Back to Front Page

የኢህአዴግ የስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ተጠርቷል። ለምን?

የኢህአዴግ የስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ተጠርቷል። ለምን?

 

ዑስማን ሙለዓለም

ከሐራ ገበያ

ህዳር 2012 ዓ/ም

 

 

በለፈው ክረምት ላይ ተሰብስቦ ያለ መግለጫ የተበተነው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ሌላ ስብሰባ ቅዳሜ ህዳር 6፣ 2012 ዓ/ም ሊያደረግ መሆኑ ታውቋል።ግን ለምን አሁን ተጠራ?እንገናኛለን ብለው የተቀጣጠሩበት ጊዜኮ አልፏል።ታድያ አሁን በማን ግፊት ይሆን ስብሰባው የተጠራው? በአቶ ለማ? በህወሓት? በአዴፓ? በአብይ? ወይስ በጆሃር?

 

ለለወጡ/ለነውጡ መሪዎች ምስጋና ይግባቸውና አገራችን ኢትዮጵያ በየቀኑና በየሰኣቱ አዳዲስና አስደናጋጭ ሁኔታዎች የሚከሰቱባት አገር ሆናለች፡፡ ካለፈው የስራ አስፈፃሚው ስብሰባ እስካሁን የተከሰቱ ሁኔታዎች ምን ምን ነበሩ? ብሎ ማስታወሱ ጥሩ ነው፡፡ በአጭሩ ቀውስ ላይ ቀውስ ሲፈጠር ከርሟል ብሎ መዝጋት ይቻላል። ነገር ግን የስራ አስፈፃሚው ስብሰባ በምን አይነት ድባብ እንደሚካሄድ ለማየት እንዲጠቅመን የነበሩ ክስተቶች ዘርዘርና አጠር አድርጎ ማየቱ በጣም አስፈላጊ ነው።

 

Videos From Around The World

1.   ክረምቱ አልቆ መስከረም ሲጠባ በምንሊክ ቤተመንግስት ጠቅላዩ የኢህአዴግ ሊቀመንበር የሚል ስም ይዘው የኢትዮጵያ ህዝቦችን መንጋ እያሉ እያሰደቡን አደሩ። ይህ አገላለፅ በብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ላይ ክፉኛ ቁጣ አስነስቶ ነበር። በአንድነት ሃይሎች ደግሞ ጠቅላዩን የኛ ባትሆን ይቆጨን ነበር አሰኝቶላቸው ነበር።

2.   አመታዊውን የእሬቻ በዓል በፍንፍኔ ይከበራልተብሎ ከተገለፀበት ቀን ጀምሮ ምድረ ትምክህተኞች ተንጫጭተው ነብር። በዓሉ በፍንፍኔ በድምቀት ተከበረ። በበዓሉ ላይ ኦቦ ሽመልስ ነፍጠኛን በተመለከተ በአደባባይ በግልፅ በመናገራቸው መንጋ ተብለው በአዲስ አመት መባቻ የተሰደቡት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ደስ ብሏቸው ነበር። በተቃራኒው ደግሞ ነፍጠኞቹ እርር ድብን ብለው ተበሳጭተው አዎ! ነፍጠኞች ነን! እና ምን ይጠበስ? ብለው ነበር። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ነፍጠኝ የሚል ስም ከተረሳ ዘመን አስቆጥሮ ቆይቷል። ታምራት ላይኔ ድሮ 16 ሚልዮን ዶላር መንትፈውና በስልጣን ባልገው ከስልጣን ወርደው፣ ተከሰውና ተፈርዶባቸው ላይታረሙ ማረሚያ ቤት ከመውረዳቸው በፊት የታጋይ ካባ ለብሰው በነበረበት ወቅት በፍንፍኔ ስታድዮም ነፍጠኛ በማለታቸው አሁን የተቀላቀሉት ካምፕ የስድብ ውርጅብኝ አድርሶባቸው ነበር። ከዛ በኃላ ቃሉ ብዙም ሳይጠራ ቆይቶ በቅሩቡ ኦቦ ሽመልስ በማንሳታቸው ምድረ ትምክህተኛ የተለመደው አካኪ ዘራፍን ተያይዞታል፡፡ በዚህም የነፍጠኝነት ስርዓት ምን ያህል አስከፊ እንደነበረ ያሁኑ ትውልድ እንዲገነዘብ ዕድል ፈጥሮ አልፏል።

3.   የፍንፍኔ - ጎጃም እና የፍንፍኔ - ደሴ መንገድ መዘጋት በአማራ ክልልና በኦሮሚያ ክልል አስተዳደሮች መካከል ጭቅጭቅ አስነስቶ አልፏል። ፀረ ህወሓት የነበረው የኦሮ-ማራ የቅንጅት ግንባርም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የፈራረሰበት ጊዜ ሆኖ አልፏል።

4.   የአማራ ክልል ከዶክተር አምባቸው መገደል በኃላም መረጋጋት አልቻለም፡፡ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ህግና ስርዓት ጠፍቶ፣ ግጭትና ተኩስ ያልተለየበትና ስርዓተ አለበኝነትን መገለጫው ሆኖ ቆይቷል። በቅማንቶች ላይ የሚፈፀም ጭፍጨፋም እንደቀጠለ ነው። በከምሴ በየግዜው የሚያገረሹ ግጭቶች እስካሁን አልቆሙም። ከትግራይ ክልል በሚያዋስኑ አካባቢዎችም የሽምቅ ተዋጊዎችን እያስገቡ ግጭትና ንትርክ መክፈታቸው ቀጥሏል። በአፋርና በቤንሽንጉልም በተመሳሳይ ሁኔታ ህዝብ ከህዝብ እንዲጋጭ ተደርጋል። አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡

5.   የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ፌደራል ሃይሎች በትግራይ መዲና መቀሌ ላይ ተሰባስበው ህገመንግስቱና ፌደራል ስርዓቱን እንዴት እንታደገው? አገራችን ኢትዮጵያ ከመፈራረስና ህዝብዋ ከዕልቂትና ከብተና እንዴት ማዳን እንችላለን?በሚል ዙሪያ የመከረ ስብሰባ ተካሂዷል። ሁለተኛው ዙር ስብሰባም በያዝነው ህዳር ወር ለማካሄድ በዝግጅት እንዳሉ ተሰምቷል።

6.   ጠቅላዩ ይህ የዲሞክራቲክ ፌደራል ሃይሎች ስብሰባ ይሆን ሌላ እልህ ያስገባቸው ለጊዜው አልታወቀም ግን ከውጭ አገር ሽርሽራቸው እንደተመለሱ ሳያርፉ መደመርና ውህደት የሚሉ ቃላቶች ፈበረኩ፡፡ ሶማሊ ክልል በቀጥታ ሂደው እንወሃሃድ አሉ፡፡ ስንወሃሃድ በኔ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስተር የመሆን እድል ይኖሯችኃል የሚል ሃሳብ አራመዱ 7ኛው ንጉስ። ይህ እድል በወያኔ ጊዜ ተነፍጋቹኃል የሚል አዜኔታ አይሉት ባልት አሰሙ፡፡ ከዛማ ምን አለ የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ስራ ፈተው የመደመር እሳቤና ውህደትሆነ ማቀንቀኛቸው። ሁሉም የመንግስት ቴሌቭዥኖች ሲከፈቱ ሌላ ነገር የለም። በአንድ ልሳን መደመር፣ ውህደት፣ የዶ/ርአብይ ፍልስፍና የሚሉ ብቻ ሆኑ። አብይ አህመድ መፅሓፍ ፃፉ ተብሎ የማስመረቅ ሽርጉዱ ደግሞ ሌላ የቴሌቭዥኖች ስራ ሆኖ ከረመ።

7.   መፅሓፍ በሙሁራን በተለይም ከፌደራል ስርዓት ደጋፊዎች ጠንከር ያለ ተቃውሞና ሂሶች ቀረቡበት። መስቀል ምልክቱ ያደረገ ሃይማኖትና ፖለቲካ የተቀላቀለ ስብከት እንጂ ፍልስፍና አይደለም አሉ። ሙሁራኑ በመቀጠልም የሌሉ፣ የማይስማሙ እና በልዩነቶች የተወጣጠሩ የኢህአዲግ ድርጅቶች ሊወሃዱ ቀርቶ የነበራቸው ግንባር ጠብቀው መሄድ ተስኗቸዋ እየታየ ውህደት ብሎ ነገር ዕብደት እንጂ ምንም አይደለም አሉ። የኢህአዲግ ድርጅቶች ውህደት እየተባለ ባለበት ሁኔታ ደግሞ በኦሮሚያ የሚንቀሳቀሱ የኦሮሞ ድርጅቶች ትብብር ያስፈልገናል ብለው በአንድ ጥላ ስር እንደራጅ ሲሉ አብይ አህመድ ኦዲፒን ይዘው እኔም ልግባ ብለው ተቀላቅለዋል። የውህደቱን አጀንዳ ረስተውት ወይስ ምን ፈልገው ይሆን? አይታወቅም።

8.   ሌላው ምንጩና መጠኑ በውል በመንግስት የማይታወቅና ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ የሚያውቁት በሚልዮን ዶላሮች ወጪ ተደርጎ የአፄ ምንሊክ ቤተመንግስት እድሳትና የአፄዎቹ ሐውልት ስራና ምርቃት ተፈፅሞ ነበር። ምንም እንኳን ለአፄ ሐይለስላሴ ተብሎ የተሰራው ሐወልት ለአቶ በቀለ ገርባ ይቀርባል ተብሎ ቢታማም፡፡ ይህ ስራ ከሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች ችግሮች በቅድመ ተከተል ቅድሚያ ተሰጥቶት የተሰራ ስራ ሰለሆነ ብዙዎችችን ኢትዮጵያውያን ቢያሳዝነንም ጠቅላዩና ጥቂቶችንም ጨምሮ ያስፈነጠዘ ሆኖ አልፏል።

9.   ኦሮሚያ ክልል ሰላም ሳይታይ ከርሞ በአዲሱ ዓመትም ሰላም ሳይነፍስበት አለ። ደማቅ የእሬቻ በዓል ከመካሄዱ ውጭ ሌላው ጊዜ ህዝቡ ጥያቄዎቻችን አሁንም ይመለሱልን ብሎ በትግል አሳልፎታል። በአራቱም የወለጋ ዞኖች በህዝቡና በመንግስት ፀጥታ አስከባሪዎች መካከል እስካአሁንዋ ሰዓት ውጊያው አልተቋረጠም። ጉጂ፣ ምስራቅና ምዕራብ ሀረርጌም እንደዛው ነው ያለው።

10. መነካካት የሚወዱትና ነካክተው ምን እንደሚፈጠር የማይገምቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁንም በፓርላማ ገብተው ነፍጠኞች የሏካቸውን ለማስፈፀም ሲዘላብዱ የማይነካ ነክተው እርፍ አሉ፡፡ ቀደም ብሎ ጠርጥሯቸውና መጥላትም የጀመራቸውን ህዝብ አስቆጥተው እንዳሉ ምንም ሳይታዘቡ ወደ ሩስያ ሲሄዱ እንደተለመደው ወጣ ካልኩኝ በኃላ የጆሃር መሐመድ ነገርን አደራ አሉ፡፡ አደራ የተባሉት ሰዎች የጠቅላዩ አደራ በሉባቸውና በመላው ኦሮሚያ በቀጥታ ጥሪ፣ ማንም ሳያዘው፣ ቆፎው እንደተነካ ንብ ቁጣውን ለማሰማት ወጣ። እዚህ ላይ ግን ሁለት ነገር ልበል።

ሀ. በኦሮሚያ የተካሄደው ተቃውሞ ጆሃር ለምን ተነካ አይደለም፡፡ተቃውሞው የኦሮሞ ህዝብ በአብይ አህመድ ላይ የነበረው ጥርጣሬና ጥላቻ የመጨረሻ ጥግ መድረሱ ነው የሚያሳየው።

ለ. ተቃውሞው አብይ አህመድ ሊቀባው እንደፈለገው ፀረ ሌሎች ብሄሮች/ህዝቦች የተነሳ አይደለም፡፡ ፀረ አብይ አህመድ የሚመራው መንግስትና ስርዓት በሰለጠነ መንገድ የተደረገ ህዝባዊ ተቃውሞ ነው። የአብይ አህመድ መንግስት ተቃውሞውን ለመጨፍለቅ ባደረገው እንቅስቃሴ ከ87 በላይ ሰዎች እንዲገደሉ ሁኗል። ሰላማዊ የነበረውን ትግል ደማዊ ሁኖ እንዲታይ ሆነ ተብሎ በገደል ማሚቶዎቹ የኢትዮጵያ አሃዳዊ ሚድያዎች ተዘምቶበታል። ገድለው ቢያፍሩ የሚያስብል ነው።

በዚህ መሃል ኦፒዲዎች ህዝቡን ለማረጋጋት ህዝባዊ ስብሰባ እናደርጋለን አሉ። በተለያዩ አከባቢዎችም ስብሰባ ጠሩ። ጠቅላዩ ሀረርና አምቦማ ብቻዬን አልሄዳትም ያሉ ይመስል ኦቦ ለማ መገርሳን አስከትለው ሄዱ፡፡ ጠቅላዩ ህዝቡ በሁለቱ መካከል ያለው አተያይ ምን ያህል እንደተለያየ ሀረር ላይ ሳይታዘቡ አልቀሩም። እንደኔ እንደኔ ሀረር ላይ ለመሆኑ ኦሮሞ ነህ ወይ? ተብለው ሲጠየቁ ከሀረር በቀጥታ አዲስ አበባ እንጂ ወደ አምቦ መሄድ አልነበራቸውም። ነገር ግን ከፍ ባልክበት ተዋረድ ሲላቸው አምቦ ሂደው መውጫ አጥተው፣ ተጨንቀው፣ አጃቢዎችንም አስጨንቀው በሄሊኮፕተር ወደ ፍንፍኔ ሳይሆን ወደ ምንሊክ ቤተመንግስት እንደ ቀዳማዊ ሐይለስላሴ እና እንደ መንግስቱ ሸሽተው ገቡ፡፡ የማን ይያዙ?

ቢቢሲ የአምቦ ሁኔታ ሲዘግብ የሳቸው ሚድያዎች እንደሀረሩ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአምቦ ሕዝብ ጋር ያደረጉት ውይይት በድል ተጠናቀቀ አሉን። ይህ የአምቦ ህዝብ ተቃውሞ ልዩ ክስተት ነው ለኖቤል ተሸላሚው ንጉስ። በአሮሞ ህዝብ ዘንድ ደግሞ ትልቅ የለውጥ ምእራፍ ነጥብ ነው። የኦሮሞ ህዝብ ትግሉ ወደ ከፍ ያለ ምዕራፍ ያሸጋገረበትና ለእሳቸው ያለው ድጋፍ ደግሞ ወደ ቁልቁለት መንገድ የከተተበት ነው።

11. ሰሙኑን ድግሞ ዩኒቨርስቲዎች ላይ የተጀመረ የተቃውሞ እንቅስቃሴ አለ። ፖሊስና መከላከያ የየዩኒቨርስቲዎቹ ካምፓሶችን ካምፓቸው እስኪመስል ድረስ ተቆጣጥረውታል። ኮማንድ ፖስት ክልሎች አዳርሶ ዩኒቨርስቲዎችንም ባለተረኛ አድርጎዋቸዋል። በዩኒቨርስቲዎቹ የሚደረጉ ብጥብጦችና የእምቦቆቅላ ተማሪዎች ደምና ህይወት ግን እየታደገ አይደለም ያለው፡፡

12. የሰኔ አስራምስቱ በባህርዳርና በአዲስ አበባ በከፍተኛ ባለስልጣኖች ላይ የተፈፀመ አስደንጋጭ ግድያ የእስካሁን ምርመራው በተመለከተ መግለጫ ይሰጣሉ ተብሎ ለሚዲያዎች ጥሪ ከተደረገ በሃላ ተሰርዞ ነበር፡፡ ጠቅላዩ ለምን ይቆይ ብለው እንደነበር አልታወቀም፡፡ ከሰብሰባው በፊት አቃቤ ህጉ ስለ ሰኔ 15 ተራርጦ የሰጠው መግለጫ ላይ ክስተቱ ባጋጠመ በሰዓታት ውስጥ ከተሰጠው መግለጫ ምንም የተለየ ነገር የሌለውና የባህርዳሩን የአዲስ አባበው እንዴት እንደሚገናኝ ማሳየት ያልቻለ ምርመራ ውጤት በሚል ከሁለት ቀን በፊት መግለጫ ሲሰጥ አምሽታል፡፡

 

እንግዲህ እላይ ያየናቸው የተወሰኑ ነጥቦች እያሉ ነው ስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ሊካሄድ ነው እየተባለ ያለው፡፡

 

በአጠቃላይ ያለፈው ክረምት የተካሄደው የስራ አስፈፃሚው ስብሰባ መግለጫ አልነበረውም፡፡ ከወጡት መረጃዎች እንተረዳነው እያንዳንዱ ፓርቲ ከጥልቀት ተሃድሶ አንፃርና ከለውጡ አንፃር በየድርጅቱ ገምግሞ እንዲመጣ መወሰኑን ነው፡፡ የፓርቲ ውህደት በተመለከተም በክረምቱ ስብሰባ በአጀንዳ ቢያዝም ውይይት ስላልተደረገበት ለቀጣይ ስብሰባ ውይይት እንደሚደረግበት ተብሎ ነበር በቀጠሮ የተለያዩት። በነጩ አደራሽ! የተያዘው ቀጠሮ አልፏል። አሁን ድግሞ በድንገት ስብሰባው ተጠርታል። የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ በተያዙት አጀንዳዎች ስብሰባው አድርጎ ግልፅ መግለጫም ሰጥቶ እነደነበር ይታወቃል። ኦዲፓ የስራ አስፈፀሚም ማእከላይ ኮሚቴም ስብሰባ አድርጋል ነገር ግን መግለጫው ግልፅ አልነበረም። ሌሎቹ እንኳን መግለጫ ሊሰጡ ይቅርና መሰብሰባቸውም አልታወቀም።

 

የቅዳሜው ስብሰባ ከላይ በታጀቡት ሁኔታውች ድባብ ውስጥ ሆኖ የሚካሄድ ነው። ምን አጀንዳ ይኖረዋል? መገመት ይቻላል፡፡

 

አንደኛ፡- ወቅታዊ ሁኔታዎችን ይገመግማል። እንደኔ ችግሮችን ነጣጥሎ ይገመግማል አልልም። የተሳሰሩ ሁኔታዎች ናቸውና። ለምን ሰላም አልተረጋገጠም? ከቀውስ መውጣት ለምን ተቸገርን? ብለው ይገመግማሉ። ግን ዋናው ችግር የአመራር ነው ብለው ካለፉና ስብሰባው ከጨረሱ ችግሩ ይቀጥላል። መፍትሄው አንድ አንድ ነው፡፡ ቁልፍ ተጠያቂው ማን ነው? ቀጥሎስ ማን ይጠየቃል? ብለው መወሰንና መወሰን ብቻ ነው ያላቸው ዕድል። ይህንን ይችላሉ? መወሃድ የሚችሉ ከሆነ ተጠያቂም መለየትና እንዲጠየቅ ማድረግ ይችላሉ። መወሃድ የማይችሉ ከሆነ የዚህ ተጠያቂን ተጠያቂ ማድረግ ጥያቄም የመመለስ ብቃት የላቸውም። ይህ ሁኔታ ደግሞ ተጠያቂው ዕድሜ እንዲያገኝ አድርጎ ያልፋል። የኢትዮጵያ ህዝብ ተጠያቂውን ልክ የኦሮሞ ህዝብ እንደጀመረው ትግሉን ተቀላቅሎ ሆ ብሎ ካልጠየቀ ከኢህአዴግ ይሁን ከሌለ ድርጅት ተጠያቂውን ይጠይቃሉ ብየ አልጠብቅም።

 

ሁለተኛው፡- የፓርቲ ውህደት ነው። ይህ አከራካሪ አጀንዳ ነው። ለኢትዮጵያ ህዝብ ምኑም ያልሆነ አጀንዳ ለሊህቃኑ ግን ትልቅ መከራከያ ነው። ይህን አጀንዳ አጀንዳ ማድረግ የተፈለገው ለአሻጥር ነው። ስርዓቱ አደጋ ላይ ሆኖ አጀንዳ ለማስቀየር የተጠነሰሰ ነው፡፡ ተንኮል የተሞላበት ነው፡፡ ከፍተኛ የውስጥና የውጭ አማካሪዎች ጠቅላዩን አማክረው ከኃላ ሁነው ቼ ፈረሴ እያሉ የሚስጋልቡት አጀንዳ ነው። በዚህ አጀንዳ የሚስማሙ አይመስለኝም። በህግም በፕሮሲጀርም ችግር ስላለው አንደ ምርጫው ይደረግ አይደርግ ክርክር መጨረሻው ይደረጋል ብሎ እንዳይደረግ ግን አትዘጋጅ ህውከቱ እንዲቀጥል አድርግ አይነት ዕጣ ፋንታ ሊኖረው ይችላል። አሽናፊ ተሸናፊ የሌለው ክርክር ነው የሚሆነው። ሌላው ሊወሰን የሚችል ነገር ቀድሞ በተወሰነ የውህደት ሂደት አንዋሃድም ያለውን ሃይል በመተው የውህደት ውሳኔ በሙሉ ስምምነት እንደተወሰነ የሚገልፅ መግለጫ ማውጣት፡፡ ይህ ውሳኔ የሚተገበር ሳይሆን ለጊዜው የማሰመሰል ውሳኔ ነው የሚሆነው፡፡

 

ለአብይ ያለፈው ስብሰባ መግለጫ አለመስጠቱ ዋጋ አስከፍሎታል። ሰለዚህ የአሁኑ ስራ አስፈፃሚ ስብሰባ መግለጫ ይኖረው ይሆናል ብዬ እገምታለሁ። መግለጫው ግን ምን ያህል ግልፅነት ይኖረዋል? በሚለው ላይ እጠራጠራለሁ። ውሸት ባደባባይ የጀመሩት ጠቅላዩ በመግለጫም መዋሸት ነውር ነው ብለው የሚተውት አይመስለኝም። ጥፋተኞች ግን እኛ ነን። አሁንም መሃን ከሆነውና ህልውናው ካጣ ድርጅት መፍትሔ የምንጠብቀው። አንዳንድ ሊህቃን ኢህአዴግ አብይን ካላወረደው በአገሪቱ እየሆነ ላለው ተጠያቂው ራሱ ኢህአዴግ ነው እያሉ ነው። ኢህአዴግ በኖረና በተጠየቀ ጥሩ ነበር። የሌለ ድርጅት እንዴት ተብሎ ተጠያቂ ይሆናል ነው የኔ ጥያቄ ደግሞ። ስለዚህ ይህ ስብስባ በኔ ዕይታ ብዙዎቻችን ሁሌ በተሰባሰቡ ቁጥር በተስፋ መፍትሄ የሚያመጡ እየመሰለን ከመጠበቅ ቁርጣችን አውቀን ለትግል እንድንነሳሳ ስለሚያደርግ ጠቃሚ ነው እላለሁ።

 

ቸር እንሰንብት።

 

 


Back to Front Page