረጋጋትን አሰፍናለሁ ብሎ ለተነሳ ጠቅላይ ሚኒስትር ትክክለኛ ስትራቴጂ ነው ብየ ለመውሰድ ይከብደኛል። በርግጥ ሂሳብ ከማወራረድ አንጻር ከታየ ትክክል ሊሆን ይችላል። ነገር ግን የፖለቲካ ኪሳራው እና በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን ለሚደረገው ጥረት ጋሬጣ እንደሚሆን ግን ጥርጥር የለውም።

በአገራችን የህወሓት የበላይነት ነበር የሚለው መከራከርያ ከተጨባጭ የሥልጣን፣ ኢኮኖሚ እና ፖለቲካ መስፈርቶች አኳያ ሲመዘን ውሃ የማያነሳ ቢሆንም ባለፉት 27 ዓመታት በኢኮኖሚው፣ በጸጥታው እና በወታደራዊው መስክ በአገራችን ለተመዘገቡ ውጤቶች የህወሓት ሚና የላቀ ነበር የሚል እምነት አለኝ። ታድያ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ውጤት ካስመዘገው ድርጅት መተባበር እና መደጋግፍ ሲገባቸው ለምን ወደ ሥም ማጥፋት ዘመቻ ገቡ? ከላይ እንደጠቀስኩት በምርጫው ወቅት የህወሓት አመራሮች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንዳይመረጡ ስለተቃወሙ ብድር ለመመለስ ነው የሚል መከራከርያ ሊቀርብ ይችላል። ይህ መከራከርያ ግን ከኢህአዴግ አሰራር አንጻር አሳማኝ አይሆንም። ምክንያቱም በኢህአዴግ አሰራር ተከራክረህ (አንዳንዴም ተሰዳድበህ) ውሳኔ ከተወሰነ በኃላ የደገፈውም ያልደገፈውም ውሳኔውን ያከብራል። በዶ/ር አብይ ምርጫ የሆነውም ይሃው ነው። ስለሆነም ጠቅላይ ሚኒስትራችን በህወሓትና በትግራይ ላይ ለማነጣጠር ሌሎች ምክንያቶች አሉዋቸው ማለት ነው። የተወሰኑትን እንይ። የመጀመርያው ምክንያት ሊሆን የሚችለው የነበረውን ስርዓትና አስተሳሰብ በመቀየር አዲስ ስርዓት ለመተካት መፈለጋቸው፣ ሁለተኛው በራስ መተማመን አለመኖር፣ ሶስተኛው በህወሓት ላይ ቂም የቋጠሩ የውስጥ እና የውጭ ሃይሎች ግፊት ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህን ጉዳዮች በአጭሩ ፈታ አድርገን እንያቸው።

ፈረንጆች Control the Past to Control the Future የሚል አባባል አላቸው (መጻኢውን ለመቆጣጠር ያለፈውን መቆጣጠር አለብህ እንደማለት)። አገራችን እና መንግስታችን ሲመሩባቸው የነበሩት የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ መርሆች (አብዮታዊ ዴሞክራሲ እና ልማታዊ መንግስት) የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጸሐፊም አሰልጣኝም በመሆን ተግባር ላይ የዋሉ መርሆዎች ነበሩ። ለዚህም ይመስላል በአሁኑ ወቅት በነዚህ መርሆች ሲመሩ የነበሩት የሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች (በተለይ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች) ከህወሓት ውጪ አንዳቸውም ስለነዚህ መርሆዎች ጥብቅና ሲቆሙ አይስተዋሉም። ስለሆም አገራችን ስትመራባቸው ለነበሩት መርሆዎች በዚህ ወቅት ሁነኛ ጠበቃ በመሆን መቆም የሚችል አንድ ድርጅት የትግራዩ ህወሓት ብቻ ነው ማለት ነው። በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኃላ በኢኮኖሚ ዙርያ ካስቀመጡዋቸው አቅጣጫዎች መካከል የልማታዊ መንግስት ዋና ዋና መገለጫዎች ከሆኑት መካከል በአገሪቱ ኢኮኖሚ ወሳኝ ተራ ያላቸው በመንግስት እጅ የሚገኙት የልማት ድርጅቶች ወደ ግል ማዞር እና መንግስት በትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ የሚኖረው ተሳትፎ መቀነስ የሚሉ ናቸው። እነዚህ አካሄዶች በልማታዊ መንግስት ምትክ አማራጭ መርህ ለመከተል የሚያስችሉ መንደርደርያዎች መሆናቸው ማየት ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ኢትዮጵያዊነትን ለመግለጽ ሲጠቀሙባቸው ከነበሩት አገላለጾች መካከል እኔ ኢትዮጵያ ነኝ የሚል ነው። በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ኢትዮጵያዊነት በዋናነት የሚገለጸው በዴሞክራሲያዊ ብሄረተኝነት እንደሆነም ይታወቃል። እዚህ ላይ ሁለት በግልጽ የወጡ ማንነቶች የታያሉ። የመጀመርያው እኔ ኢትዮጵያ ነኝ የሚለው ትኩረቱ ግለሰብ (Individual) ሲሆን በዴሞክራሲያዊ ብሄረተኝነት አስተሳሰብ ደግሞ ቡድን (Group) ላይ ያተኮረ ነው። ጠቅላያችን በቡድን ላይ ያተኮረ አወቃቀራችን ስላልተመቻቸው መዋቅሩ በቡድን ላይ ከተመሰረተች ኢትዮጵያ በግለሰብ ወደ ተመሰረተች ኢትዮጵያ ለመለወጥ ይመስላል። በዚህ ጉዳይ ላይም ከሌሎች መሰል ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ስለ ቡድን መብት የታገለውና አሁንም በተመሳሳይ አቋም በመታገል ላይ የሚገኘው ህወሓት ስለሆነ ጠቅላይ ሚኒስትራችን እነዚህ ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮችን ለማሳካት የጉዳዮቹ ጠበቃ ነው ብለው ለሚያስቡት ህወሓት ዒላማ ማድረጋቸው ምክንያታዊ ናቸው የሚል መከራከርያ ሊነሳ ይችላል።

ሁለተኛው ምክንያት ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሁሉንም አሜን ብሎ እንዲገዛላቸው መፈለግ በአንድ በኩል፣ ይህንን ለማሳካት በአገራችን ያለው ነባራዊ ሁኔታ የማይፈቅድ መሆኑ እንዲሁም ልምድ እና አቅም አለመኖር በሌላ በኩል፣ የነዚህ ድምር ውጤት የሆነው በራስ የመተማመን እጦት ሊሆን ይችላል አልገዛም ባዩ ህወሓት ላይ ጣት የቀሰሩት። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ስልጣን እንደመጡ በርካታ የሥራ ሃላፊዎች እና የፖለቲካ ሹመኞች ከስልጣናቸው ወይም ከሹመታቸው እንዲለቁ ተደርጓል። በሥራቸው ውጤታማ ያልነበሩት እና የፖለቲካ ሹመትን እንደ ርስት አድርገው ይዘውት ለነበሩ ሰዎች እንዲነሱ ማድረጋቸው ደግ አደረጉ። በዚህ ግን አላበቁም። ከፌዴራል አልፈው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና የክልል ካቢኔዎች ምርጫ ላይ ጫና ማድረግ እና ትእዛዝ እስከመስጠትም ደረሱ። በበርካታ ክልሎች በራሳቸው ፈቃድ የሚለቁ አመራሮች ተበራከቱ። በምትካቸውም ተደምረናል የሚሉ ተተኩ። ከክልሎች መካከል በዋናነት ትግራይ፣ በተወሰነ መልኩ ደግሞ አፋር ብቻ ሲቀሩ ሌሎቹ በተደመሩ አመራሮች እንዲመሩ ተደርገዋል። በደህንነት፣ በወታደራዊ እና በሲቪል ጉዳዮች የዳበረ ልምድ ያላቸው፣ በመደመር መርህ ሳይሆን በለመዱት አሰራር የሚጓዙ በመቐለ የተሰበሰቡ የህወሓት አመራሮች እና ነባር አባላት ለጠቅላያችን ስጋት እና በራስ መተማመናቸውን ያጎደሉባቸው ይመስላል።

ሶስተኛው ምክንያት የውስጥ እና የውጭ ሃይሎች ያሳደሩባቸው ጫናዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ከአገር ውስጥ በተለይ በትጥቅ ትግል የወደቀው የደርግ አባላትና ደጋፊዎች፣ ኢትዮጵያን በፌዴራል ሥርዓት በማደራጀት የኢትዮጵያ አንድነት ፕሮጀክት አፍርሶብናል የሚሉ ብዝሃነትን መቀበል ያቃታቸው አካላት፣ ወንጀል በመስራታቸው ምክንያት ከአገር ሸሽተው የነበሩ ወይም ለእስር ተዳርገው የነበሩ አካላት ወዘተ. አሁን በተገኘው አጋጣሚ ከህወሓት ጋር ሂሳብ ለማወራረድ ያለ የሌለ አቅማቸውን በመጠቀም በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው። እነዚህ ሃይሎች ተደምረናል የሚል ዘፈን ስለሚዘፍኑ ብቻ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደጋፊ አድርገው የቆጠሩዋቸው ናቸው። በሌላ በኩል ኢትዮጵያን በእብሪት በመውረር ከድንበራችን አልወጣም ብሎ የነበረው ሻዕቢያ በመላው ኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ ተሸንፎ የተመለሰ ቢሆንም ለሽንፈት የዳረጉኝ የህወሓት አመራሮች ናቸው ብሎ ስለሚያስብ ህወሓትን ከገጸ-ምድር ለሚያጠፋለት ማንኛውም አካል አጥብቆ እንደሚወዳጀው ግልጽ ነው። የፌዴራሊዝም ስርዓት፣ የልማታዊ መንግስት አስተሳሰብ እና ለውጪ ሃይሎች አለመንበርከክ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለተቀሩት የአፍሪካ አገሮችም እንደ መጥፎ አርአያ አድርገው የሚቆጥሩት የቅርብ እና የሩቅ የውጭ ሃይሎች እነዚህን አስተሳሰቦች የሚያቀነቅነውን ሃይል እንዲዳከም ብሎም እንዲጠፋ ፍላጎታቸው እንደሆነም ግልጽ ነው። በመሆኑም እነዚህ አካላት መንገድ ሲዘጉም፣ ዝም፣ እገሌን እሰርልን ሲሉም በማሰር እና አስራለሁ በማለት ማስፈራራት፣ ባጠቃላይ የህወሓት ሃላፊዎች ተረጋግተው ስራቸውን እንዳይሰሩ ሁሌም በሚፈጠርላቸው አጀንዳ ዙርያ ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ፣ እንዲሁም የትግራይ ህዝብም ለወደፊቱ ተመሳሳይ አቋም ያላቸው ልሂቃን እንዳያወጣ አንገቱን እንዲደፋ ለማድረግ እየተሰራ ያለም ይመስላል።

እዚህ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህወሓት ላይ ያተኮሩት ሰርቀው ወይም የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈጽመው የተደበቁ የቀድሞ አመራሮች ፍለጋ እንጂ ከትግራይ ህዝብ ጋር ጉዳይ የላቸውም የሚል መከራከርያ ሲቀርብ ይሰማል። የሰረቀ እና የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈጸመ ማንኛውም ሰው በህግ መጠየቅ አለበት። ነገር ግን ይኼ ጉዳይ በመቐለ ላሉት ሰዎች ብቻ የሚመለከት ተደርጎ መቅረቡ ግን ቅንነት የሚጎድለው መሆኑንነ ማየት ይቻላል። ይቅርታ ከሆነ ለሁሉም ይቅር ማለት። መጠየቅ ይገባቸዋል ከተባለ ደግሞ ያለመድልዎ ሁሉንም መጠየቅ ይገባቸዋል። የቀድሞም ሆኑ አሁን ያሉትም አመራሮች የየድርሻቸውን ሊወስዱ ይገባል። ነገር ግን አሁን የቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊሰሩ የሚገባቸው በርካታ ተግባራት እያሉን አገራችን አሁን ካለችበት ሁኔታ ሊያወጡ በማይችሉ ጉዳዮች ላይ ጊዜ እና ጉልበት ማጥፋት ለምን አስፈለገ? የወጣቶች ሥራ አጥነት፣ በየመንደሩ የምናያቸው ስርዓት አልበኝነት፣ በየቀኑ እየተበተኑ ያሉት ክልሎች፣ አላግባብ እየተፈናቀሉ ያሉት ዜጎች፣ ስለ አጠቃላይ ኢኮኖሚው ወዘተ ላይ አተኩረን ለምን አንሰራም? አቶ ወይም ጄኔራል እገሌ ቢታሰሩ የሳምንት ወሬ ከመሆን አያልፍም። ከዚያስ?

የአገር አንድነትና ህልውና ጥያቄ ውስጥ ሊያስገቡ የሚችሉ ችግሮች እንዳይፈጠሩ፣ ሲፈጠሩም በህግና በስርዓት እንዲፈቱ የሚያስችሉ የተጠናከሩ ተቋማት በሌለባት አገራችን ዘላቂ መፍትሔ ባይሆንም ስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ እና መሪዎቻችን (የፌዴራልም የክልልም) በሰከነ መንፈስ የሁኔታዎች አመጣጥና አካሄድ እየመረመሩ በውይይትና በምክክር መፍትሔ ማስቀመጥ የተለመደ አሰራር ነበር፡፡ ይህ አሰራር የተጠናከሩ ተቋማት እንዳይፈጠሩ የራሱ አሉታዊ ገጽታ ያለው ቢሆንም፣ አገራችን ባለፉት 25 ዓመታት ለነበራት ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም እድገት የማይተካ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡

አሁን በአገራችን እያየነው ያለው ጎራ የለየ የቃላት ጦርነት፣ በህዝቦች መካከል የነበረውን መጠራጠር እንዲያገረሽ እና አገርን ሳይሆን መንደርን ማእከል ባደረገ ፖለቲካ ተጥለቅልቀን ወደምንፈራው መለያየት እንዳይመራን አሁን የተፈጠረው የቃላት ጦርነት ወደ ዘላቂ ሰላም እንዲቀየር ሁሉም መረባረብ ይገባዋል፡፡ ፈረንሳዊው ጄኔራል ፎሽ (FOCH) በእያንዳንዱ ጦርነት ውስጥ ሰላም አለ! ብሎ እንዳለው፣ አሁን የምንሰማቸው የቃላት ጦርነቶች፣ አሁን የምንሰማቸው የሞት ዜናዎች፣ አሁን የምንሰማቸው መፈናቀሎች እና መሰደዶች በውስጣቸው ያለውን የበለጠ መከባበር እና መተማመን እንዲሁም የበለጠ የሰላምና የአንድነት ፍላጎትን እውን ለማድረግ ከማንም በላይ ወሳኝ ተራ መጫወት የሚገባቸው መሪዎቻችን ናቸው፡፡

መሪዎቻችን መርካት የሚገባቸው ዘላቂ ሰላም ሊያረጋግጥ በሚችል ጉዳይ እንጂ ጊዜያዊ ጭብጨባ በሚያስገኙ ጉዳዮች ከቶ መሆን የለበትም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትራችንም የአገሪቱ ቁንጮ ስልጣን የያዙ እንደመሆንዎ መጠን፣ ለአንድነትና ለሰላም የሚያደርጉት ስብከት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ሁሉ፣ አንዱን ደምረው ሌላውን እየቀነሱ አለመሆንዎንም ረጋ ብለው ቢያዩ ለአገራችንም፣ ለእርስዎም ለሚመሩት ህዝብም ወሳኝነት አለው፡፡

የሚያጨበጭብልዎት ሳይሆን እየተሳሳቱ መሆንዎንም የሚያመላክትዎት ሰው በብዛት ከአጠገብዎ ቢያበዙ ለሁላችንም በእጅጉ ይጠቅመናል፡፡ ሻለቃ ቃለክርስቶስ አባይ የ1953 መፈንቅለ መንግስት አስመልክተው በጻፉት መጽሓፋቸው ውስጥ አንድ የዘገቡት ታሪክ አለ፡፡ የአዲስ አበባ ህዝብ መፈንቅለ መንግስት መካሄዱን እንዳወቀ ወደቤተመንግስት አካባቢ በመምጣት አጼ ኃ/ስላሴን በመርገም መፈንቅለ መንግስት አድራጊዎቹን ሲያሞካሽ ይውልና፣ ሁኔታው ከተቀየረ በኃላ አጼውን ሲረግም የነበረ ሰው እንደገና ኃ/ስላሴ ድረስ በነፍሴ እያለ ይዘፍን ነበር ብለዋል፡፡ መሪዎቻችን ልብ ካልገዙ ዛሬ በሰልፍ ሲሰግድ እና ሲያጨበጭብ የነበረ ሰው ነገ ለመሳደብ እና ድንጋይ ለመወርወር በጣም ቅርብ ነው፡፡

ይነስም ይብዛ በፌዴራልም ሆነ በክልል በስልጣን ላይ ያሉ መሪዎቻችን አገራችን በ1983 አዲስ ምዕራፍ እንድትጀምር፣ እስካሁን የተመዘገቡት መልካም ነገሮች እና ባይፈጠሩ የምንላቸው ፍጻሜዎች ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ፣ ይነስም ይብዛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ግልጽ ነው፡፡ ወይም በዚሁ ሥርዓት የተወለዱ ወይም ያደጉና የተማሩ ናቸው፡፡ ኢህአዴግ ደግሞ በርከት ያሉ ችግሮች አጋጥመውት ችግሮቹን በውይይት እና በምክክር እየፈታ የመጣ እና በዚህ ረገድ የካበተ ልምድ ያለው ድርጅት ነው፡፡ አሁን ደርሶ አገርን አደጋ ውስጥ የሚያስገቡ ጉዳዮች እየተፈጸሙ ሁሉም በየጎራው ሆኖ መነታረክ ለማንም አይጠቅምም፡፡

ሰውየው ከቤቱ ሲወጣ ልብስ ደራርቧል፡፡ በዚህ ጊዜ ጸሐይና ንፋስ የሰውየውን ልብስ ማን ያስወልቀው በሚል ይወራረዳሉ፡፡ እናም ንፋስ ጀምር ይባልና፣ ንፋስ ጉልበት እየጨመረ የሰውየውን ልብስ ለማውለቅ ይሞክራል፣ ሰውየው ደግሞ ንፋሱ በበረታ ቁጥር ልብሱን እያጠበቀ ስለሚሄድ ንፋስ ሞክሮ ሞክሮ አልተሳካልኝም ይላል፡፡ ጸሐይ በተራው ይመጣና ቀስ እያለ ሙቀት እየጨመረ ሲሄድ ሰውየው አንድ በአንድ ልብሱን አውልቆ ቁጭ አለ አሉ፡፡ ከፊውዳል ወደ ወታደራዊ መንግስት፣ ከወታደራዊ መንግስት ወደ አብዮታዊ ዴሞክራሲ እና ልማታዊ መንግስት አስተሳሰብ ሲገላበጥ የነበረን አገር በአንድ ጊዜ ሁሉን ለመክፈት መሞከር ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን መተንበይ አያዳግትም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል እየጎለበተ የመጣው ብዝሃነትን የማያከብር አሃዳዊነት አካሄድ፣ በትግራይ እየተሰማ ያለው እንዳንበተን የሚል ስጋት፣ በደቡብ ክልል የተጀመረው መሰነጣጠቅ፣ በኢትዮ-ሶማሌ ክልል ያለው የተዳፈነ እሳት፣ አገራችን ወደምናስበው የአንድነት እና መተሳሰብ ደረጃ ለማድረስ ገና የሚቀረን በርካታ የቤት ስራ እንዳለ የሚያመላክት ነው፡፡ የማይተማመኑ ባልንጀሮች በየወንዙ ይማማላሉ እንደሚባለው አንድ ነገር ኮሽ ባለ ቁጥር ሁሉም በየፊናው ማስፈራርያ የሚያቀርበው አሁንም ያልተቀረፈ ስጋት በህዝባችን ውስጥ ስላለ ነው፡፡ ይህንን ስጋት ለመቅረፍ ደግሞ ሂደት በመሆኑ ጊዜ ያስፈልጋል፣ የመሪዎቻንን ቅን ልቦናና ትጋትም ያስፈልጋል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ግዕዝ ቃል ይቀትል ቃል ይሓዩ እንዲል የመሪዎቻችን ንግግር ሰላምና መቀራረብን ሊሰብክ እንደሚችል ሁሉ በቋፍ ላይ ያለውን ወገን እንዲነታረክ እና ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዲያመራ ሊያደርግ ስለሚችል መሪዎቻችን ሲናገሩ እንደቤታቸው ሳይሆን መድረክ ላይ ሲወጡ እንደመሪ ቢሆን እላለሁ፡፡

አሁንም ያለን የተሻለ አማራጭ እንደ ድሮው ልዩነታችንን ይዘን አገር ለመምራት ግን እስከነልዩነቶቻችን ቁጭ ብለን በሃሳብ ላይ ውይይት ማድረግ፣ መከራከር፣ አሸናፊ ሆኖ የወጣውን አስተሳሰብ ለመተግበር ደግሞ በልበ ሙሉነት መነሳትን ነው፡፡ ሂሳብ የማወራረድ እና የበቀል ፖለቲካ ይበትነን እንደሆነ እንጂ በፍጹም አንድ አያደርገንም። ለዚህም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ድርጅትዎን በአስቸኳይ ይሰብስቡ፣ አሁን ያለው ችግር ከዚህ ቀደም ከተደቀነብን ችግር የተለየ ነው ብየ ስለማላስብ በሃሳብ ላይ ከተወያያችሁ ችግሩን የማትፈቱበት ምንም ምክንያት አይታየኝም፡፡ ይሁንና ግን ድርጅቱም እንደ ድርጅት ለመቀጠል የማይችል ከሆነም ይህንኑም በውይይትና በምክክር ብታደርጉት፡፡ አገር በቋፍ ላይ ሆና ደጋፊ ለማብዛት በሁሉም ወገን የሚደረግ እሽቅድድም የአገራችንን ውድቀት ያፋጥን እንደሆን እንጂ አይጠቅመንም፡፡ በዚህ ከቀጠልን ደግሞ ማንም አሸናፊ ስለማይኖር በውስጣችን ስንራኮት አገራችንን ለታሪካዊ ጠላቶቻችን አሳልፈን እንሰጣለን፡፡ ድርጅቱ ከዚህ ቀደም ሲያደርገው እንደነበረው ከተወያየ ግን ሁሉም አሸናፊ ሆኖ የሚወጣበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ሰላም ለኢትዮጵያ!

 

Back to Front Page