Back to Front Page

ኢትዮጵያ የማናት?

 

ኢትዮጵያ የማናት?

ከአበበች መስፍን

ህዳር 11/2ዐ12 ዓ.ም

ማነው ኢትዮጵያዊ፣ ኢትዮጵያን ወካይ፣

እኔ ነኝ የሚል፣ ይውጣ አደባባይ፡፡

እስቲ ይናገር ፣ ኢትዮጵያ የማን ናት፣

የጥቂቶች፣ ወይስ፣ የሁሉም እናት ናት ፡፡

ማን ነች እስዋ፣ ማነው ባለቤትዋ ፣

እነማን ናቸው፣ የት አሉ ልጆችዋ፡፡

ታላቁ የቱ ነው፣ የቱ ነው ታናሹ፣

የግሌ ናት ባዩ፣ የቱ ነው ወራሹ!!

ማነው የቤት ልጅ፣ ማነው የእንጀራ ልጅ፣

ስጋውን የካደ ፣ ለናቱም የማይበጅ፣

ፈቃድ ሰጪ ማነው፣ የቱ ነው ከልካዩ፣

ይኸው ነው ድርሻችሁ፣ ብሎ አከፋፋዩ፡፡

ማነው ጠያቂው ፣ መላሹስ የቱ ነው፣

እንደግል ቤቱ፣ አዛዥ የሚመስለው፡፡

እውነቱን እንወቅ፣ ይቀዳ ከምንጩ፣

ይቅረብ እሴታችን ፣ አጉልቶ ገላጩ፡፡

ከምእራብ ያለው ነው፣ ወይስ ከምስራቁ፣

ከሰሜን ከደቡብ፣ ከመሓል መፍለቁ፣

ኢትዮጵያዊነት፣ ምንድነው መስፈርቱ፣

ይፈተሽ መዝገቡ፣ ይታወቅ እውነቱ፡፡

መሪው የቱ ነው፣ ተመሪውስ የታል፣

የትኛው፣ ለየትኛው፣ ውክልና ሰጥቷል፡፡

የቱ ልጅ ነው ቅርቧ፣ የቱ ነው የራቃት፣

የናትነት ፀጋ፣ ፍቅር ያልተጋራት፡፡

ይልቅስ፣ ቅኔውን ትተን፣ ውዳሴ በከንቱ፣

ይሻላል ማወቁ፣ ከስር መሰረቱ፡፡

መቼ ፣እንዴት፣ በማን፣ በምን አይነት ቅኝት፣

የሚለው ጥያቄ ይመለስ፣ ከታሪክ ድርሳናት፣

ማነው ኢትዮጵያዊ፣ ኢትዮጵያስ የማናት፣

የማን፣ የእነማን፣ የየትኛው እናት ናት?????

 

Back to Front Page