Back to Front Page

ለምን ይዋሻል? ለምን ? ክፍል አንድ

 

ለምን ይዋሻል? ለምን ?

 

ክፍል አንድ

 

ክፍላይ ገ/መድህን  6-19-19

ካዛንጅስ ፊንፊኔ

 

በኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ዘንድ አንድ የተንሸዋረረና የተዛባ ሓሰብ አለ፡፡ ስለ ህወሓትና የህወሓትና ኢህአደግ ስራ አስፈፃሚ ሰለሆነው አቶ ጌታቸው አሰፋ፡፡ በኔ አሰተሳሰብ፣ አተያይና ካለኝ የሞያ ቅርበት ምክንያቴን እንደወረደ አቀርባለሁኝ ፡፡

 

ስለ ታጋይ አቶ ጌታቸው አሰፋ በትግል ወቅት በሩቁ የማውቀውን፣ ከ1993 ዓ.ም. በኃላ ደግሞ ቀጥታ አለቃዬ ሆኖ ስለመራኝ ስለሱ ማንነት መናገር አለብኝ ብዬ ያሰብኩት ወራቶች ያስቆጠሩ ቢሆኑም ሌሎች ብዙ አብረውት የሰሩ በቅርብ የሚያቁት ከኔ የተሻለ መግለፅ ይችላሉ በሚል ሃሳቤን ቀደም ብዬ ሳላካፍል መቆዬቴ ይቆጨኛል።በዚህ ግለ ሂሴን ተቀብዬ ዛሬ የማቀውን እንዳለ ለማቅረብ ጥረት አደርጋለሁ።

 

በትግል ወቅት ጌታቸው ብዙ ጊዜ ያሳለፈው በህወሓት የሰራዊቱ አባል በመሆን ነው።እኔ ደግሞ በተለያዩ ክፍሎች ስለነበሩክበሩቁ የማቀውን ልግለፅ።ጌታቸው ከተራ ሰራዊት አባልነት እስከ ኮር አዛዥነት በመሆን መርቷል። አብዛኛው ጊዜ ኮሚሳር በመሆን የሰራዊቱን የፖለቲካ ግንባታ ስራ ይሰራ ነበር።ወደ መጨረሻው አካባቢ ወታደራዊ አዛዥ ሆኖ በስትራተጂካዊ ማጥቃት ወቅት የነበሩ ውግያዎችን መርቷል።

 

Videos From Around The World

በጦርነቱ ዘመናት ሁለቴ ወይም ሶስቴ በውጊያ ቆስሎ በድርጅቱ ሆስፒታል ገብቶ እንደነበር የጌታቸው ኦፕሬተሩ የነበረ ታጋይ የኔ ደግሞ አብሮ አደጌ ጓደኛዬ አጫውቶኛል።ካልተሳሳትኩኝ መጀመርያ በተምቤን ቃቓ በተባለ አካባቢ ደርግ ተራራ ክ/ጦሮች ብሎ ልዩ ስልጠና ሰጥቶ ለመጀመርያ ጊዜ የሄሊኮፕተሮች የተኩስ ድጋፍ እያደርጉለት ባደረገው ወረራ ወቅት በነበረው ውጊያ በቦምብ በብዙ የሰውነት አካሉ ተመቶ ቆስሎ እንደነበረ አውርቶኛል።ሁለተኛውና ሶስተኛው ረስቸዋለሁ ግን በራያ መቻረ እና በወቅቱ ከትግራይ ውጭ በማእኸላይ ኢትዮጵያ በነበሩ ኦፕረሽን ተመቶ ቆስሎ እንደነበረ ነው።አንዴ ተምቤን አካባቢ አቅመራ በነበረው ሆስፒታልአካባቢ ቀኝ እጁ ይሁን ግራ እጁ በጥይት ተሰብሮ ጆሶ ተጠምጥሞበት ለቼክኣፕ መጥቶ እያለ አግኝቸዋለሁ።እኔ በወቅቱ እዛ አካባቢ አቅማራ የነበሩ ስታፍ ሰራተኞች አባል ሁኜ እሰራ ነበር።በነገራችን የሰራዊታችን አመራር ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ በጥይት ያልቆሰለ የለም።እንደ ክትባት ሁሉም ተወግቷል።

 

ጌታቸው ነባር አመራርና በትግሉ ወቅት ጀምሮ ማ/ኮሚቴ ሆኖ በጉባኤ ተመርጧል።ጌታቸው በድርጅቱ የሚታወቀው የመርህ ሰው መሆኑና በፖለቲካ ስብእናውና ዲሲፒሊን ያለው መሪ መሆኑ ነው። ማሌሊት የሚባል ድርጅት በሚመሰርትበት ወቅት የዚህ ድርጅት አባል ለመሆን ሁሉም ከፍተኛ ፍላጎትና ጉጉት ባሳደረበት ወቅት ጌታቸው እንዴት ማሌ ፓርቲ በትግራይ ብቻ መመስረት እንችላለን በኢትዮጵያ ደረጃ አገር አቀፍ ነው መሆን ያለበት የሚል የተለየ ሃሳብ በማራመድ አባል አልሆንም በማለት መከራከሩና በውይይት እስኪያምንበትም አባል ሳይሆን ቆይቷል።መለስም በዚህባህሪው ተደስቶ እንደ ጥሩ ምሳሌ ጉባኤ በሚደረግበት ወቅት ጌታቸው ለማ/ኮሚቴ ሲጠቆም ላመነበት ነገር ያለው ፅናትና ብዙ ሰው ትክክል ብሎታል በሚል የማይሄድ በራሱ ባመነበት ብቻውንም ቢሆን ፀንቶ የሚቆም ታጋይ ነው ብሎ ምስክርነቱን ሰጥቶ ጉባኤተኛው ከዛ ጊዜ ጀምሮ በከፍተኛ ድምፅ ሲመርጠው ቆይቷል።በድርጅቱ አባላት ይህ የጌታቸው ባህሪ እስካሁን ድረስ እንዳልተቀየረ ሁሉም የሚስማማበት ነው።

 

ከበርሃ ትግል በኃላ ወደ አዲስ አበባ ከገባን ጀምሮ ጌታቸው መጀመርያ የመከላከያ ዘመቻ ሃላፊ በመሆን ሲሰራ ቆይቷል። ህገ መንግስቱ ከፀደቀ በኃላ የኢህአዴግ ሠራዊት ከፓርቲ መዋቅር ሲሰናበትና እንደ አገር ጦር ሲደራጅ ጌታቸው ያደገበትና የሚወደውን የውትድርና ህይወት ትቶ ከድርጅት እንዲቀጥል ተወሰነ። እኛ ወደ ምንሰራበት በአቶ ኩማ መደቅሳ ሚኒስተርና በአቶ ክንፈ ገ/መድህን ምክትል ሚኒስተርነት በሚመራ በወቅቱ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በመመደብ ለአጭር ጊዜ ሦስተኛ ሰው በመሆን ሲስራ ቆይቶ ከዛ ቢሮ ተዛውሮ ወደ ፖሊስ ኮሚሽንርነት ተሽሞ ሰርቷል።በፌደራል ፖሊስ ሲስራ እያለ የኢሳያስ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ ወረራ በፈፀመበት ወቅት በአገር ደረጃ ተቃቁሞ በጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ሲመራ በነበረው ማእከላዊ ኮማንድ ፖስት አባል በመሆን ጦርነቱ እስኪገባደድ ድረስ የኮማንድ ፖስቱ አባልና ዘመቻና መረጃ በመሆን ሰርቷል።

 

ጦርነቱ እንዳለቀ በህወሓት ውስጥ ከፍተኛ ልዩነት ተፈጥሮ በነበረበት ወቅት የህወሓት ማ/ኮሚቴ ለወራት ባደረገው ክርክር ጌታቸውም ጥሩ ተሳታፊ እንደነበርና በድምፅ ካሸነፉት ወገን እንደነበረ ይታወቃል።ከዚህ በኃላ በነበሩ መድረኮችም ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የወቅቱ የተሃድሶ መስመሮች እንዲሰርፁ ተንቀሳቅሷል። በዚህ ሁኔታ ሁሉም የሚወደውና የምንሰራበት መስርያቤትአለቃችን ክንፈ ገ/መድሕን በድንገት ተገደለብን።ጌታቸው ከመከላከያ እንደተቀየረና ወደኛ መስርያቤት ከመጣ ጀምሮ ወደ ፖሊስም ከተዛወረ በኃላ ከአቶ ክንፈ ሁሌም ተጣብቀው ነው የምናያቸው።እየተጠራሩ አንዴ እኛ መስርያቤት አንዴ ፌደራል ፖሊስ አንድ ላይ ነበሩ።ከስራ ውጭም አይለያዩም ነበር።የክንፈ ሞት ለያያቸው።ጌታቸው ክንፈን ተክቶ ሲመደብ ሁላችንም ደስ ነው ያለን።ብዙም በጥልቀት ባናቀውም የክንፈ የቅርብ ወዳጅ መሆኑ በራሱ እንድንቀበለው በቂ ምክንያት ነበር።ጌታቸው ክንፈ ቢሮ አልገባም ብሎ ሌላ ቢሮ ገባ።የክንፈ በሞት መለየት ለጌታቸው አንድ ታጋይ ማጣቱ ብቻ አልነበረም።በጣም የቅርብ ወዳጁና ሁሉም ነገር እየተመካከሩ የሚሰሩ ስለነበር በድንገት መለየቱ ጎድቶታል። በርሃ በትግሉ ወቅት ብዙ ጓዶቹን ለቀበረ ጌታቸው መስዋእትነት አዲስ ሆኖበት አይመስለኝም።ግን በጣም አዝኖ ነበር።መለስ እንደተሰዋ የነበረን ጥልቅ ሐዘን ለማፅናናት ራሱ ጌታቸው በስብሰባ የነገረንን አንድ ነገር ልንገራቹህ። ‘’መለስ አንዴ ሞቷል።መለስ የተሰዋው እኛ እንድናዝን ሳይሆን የሱን አርአያነት ተከትለን ለህዝብ እንድናገለግል እስከ መጨረሻ መስዋእትነት ለሀገር እንድንሰራ ነው።’’ ብሎ በመቀጠል ዓይኑ ላይ እምባ እያቅራራ ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለን።‘’ክንፈ እንደተሰዋ ሰሞን መለስ ቢሮ ተጠርቼ ሄድኩኝ። የክንፈን ቢሮ እየመራሁ እንድቆይ ሊነግረኝ ነበር የጠራኝ። መጀመርያ ሁኔታ ምን እንዳለ ጠይቆኝ፣ ስላለው ሁኔታ አብራርቼ ስጨርስ  ስለ ክንፈ ለመናገር ስጀምር ሳላስበው በድንገት እንባየ ፍስስ ብሎ ስቅስቅ ብዬ አለቀስቁኝ። ሁሌም ሀዘኑም ስቃዩንም ደስታውንም በሆዱ የሚያደርገው መለስ ሳለቅስ ምንኛ እንደተጎዳሁ አይቶ ትንሽ ጊዜ ሰጥቶኝ ዝም አለ።ትንሽ እንደቆየ ጌታቸው አትቆዝም።ቀጥ ብለህ ስራህን ስራ ብሎ ተቆጣኝ።አሁንም መለስ መሞቱ ቢያሳዝነንም እንድንቆዝም ግን የሚፈቅድልን አይመስለኝም።ቀጥ ብለን ስራችንን በመስራት መለስን እናስታውሰው’’ አለን እንባው እየተናነቀው።ጌታቸው የመስራቤታችን ባልደረቦችና አመራሮች የነበሩ አቶ ወልደማርያም ዋቆ በድንገት በበሽታ ሲሞቱ በኃላም አቶ ታሪኩ በመኪና አደጋ ሲሞቱ ሐዘኑ ጥልቅ እንደነበረ ሁሉም የመስራቤቱ ሰራተኛ የሚያቀው ነው።አሁን አንዳንዶቹ ሊሱሉት እንደሚፈልጉት ጨካኝ አረምኔ አራዊት ሳይሆን ጌታቸው ርሁርህ ሰው ነው።

 

አቶ ጌታቸው የድሮ ቢሮክራሲ የሚያቁ ሠራተኞች ካልሆኑ በስተቀር አቶ የሚለው ሠራተኛ የለም።እነሱም አቶ ይበሉት እንጂ አንቱ የሚለው የለም።ከፅዳት ሠራተኞች ጀምሮ እስከ አብረውት የሚሰሩ አንተና ጌታቸው ብለው በስሙ ነው የሚጠሩት።ከዋና መምርያዎች ደብዳቤ በፖስታ ለጌታቸው ሲመጣ ለክቡር ምናምን የሚል ነገር የለውም።ከሌሎች ሚኒስትሪ መስርያቤት ወደ መስርያቤታችን ፖስታ ወይም ደብዳቤ ሲመጣ ለክቡር ተብሎ ሲፃፍ ጌታቸው ደስ አይለውም።ይስቃል።ባለስጣንነት የማይወድ ባለስልጣን የምስለኛል ጌታቸው አሰፋ ለኔ።

 

ጌታቸው ህይወቱ ስራ ነው።ስራ ስራ ትግል ትግል ነው ህይወቱ።ሲዝናና ሲስቅ ብዙ ጊዜ አይታይም።ሁኔታ በተፈጠረ ጊዜ ሁሌም ጌታቸው በአካል ቦታው ላይ ይገኛል።የበታቾቹ በሪፖርት የሚያቁትን እሱ በአካል ሄዶ ሁኔታ በተፈጠረበት ስፍራ በአይኑ አይቶ ከዛ ቢሮ ሄዶ ተውያይቶ መመርያ አቅጣጫ ሰጥቶ ስራ እንዲሰራ ያደርጋል።የሙባረክ ግድያ ሙከራ፣የግዮን ሆቴል የፈንጂ ፍንዳታ፣የዋቢሸበሌ ፈንጂ ፍንዳታ፣የትግራይ ሆቴል ፈንጂ ፍንዳታ፣የዶ/ር አብዱልመጂድ ግድያ ሙከራ፣ብሉቶፕስ የቦምብ ጥቃት፣የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድሬዳዋ፣ሱዳን፣ኮሞሮስ በተጠለፈባቸው ጊዝያት በሁሉም ...ወዘተጌታቸው በአካል ተገኝቶ ስራውን ሰርቷል። ከዛም ትምህርትም ወስዶ ቀጣይ ችግር እንዳያጋጥም መመርያዎች በማውጣትና ማስተማርያ አድርጎ ይጠቀምበታል።ለዚህም ነው በኃላ በኃላ ሽብርተኞች ምንም ውጤታማ  እንዳይሆኑ የሚያደርግ ስራ መስራት የተቻለው።ኬንያ በተደጋጋሚ የሽብር ሰለባ በምትሆንበት ስዓት ሀገራችን ሰላም ያገኘቸበት ሁኔታ መፈጠር ላይ ጌታቸው ሚናው ትልቅ ነበር።ሁሉም ነገር በፕላንና በፕላን ብቻ በበቂ ዝግጅት ብቻ መሰራት አለበት የሚለው ጌታቸው ሁሉንም የመስራቤቱን አባላት በተዋረድ አሳታፊ በሆነ መንገድ ስራውን ያከናውናል።ጌታቸው ስራ አፈፃፀም ላይ የሚቀልድ፣አላስፈላጊ ጊዜ የሚወስድ፣ስንፍና የሚያሳይ ሰራተኛ ሲያገኝ ትዕግስት የለውም።በጣም ይቆጣል።ለማያቀው በጣም ያስደነግጣል።ይህችን ደካማ ጎኑን ነው ተጠቅመው ከሰማይ ተነስቶ የሚቆጣና እንደሚፈራ አድርገው የሚስሉት።ጌታቸው ስራ አልተሰራም።ውጤት አልተገኘም ብሎ ይቆጣል።ይቆጣል ብቻ አይገልፀውም።በጣም ይናደዳል።ራሱን እስከሚጎዳ።ይህም ሆኖ ቂም የሚባል ነገር የለውም።ወዲያው ትንሽ ቆይቶ ከተረጋጋ በኃላ ቀስብሎ ጥፋት ሰርቷል የሚለውን ሰው ይመክረዋል።ይገስፀዋል።የሚገርመው ነገር መቆታቱንም ስህተት መሆኑ ይቅርታ ይጠይቃል።ብታጠፋም መቆጣት መናደድ አልነበረብኝም ብሎ የራሱንም ስህተት ያምናል። በመስራቤቱ አመራር መካከል ግምገማ ሲደረግም ግለሂስ ያደርጋል።ሌላ ጌታቸው የማይወደው ነገር ውሸትና ማጭበርበር፣በስልጣኑ የሚመካ ብቻ ሳይሆን ባለስልጣን መሆኑ ለማሳወቅ ድራማ የሚስራ፣ስልጣን ሲጨምር አነጋገሩ የሚቀየር፣አለባበሱ አካሄዱ አረማመዱ የሚቀይር፣ የመኪና በር ክፈቱልኝ፣ኃላ ወንበር ልቀመጥ የሚል መሪን ነው።አምርሮ ይጠላቸዋል።ጌታቸው ከዚህ የፀዳ ሆኖ በተግባርም አረአያ በመሆንም በስልጠና ወቅትም ስእላዊ በሆነ መንገድ እየገለፀ ያስተምረንም ነበር። 

 

ጌታቸው የመስርያቤቱን የሰው ሃይል መቀየር ላይ ራሱም የሚሳተፍበት የስልጠናና ትምህርት ሰፊ እንቅስቃሴ አድርጋል። መስርያቤቱ በደርግ ጊዜ ሰፊ መሬት ያለው ማሰልጠኛ አለው።ይህን ማሰልጠኛ ዘበናዊ የማስተማር ዘዴዎችን እንደግባእትነት የሚጠቀም ለማድረግ በቴክኖሎጂ የተሟላና ዘበናዊ የሌክቸር አደራሽና ስንዲኬት ክፍሎች ያሉት እንዲሆን፣ተማሪዎችና ሰልጣኞች በትምህርት ወቅት የተመቻቸ ኑሮ እንዲኖራቸው ዘበናዊ ካፊተርያ በመገንባት በሰው ችሎታና ብቃት መለወጥ ላይ ትኩረት መስጠቱን አስረጂ ነው።በዚህም እንቅስቃሴ በቀጥታ ራሱም እየተሳተፈበት ሁሉም የመስርያቤቱ ሰራተኛ የኮራበት ስራ ተሰርቷል።ካሪኩለም እንደየሁኔታው በየጊዜው እየተሻሻለ በተማላ መንገድ እንዲዘጋጅ አድርጋል።ቀጥተኛ ተሳትፎም በዝግጅቱ ወቅት እንደነበረው በመስራቤቱ ግምገማ ወቅት ማሰልጠኛ ማእከሉ ሲገመገም የተረጋገጠ ነው።ይህን ማሰልጠኛ ጌታቸው በሚወድውና በሚያከብረው ወዳጁና ይህን መስርያቤት ለመቀየር ጥናት እያደረገ  በድንገት በሞት በተለየው የመስርያ ቤቱ ዋና ዳይሪክተር በነበረው አቶ ክንፈ ገብረመድህን እንዲሰየም የመስራቤቱ የበላይ ማነጅመንት ቀርቦ ፀድቃል።የማሰልጠኛው ኮለጅ ሞቶም ‘’elite without elitism’’የህዝብ አገልጋይ የሆነ የተማረ የሰው ሃይል መፍጠር ነበር።የኮለጁ መፈክር። በዚህ ትምህርት ቤት ጌታቸው አሰፋጥሩ አሰልጣኝም አስተማሪም እንደሆነ አስመስክሯል።

 

መስርያቤቱ ስም ብሔራዊ ድህንነትና መረጃ አገልግሎት (National Intelligence and Security Service) (NISS)የሚል በአገራችን ቢሮክራሲ አገልሎት የሚል ስም ከሚኒስትር ከዋና መምርያ ባለስልጣን ከሚለው ስም በታች ስለሆነ፣ የመስርያቤቱ ደረጃ ዝቅ ተደርጎ እንዲታይ ስላደረገው ሁሉም የመስርያቤቱ አመራሮች በስሙ ላይ ጥያቄና ተቃውሞ አሰሙ።በወቅቱ ጌታቸው የሰጠን መልስ አገልግሎት ስራን ዝቅ የሚያደርጉት ይታረሙ እንጂ እኛ ህዝባችንና መንግስታችንን ከማገልገል ውጭ ምን ስራ አለን? ደግሞም አሁን ዘበናዊ አመራር ስለ አገልግሎት ለደምበኞችና ለዜጎች እያስተማረ ባለበት ሁኔታ የሚያስከብር እንጂ የሚያሳፍር የለውምና የምናርመው ስሙን ሳይሆን አመለካከቱን ነው ብሎ ገለፀልን።

 

 

 


Back to Front Page