Back to Front Page

ህወሓት ምን ስላለች ነው ይህ ሁሉ የጭቃ ናዳ?

ህወሓት ምን ስላለች ነው ይህ ሁሉ የጭቃ ናዳ?

 

ዮሃንስ አበራ (ዶር) 7-14-19

 

ለህወሓት መግለጫ መልስ የሰጠው አዴፓ ብቻ አይደለም፤ የሰማይ ወፍ ሁሉ ነው፡፡ መልሶቹ ሁሉም አንድ አይነት ናቸው፤ ይህም ህወሓት ካቀረበችው ጥንቃቄ የተደረገበት መግለጫ ጋር የሚገናኙ አለመሆናቸው፡፡ አቦ ዘማርያም እንዴት ዋሉ ተብለው ሲጠየቁ ተልባ እየዘራሁ ነኝ ብለው የመለሱበት የትግርኛ ቀልድ አዘል ተረትና ምሳሌ ለዚህ የሚመች ነው፡፡ አቦ ዘማርያም የግዜር ሰላምታውን በቅጡ ሳያዳምጡ በውስጣቸው የሚያስቡትን ነው የተናገሩት፡፡ የአዴፓ መግለጫ የፖለቲካ ግብረገብነት የጎደለው መሆኑ የሚያመለክተው የህወሓትን የተፀውኦ ስም በአማርኛ ተርጉሞ መጥራቱ ነው፡፡ ከኔ የበለጠ እነሱ እንደሚያውቁት በአማርኛ ሰዋስው ደንብ የወል ስም ወይንም ቅፅል ስም እንጂ የተፀውኦ ስም አይተረጎምም፡፡ ህወሓት ትህነግ ስለተባለ ተፈንክቶ ደሙ ይፈሳል ብለው አስበው ከሆነ ብስለት የጎደለው ተግባር ነው፡፡ ባልና ሚስት ሲጣሉ እንደሚያደርጉት ማሬ ማሬ መባባል ቀርቶ አቶና ወይዘሮ እያሉ በስም እንደሚጠራሩት ያህል መውረድ የለበትም፡፡ ምንም ብትኳረፍ ፖለቲካ የራሱ የሆነ የቛንቛን ኤቲክስ አለው፡፡ አዲስ አባባ ፍንፍኔ ስትባል በዝምታ ራስ ምታቱ የሚነሳበት ጠባብ ፖለቲከኛ ሁሉ የህወሓት ስምን ተርጉሞ እንደ ስድብ ሲጠቀምበት ከግንድ ጋር የሚያላጋ ልጅ ያለውንና የሌለውን እየመረጠ ይመስላል፡፡

Videos From Around The World

ህወሓት ከከፈተኛ የፌደራል የስልጣን እርከን ተገልላ አመራሮቹ ወደ ትውልድ አገራቸው ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ ህወሓትና የትግራይ ህዝብ በመሃል አገር ከፖለቲካ መሪዎች ጀምሮ የማንም መንገደኛ የስድብ መለማመጃ ሆነው ከረሙ፡፡ በየሶሻል ሚድያው፤ በየቡና ጥሪው፤ በየበርጫው፤ በየስፖርት ወድድር ሜዳው፤ በየቡና ቤቱ፤ በየመማርያ ክፍሉ ተችተው፡ ተሳድበው፡ ተራግመው፡ በማይሰለቹ፤ ተዉ ለሃገር አይበጅም ቢባሉ ንቀታቸው ጣርያ አልፎ የሚሄድ፤ ያለ ህወሓትና የትግራይ ህዝብ ሌላ ጠላት ኑራቸው የማያውቁ የሚመስሉ፤ ስንት የአገር ልማትና የድህነት ቅነሳ የተወዘፈ ስራ እያለ ውድ ጊዜያቸውን በዚህ ፋይዳ ቢስ ተግባር የሚያሳልፉ ሰዎችን እያየንና እየሰማን ይኸው በትንሹ አንድ አመት አለፈ፡፡

ሓይል ለምግብ ማብሰያ ሳይቀር በሚያጥርበት አገር የኤልክትሪክ ሃይል እየተለቀቀላቸው በአስር ሃያ የተሌቪዝንና ሬድዮ ቻናሎች ስላለፈው ጨለማ ስርአት፤ ስለህወሓት መጥፎነት፤ ሰለአሁኑ ለውጥ ሰማያዊነት ሲተረክ ይውላል፡፡ እንደ አኒማል ፋርም ፖለቲካዊ ተረት ህወሓትና የነካችው ሁሉ መጥፎ፡ ሌላው ሁሉ ጥሩ የሚለው አዝማች ህፃናት ሳይቀሩ እንዲያቀነቅኑት ተደረገ፡፡ በታሪኩ ተጠቂ፡ ከዛ ሲያልፍ ነፃ አውጪ እንጂ አጥቂ ሆኖ የማያውቀው የትግራይ ህዝብ ይህ ሁሉ የማያባራ ውርጅብኝ እየሰማ በትእግስት ማሳለፉ ታላቅነቱንና ለዚች አገር ያለበትን የሃላፊነት ስሜት ማሳየቱ ነበር፡፡ ይህ ግን በጨዋ ደንብ እንደ ጀግንነት የቆጠረለት የለም፡፡ መቀሌ ላይ የመሸጉት፡ በትግራይ ህዝብ ጉያ የተሸጎጡት እየተባለ እንኳንና ሊተኩስ መሳሪያ በእጁ ነክቶ የማያውቀው ሁሉ ከብረት ጋር ተጣብቀው የኖሩትን ሰዎች በፈሪነት ሲፈርጁ ይሰማሉ፡፡ የትግራይ ህዝብ የህወሓት አመራሮችን የተቀበለው ልጆቹ ስለሆኑ ነው፡፡ የገዛ ልጆቹን፡ ያውም አብረው የመሃል አገር መንግስት ጥቃትን የተከላከሉ ባለ ውለታዎች የት እንዲጥላቸው ነው የሚጠበቀው? ለማንስ ብሎ? አብረው ሲያቦኩና ሲጋግሩ የከረሙ ሁሉ ራሳቸውን ወደ ዳኛነት ቀይረው ወንጀለኞችን አቅርቡልኝ አለዘያ... እያሉ ህዝብን ቢያስፈራሩ ከጅምሩስ በህወሓት ላይ ዳኛ አድርጎ የሰየማቸው ማነው? የትግራይ ህዝብ ህግ አክባሪ ነውና ዳኞችን የመረጣቸው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው ብሎ እርግጠኛ ሲሆን ልጆቹ ቢሆኑም ለህግ ያስረክባል፡፡ መጀመሪያውኑ የትግራይ ህዝብ ህወሓት እንደሰው ስህተቶች ብትሰራም በአብዛኛው ግን በጎ ስራ ሰርታለት ብሎ ያምናል፡፡ ጀግንነትና የዋህነት የተቀላቀለበቻው ራስ ስዩም መንገሻ በማእከላይ መንግስት ላይ በምክንያታዊነት ያመፀውን የገዛ ልጃቸው አባ ይላቅ ካሳን የፊጥኝ አስረው ወደ አራት ኪሎ ከላኩት በኋላ የሆነውን የታሪክ ሊቃውንት ይጨርሱት፡፡

የህወሓት አመራሮች የሰሯቸው ጥፋቶች ቢኖሩም ፖለቲካኛ ስለሆኑ ነው፡፡ ባለፈው፡ በአሁኑ፡ ለወደፊትም ብፁእና ፃድቅ የሆነ ፖለቲከኛ የለም፡፡ ጥሩ ነው ማለቴ ሳይሆን በነሱ ብቻ ተደርጎ የሚቀር ይመስል ፖለቲካኛ ሁሉ ባይመፃደቅ ጥሩ ነው ብየ ነው፡፡ ሕወሓት ሲወገዝ የከረመበት በአስተዳደር ላይ የሃይል አጠቃቀም ሳስበው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርላማ ቀርበው ትእግስታችን አልቛል የሃይል እርምጃ እንዋሰዳለን ይላሉ ብየ በህልሜም አስቤው አላውቅም ነበር፡፡ የለውጥ ፖለቲካው የተጀመረው አለቦታው በቅድስና ነበር፡፡ ወልደው ሳያበቁ በስው ልጅ አይሳቁ የሚባለው ተረት መግቢያው በዚህ በር ነው፡፡ የህወሓት አመራሮች የተፈጠሩት ከሰይጣናት አይደለም፤ የትግራይ ወላጅ ልጆቹን በሃይማኖት አንፆ ያሳድጋል፡፡ ሰው ፖለቲካ ውስጥ መግባትና ቤተመቅደስ መግባት አንድ አይነት አለመሆኑን በአንክሮ መገንዘብ አለበት፡፡ ቤተመቅደስ ስትገባ የምታገኘው ሰው ከአምላክ ጋር ለመገናኘት ፈልጎ የሚመጣን ነው፡፡ ስለዚህም በሌላ ምእመን ላይ ዱላ የሚነሳበት ምክንያት የለም፡፡ በሃይማኖት አንድ አምላክ ለቢልዮኖች ይበቃል፡፡ በፖለቲካ ግን አንድ ወንበር እንኳንና ለቢልዮን ለሁለት ሰውም አትሆንም፡፡ ለዚህ ነው በፖለቲካ ውስጥ ያለ ሰው ሳይቀደም ለመቅደም ዝግጁ የሚሆነው፡፡ ለዚህ ነው የሚወስደው የሃይል እርምጃ ገደብ የማይኖረው፡፡ መባል ያለበት ለምን አሰርክ፡ ለምን ደበደብክ፡ ለምን ገደልክ ሳይሆን ለምን ፖለቲካ ውስጥ ገባህ ነው፡፡ የፖለቲካ ስልጣን እንደ ከበሮ ሲየዩት ያምር ሲይዙት ይደናገር ነው፡፡ ስለዚህ ፖለቲከኛ ሁሉ መጠኑ ይለያይ እንጂ ሃይል የመጠቀሙ አዝማሚያ ባህርያዊ ነው፡፡

ባለፉት ሁለት አመታት ተዘውትሮ የሚነገረው ትርክት አራት አባል ድርጅቶች ያሉት ኢህአዲግ ኢትዮጵያን ለ27 አመታት ሲያስተዳድር እንደ ስላሶች አንድም አራትም ሆና ኢትዮጵያን የገዛችው ህወሓት ናት የሚለው ምስጢረ ስላሴ (አራቴ) ነው፡፡ ኦህዴድና ብአዴን ህወሓትን እስከመገርሰስ የደረሱት ጫካ ገብተው ባካሄዱት የትጥቅ ትግል ነውን? የማይካደው ሃቅ ህወሓት አይኗ እያየና ጀሮዋ እየሰማ፡ ምናልባትም ድጋፍ እየቸረች ስላጎለመሰቻቸው ነው፡፡ ህወሓት ጨቁና ይዛቸው ቢሆን ኖሮ ከማን እይታ ውጪ ሆነው ነው ይህን ያህል ክንዳቸውን ያፈረጠሙት? የህወሓት እህት ድርጅቶች የሚባሉት 27 አመት ሙሉ ሲወሰን በነበረው ውሳኔ ሁሉ እጃቸውን እያወጡ ድምፅ ሳይሰጡበት በህወሓት ድምፅ ብልጫ ብቻ ሲወሰን ነበረን? የኢትዮጵያ ህዝብ ይህን ያህል የመርሳት ችግር ያለበት አይመስለኝም፡፡ ከፍርድ ለማምለጥ ጴጥሮስ ለቅዱስ ሃዋርያነት ያበቃውን ክርስቶስን አላውቀውም ብሎ ብቻውን እንዲሰቀል ያስፈረደበት አይነት ተግባር ሲፈፀም ይታያል፡፡ ጴጥሮስስ የማይቀር ትንቢት ሆኖበት እንጂ ወዶ አይደለም፡፡ በአለም ትልቁ መቅደስ የሰራለት ጰጥሮስ ነው፡፡ የኢትየጵያ የኢህአዲግ ጴጥሮሶች ግን ከጣሉም በኋላ ማቆም አልቻሉም፡፡

አዴፓ በመግለጫው ህወሓትን በሴራ ፖለቲከኛነት ፈርጃ;ል፡፡ ይህ አስገራሚ አባባል ነው፡፡ እንቆቅልሽ የሆነ የሴራ ፖለቲካ እያያን ያለነውስ አሁን ነው፡፡ ህወሓት በደጋፊዎቿ ዘንድ የምትተችበት ደረቅ መርኽኝነት፤ ጀብደኝነትና ማን አለብኝነት ነው፡፡ የሴራ ፖለቲካ የሚሰራው እኮ ካቅም በላይ የሆነ ነገር አለ ተብሎ ሲታመን ነው፡፡ ራስዋን ከገመገመች በኋላ አሁን ጀምራው ካልሆነ በስተቀር ህወሓትን ለዚህ ያበቃት ስልት የራቃት ድርጅት በመሆንዋ ነው፡፡ እህት ድርጅቶቿ በግምገማ አደባባይ ወጥተው ሳይጨፋጨፉ ገመናቸውን ሸፈን አድርገው ለረዥም ጊዜ አላማ ሲዘጋጁ ህወሃሓት ናት አገር ጉድ እስኪል ድረስ ስትበጣበጥና ራስዋን ስታዳክም የቆየችው፡፡ ይህ ራስን የማጥፋት አባዜ የሴራ ፖለቲካ ከሆነ ትርጉሙ ተገልብጣዋል ማለት ነው፡፡

በመሰረቱ በአስር ካባ ለማለባበስ ቢሞከርም የኢትዮጵያ ህዝብ የታገለው የስርአት ለውጥ ለማምጣት ነው እንጂ የተበላሸውን ጥርስ በጅል አነቃቀል ሸርፎ ቀሪውን የተነካካ ሽራፊ በጀሶ እየጠጋገነ ለማቆየት አይደለም፡፡ ተሸርፎ የቀረ ጥርስ ሰላም እንደማይሰጥ የደረሰበት ሁሉ ያውቀዋል፡፡ መሰረታዊ ለውጥ ባልተነካካ አዲስ ልብስ እንጂ ከቅዳጅ የተረፈውን በመደረት አይገኝም፡፡ የህዝብ ስሜት የሚያዳምጡ ከሆነ የኢህአዲግ እህት ድርጅቶች ያላቸው አማራጭ ተስማምተው፤ ስህተታቸውን አርመው፤ መጎነታተልን አስወግደው፤ አንድ ላይ አገርን ማስተዳደር አለዚያ ሁሉም ጥርግ ብለው ወርደው አገሪቱ በጠንካራ አዲስ ትውልድ እንድትመራ ማድረግ ነው፡፡

ማንም ሰው ሲሞት ያሳዝናል ያስለቅሳል፡፡ በፖለቲካ ሽኩቻ የሚመጣ ሞት ግን ከማሳዘን አልፎ ግራ ያጋባል ያስፈራልም፡፡ በሰኔ ወር የተፈጠረው አሳዘኝ ድርጊት ያስከተለው ሞት ሁሉም አስቆጪ ነው፤ የሞቱት ሁሉም ወገኖቻችን ናቸውና፡፡ የአዴፓ የውስጥ ትግል መስሎ በታየው የባህርዳር እልቂት ጋር ምን ግንኑነት እንዳለው በቅጡ ያልታወቀው የሁለቱ የጦር ልምድ ያካበቱ የትግራይ ተወላጅ ጀኔራሎች መረሸን አስደንጋጭና ግራ የሚያጋባ ሆል፡፡ የትግራይ ህዝብ የዛሬውን አያድርገውና የቁልምጫ ስም ሳይወጣለት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ጨካኝ አምባገነን ሲለው የነበረውን ደርግን ለማስወገድ በአስር ሺዎች ልጆቹን በየሜዳውና ተራራው ቀብሮ ሌሎች አስር ሺዎችን በአካል ጉዳተኛነት የእድሜ ልክ እንክብካቤ እየሰጠ የሚገኝ ቆዳው በመከራ የሳሳ ህዝብ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ባእድ ህዝብ እስኪመስል ድረስ ሲደርስበት የቆየው በደል ተሸክሞ እናት አገሩን ጥሎ የት ሊሄድ እንደሚችል ግራ ገብቶት ባለበት ወቅት የብራ መብረቅ የሆነ የውድ ልጆቹን የግፍ ግድያ ሰማ፡ አለቀሰ፡ ቀበረ፡፡ ይህ ለትግራይ ህዝብ ከወሰን ያለፈ ነገር ነው፡፡ የትእግስት ገደቡ የት እንደሆነ መጠየቅ የሚጀምርበት አጋጣሚ ሆኖበታል፡፡ የትግራይ ህዝብ አሁንስ ፈልቶ ይገነፍላል ተብሎ ሲጠበቅ ያሳየው ጨዋነት በታሪክ የሚመዘገብ ነው፡፡ ለዚህ ሰልታዊ የሆነ የነገሮች አያያዝ አመራር ስትሰጥ የቆየችው ህወሓት ናት፡፡

እኔ ላለፉት ብዙ አመታት ህወሓትን ስተች ነበር፡፡ አቶ ልደቱ ትናንት እንዳስቀመጠው የሚተች ወዳጅ እንጂ ጠላት አይደለም፡፡ ጠላትማ እያቆላመጠ አይንን ጨፍኖ ገደል አፋፍ የሚያደርሰው ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ትችቴ ግን ህወሓት እንድትጠፋ ተመኝቼ አላውቅም፡፡ ለምን ቢባል ህወሓት ባትኖር የትግራይ ህዝብ ምንም አይሆንም የሚለው ቀልድ በሳቅ ስለማልቀበለው ነው፡፡ ሌላ የበቃ የክልል አመራርነት መጨበጥ የሚችል ሃይል በሌለበት ህወሓትን ማሳደድ የትግራይን ህዝብ ማፍቀር ነው ብየ አልተረጉመውም፡፡ የትግራይ ህዝብን የሚወድ ሃይል ያለመሪ ቀርቶ እንዲበተን የሚመኝ አይሆንም፡፡ ከአፄ ዮሃንስ ህልፈት በኋላ የተፈጠረው የአመራር ክፍተት ዘውዱን በመሃል አገር ለማደላደል ጥቅም ላይ ዋለ እንጂ ለትግራይ ህዝብ በሚጠቅም መልኩ ማስተካከል የሞከረ አልነበረም፡፡ የህዝብ ሃላፊነት የማይሰማቸው የትግራይ መኳንንትና መሳፍንት በማይረባ የወረዳ ግዛት መቀማማት ህዝቡን ሲያፋጁት ማእከላዊው መንግስት አንዴ በዝምታ፤ አንዴ በማስታረቅ፤ አንዴ በማጣላት፤ አንዴ ከሌላ የበላይ ገዢ በመላክ ክልሉን መቅኖ አሳጥተው ለዘላቂ ድህነትና ስደት እንደዳረጉት አይዘነጋም፡፡ የአሁኑ በህወሓት አመራር ላይ የሚደረገው ዘመቻ የድሮው እባብ ነው ወይስ የአሁን ልጥ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ከመታገል መጠንቀቁ ይመረጣል፡፡ እኛም መክረናል ጉድጓድ ጭረናል ያሉት አይጦች የሚመጣው የድመት መንጋ የሙሽራ ስብስብ ይሆን ጥርስ ያሾለ በላተኛ መለየት ስላቃታቸው ነው፡፡ ካላቸው ልምድ ውስጣቸው የነገራቸውን ሰርተው ተጠናቀዋል፡፡

የትግራይ ህዝብና ህወሓት በቀላሉ የማይተኩ ውድ ልጆቻቸውን ከቀበሩ በኋላ ይህ እንቆቅልሽ ባጭር ጊዜ ካልተፈታ እንደማይደጋገም እርግጠኛ መሆን አልቻሉም፡፡ የተለያዩ ስእሎችን በመገጣጠም በአይምሯቸው ውስጥ የሚመላለሰውን መላምት በመግለጫ መልክ አወጡ፡፡ ይህ መአት በመግለጫ ብቻ መታለፉ ተመስገን የሚያሰኝ ነው፤ ብዙ ሰው አድሮበት ከነበረው የመበቃቀል ስጋት አኳያ፡፡ ህወሓት በዚህ መግለጫ ያሰፈረቻቸው ቁም ነገሮች ውሱንና ጥንቃቄን የተላበሱ ናቸው፡፡ ጥቂት ትምክህተኞች አገሪቱን እየበጠበጡ መሆኑ፤ የአማራ ህዝብ ትምክህተኛ ተብሎ እንደማይፈረጅ፤ አዴፓ አክራሪ ፀረ ትግራይ ቡድኖችን መቆጣጠር እንዳቃታት ወይንም ባታሰማራቸውም እንደማትከለክላቸው፤ ባህርዳር ላይ ፈንድቶ አዲስ ኣበባ ላይ ነፍስ ያጠፋው ድራማ ባስቸኳይ እንዲጣራ፡ ካልሆነ ከንዲህ አይነት ድርጅት ጋር አብሮ መስራት እንቸገራለን ብሎ የተረጋጋ መግለጫ ማውጣት ተመጣጣኝ ያልሆነ ቁጣ ያስከተለበት ምክንያቱ ምንድነው? በሃዘን ላይ እያለን እንደማፅናናት መግለጫ ላካችሁብን ብሎ ማለትስ ሃዘን ያጋጠመው አዴፓ ብቻ ነው ወይ የሚለው ጥያቄ አያስከትልም? የለቅሶ ዳስ አፍርሶ የገዳይን ማንነት ማጣራት ህጋዊ ብቻ ሳይሆን ባህላዊም ነው፡፡ ያ ጀግና በረኽኛ ስመኘውን የበላ ጅብ ሳይጮህ ሲቀር ሌላ ጅብ መጥቶ የአገር ህልውና አለኝታዎችን ቀጠፈ! እና ይቀጥል?

ህወሓት የአማራን ህዝብ ለማጥፋት የምትፈልግበት ምንም ምክንያት የላትም፡፡ ህወሓት ውስጥ ከመስራቾች ሳይቀር የአማራ ዝርያ ያላችው መኖራቸው አባባሉን አስቂኝ ያደርገዋል፡፡ ዘር ባይኖርስ አማራና የትግራይ ህዝብ የሚለየው ነገር ቢኖር ቛንቛው ላይ አበባ የሚለው ቃል ዕምባባ መሆኑ ነው፡፡ ምንም የጋራ ነገር ባይኖረውስ? የትግራይ ህዝብ ሆነ ከሱ የተገኙት ልጆቹ አንዳንድ ዲያብሎሳዊ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ማመን እንደሚፈልጉት ፀረ ሰው አይደሉም፡፡ ለፖለቲካ ህልውና ብሎ የአማራን ህዝብ አስፈራርቶ ማነሳሳት እውነቱ ኢስኪጋለጥ ድረስ ብቻ ሊገፋ ይችላል፡፡ በአጀንዳ መሰረት መልስ እንደመስጠት የ1968 ማኒፌስቶ ለማጠቀስ መሮጥ የመጠቃቃት አይነት ግብረ መልስ ከበሰሉ ሰዎች የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ማኒፌስቶው ይሁን ሌላ ሰነድ የአማራን ስም አንስቶ ከሆነ የሚጠቅሰው የአማራ ገዢ መደብ እያለ እንጂ ህዝብ እንደ ህዝብ ማንንም ሌላ ህዝብ እንደ ህዝብ ገዝቶ የማያውቅ መሆኑን ጠንቅቀው ያውቁ የነበሩት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ታጋዮች በህልማቸውም አያስቡትም፡፡ ትምክህተኞች በተባለ ቁጥር ያንተ ስድብ ነው እያሉ አማራ ህዝብ ላይ መለጠፍ ተንኮል ነው፡፡ ትምክህተኛነት የህዝብ አመለካከት ሳይሆን የጥቂት አክራሪ ብሄርተኞች ርእዮተ አለም ነው፡፡ ትምክህተኞች ህዘቡን ከሁሉም የበላይ ነህ፡ ገዢ መሆን ያለብህ አንተ ነህ፡ ከ86ቱ ብሄሮች ልቀህ በአምላክ ለአስታዳደር የተቀባZው አንተ ነህ እያሉ በስሙ ስልጣን ላይ ለመቆናጠጥ ህዝቡን የጥይት እራት የሚያደርጉ ሰዎች አሉ፡፡ ትምክህተኞች የኣማራ ህዝብ የመረሩ ጠላቶች ስለሆኑ የትግራይ ህዝብ እያለ ያለው ተጋግዘን እናሸንፋቸው ነው፡፡ የነገር መርፌ ቢጣመም የእውነት ቅቤን አይወጋም፡፡ በኢሳትና ሌሎች ሚድያዎች ምሁራን እየተባሉ የቀረቡት አስተያየት ሰጪዎች ያለምንም ልዩነት አዴፓ ጀግና ወጣው፤ ህወሓትን ነገራት እስኪበቃት፡ እያሉ የመንገድ ላይ የጎረምሶች ድብድብ አስመስለውታል፡፡ ብአዴን የህወሓት ሎሌ ከነበረበት አዴፓ ነፃ የሆነ አማራን የሚወክል ድርጅት ሆኖ ራሱን አፅድ~ልና ምን ቢያደርግ ምን ሙሉ ድጋፍ እንስጠው ብለው የወሰኑ የሚመስሉት ጋዜጠኞችና ፖሊቲከኞች ቆንጆ የሆነ የቁልምጫ ስም ለማውጣት የተቸገሩ ይመስላሉ፡

ህወሓትን ማብጠልጠል የነጠላ ሰረዝ ያህል በተዘወተረበት ወቅት ሌላ በተደራቢ የተገነዘብነው ነገር ቢኖር የሰከነና ሚዛናዊ የሆነ የፖለቲካ አም ባለቤት የሆኑት አቶ ልደቱ አያሌው በአሃዱ ቴሌቪዥን ቀርበው መላ ባጡ ፖለቲከኞች የተዘለፉበትን ወደ ትግራይ ያደረጉት ጉዞ በስሜት ተውጠው ትክክለኛነቱን ለማሳመን ሲታገሉና ወቃሾቻቸውን መልስው በጠጣር ቃላት ሲወቅሱ አይቼ የወደፊ~ን ኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ለማየት የምችልበት አይኔ የተጋረደ ሆኖ ተሰማኝ፡፡ እድሜ ልክ ከማይቀየሩ፡ ሊቀየሩ ከማይፈልጉና እየባሰባቸው ከሚሄዱ የጥፋት ፖለቲከኞች ጋር ሆኖ መስራት የሚቻለው ኢትዮጵያን መገንባት ሳይሆን የባቢሎን ግንብን አብሮ ማፍረስ ብቻ ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ በእብሪት ከሚወዳት አገሩ እየተገፋ መሆኑ ማየት የተሳነውም ቢሆን አይስተውም፡፡ በባህረ ነጋሲ ላይ የተፈፀመው ግዴለሽነት በትግራይ ላይ እየተደገመ ነው፡፡ ወዳጆቻችን ሆነዋል ብሎ የኢሳት ጋዜጠኛ ተስፋ በጣለባቸው የኤሪትርያና የሱዳን መንግስታት ትግራይን ከበው ስለያዛት ማምለጫ የላትም እያለ ሲሳለቅ የኢትየጵያ ፖለቲካ የመዋእለ ህፃናት ጨዋታ ወደ መሆን መውረዱን ያሳያል፡፡ እንኳንና የትግራይ ህዝብ ያለ ረዳት ለዘመናት የተጋረጡበትን ውስብስብ ችግሮች አሸንፎ የወጣ ቀርቶ ማንም ህዝብም ቢሆን መውጫ ሊያሳጡት ሲሞክሩ ወደ ጢስነት እንደሚቀየር የታወቀ ነው፡፡ ይልቅስ ለኢትዮጵያ አንድነት ዘላቂነት የሚያስብ ሁሉ የትግራይን ህዝብ ይቅርታ በመጠየቅ ተከባብሮና ተፈቃቅሮ ለመኖር ጥረት ቢያደርግ መጪው ጊዜ ብሩህ ይሆናል ብየ አስባለሁ፡፡

Back to Front Page