Back to Front Page

አማራን መግደል ለምን አስፈለገ?!

አማራን መግደል ለምን አስፈለገ?!

በሰንደቁ ያይላል

11/2/2019

 

አማራ የለም የሚለው የጣእረ ሞት ጭሆት ለመጀመርያ ግዜ የተሰማው በሌ/ኮ መንግስቱ ሃ/ማርያም የመጨረሻ የስልጣን ዘመን ይመስለኛል። ከተሳሳትኩኝ አርሙኝ። ቆፍጣናው መንጌ በሜዳሎችና በመአርግ በተሽቆጠቆጠ የሚሊቴሪ ልብስ አምረውና ደምቀው በቴሊቪዥን መስኮት ብቅ አሉ። የመንግስት መስርያ ቤቶች ተዘግተዋል። የፊደል ካስትሮን የመድረክ ንግግር ሪኮርድ ለመስበር በሚመስል ሁኔታ ረዥም ዲስኩር በመሳጭና ቀስቃሽ ሙዚቃዎች ታጅቦ ለኢትዮጽያ ህዝብ አቀረቡ።

በዚሁ ከመፈርጠጣቸው በፊት እንደ መሰናበቻም ጭምር ከተጠቀሙበት መደረክ ላይ ብዙ ጥያቄዎችን ጠይቀው ብዙውን ራሳቸው መልሰው በህዝቡ ዘንድ ደግሞ ብዙ አዳዲስ ጥያቄዎችን አስነስተው አጠናቅቀውታል። ራሳቸው ጠያቂ ራሳቸው መላሽ በሆኑበት በዚህ ንግግር ከጠየቁት ጥያቄ ውስጥ አንዱ ፣ ለመሆኑ አማራ ማን ነው? የሚለው ነው።

ለመሆኑ አማራ ማን ነው?!

ሲያሻቸው የጦር መሪ ሲያሻቸው የታሪክ ተማራማሪ የሚሆኑት አምባገነኑ መሪ መንግስቱ ሃ/ማርያም በእርግጥ አማራ የለም አላሉም። ይሁንና አማራ ማለት በተራራ ላይ የሚኖር ህዝብ ማለት ነው። አማ እና ሓራ ከሚሉ የሆነ ሀገር ቋንቋ ተቀይጦ ተራራ እና ህዝብ የሚለውን ፍቺ በመውሰድ በተራራ ላይ የሚኖር ህዝብ ማለት ነው አሉን። እዚህ ጋር አማራ አለ። ህልውናው አልተካደም። ይሁንና የደጋ ሰው ፣ በከፍተኛና ተራራማ አከባቢዎች የሚኖር ህዝብ የሚል ትርጓሜ ተስጥቶታል። በመንግስቱ ሃ/ማርያም የታሪክ ትንታኔ መሰረት ፥ ከሂማላያ ከፍተኛ ተራሮች እስከ አልፕስ ሸንተረሮች የሚኖር የሰው ፍጡር ሁሉ አማራ ተብሎ ይጠራል ማለት ነው። አማራ የጂኦግራፊ ስም ከሆነ ፣ ኦሮሞስ ምን ሊባል ነው? ፣ ሶማሌውስ ምን ሊባል ነው?። ይህ የህፃን ልጅ ተረትተረት የሚመስለው የታሪክ ትንታኔ ፣ ብዙ ሰው ላይላዩን ስያየው አማራን የማጥፋትና የመካድ ተግባር አድርጎ ሊወስደው ይችል ይሆናል። ሀቁ ግን እሱ አይደለም።

ከመንግስቱ ሃ/ማርያም ቀጥሎ የአማራን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ካስገቡት ታዋቂ ሰዎች መካከል የጂኦግራፊ መምህሩ መስፍን ወልደማርያም ናቸው።

እኝህ ሰው ደግሞ ይሉናል ፥ አማራ ማለት ክርስትያን ማለት ነው። አማራ የሚባል አንድወጥ የሆነ ማህበረሰብና አንድ ማህበረሰባዊ እሴትና ወግ ያለው ህዝብ የለም ፤ ክርስትያን ማለት ነው ይሉናል። ስለዚህ አማራነት ከሀይማኖትና እምነት የተያያዘ እንጂ ከብሄር ማንነት ጋር የተያያዘ አይደለም የሚል አግላይና ከፋፋይ ትርጓሜ ይሰጣሉ። አማራ እስልምና ሀይማኖት ከተስፋፋባቸው ቀደምት የኢትዮጽያ ብሄሮች አንዱ ነው። አሁንም ቢሆን ራሳቸውን በአማራነት የሚገልፁ ቁጥራቸው የማይናቅ ሙስሊሞች በመላው ኢትዮጽያ ይገኛሉ። አማራ ክርስትያን እሴቶች እንዳሉት የታወቀ ነው። ይሁንና አፋሩም እስላማዊ እሴቶች እንዳሉት የታወቀ ነው። ታድያ አፋር የሚባል ብሄር የለም፣ አፋር ማለት እስላም ነው ለማለት ካልተቻለ ፥ ብምን ሎጂክና ሰነ አመክንዮ ነው አማራ የሚባል ብሄር የለም ፣ አማራ ማለት ክርስትያን ማለት ነው ለማለት የሚቻለው። አሁንም ጥያቄው አማራ የለም ለማለት ለምን አስፈለገ ነው?።

ከሰሞኑ ደግሞ በአማራ ህዝብ ስም ሲሸቅላና ሲሽቅጥ የኖረና በቀን ሁለቴ ሶስቴ የአማራ ህዝብ ስም ሳይጠራ ውሎ የማያውቀው አንዳርጋቸው ፅጌ አፉን ሞልቶ አማራ የሚባል የለም ይለናል። የዚህ ሰውየ ምክንያቶች ደግሞ የዋህነት ያጠቃቸው ናቸው።

ይህ ሰው አማራ የለም ለማለት ከ1000ና 1500 አመታት ወደኋላ ሄዶ ያኔ አማራ አልነበረም ይለናል። ከዛ በኋላ ነው በወቅቱ በወታደርነት ተሰማርተው በነበሩ ሰዎች ስብስብ አማራ የተፈጠረው ይለናል። የተጠቀሰው አመት ርዝመት አንድን ማንነት ለመቅረፅ እጅግ በጣም ረዥም ግዜ ነው። በእርግጥም ይህ አፈታሪክ እውነት ከሆነ አማራ የለም ሳይሆን መባል ያለበት ፥ አማራ ይህን ያክል ዘመን የተለያዩ ተፅእኖዎችን ተቋቁሞ እስከዚህኛው ዘመን መዝለቁ አድናቆት ሊቸረው ነው የሚገባ። ሌሎች በተመሳሳይ ዘመን የተፈጠሩ ማንነቶች ከስመዋልና። ከ1500 አመት በፊት አልነበርክም ፣ ስለዚህ አማራ የሚባል ማንነት የለህም የሚል አባባል ብዙም አያስኬድም።

በአጠቃላይ፥ አማራ የለም ብለህ ስታበቃ ፣ ኦሮሞ ግን አለ ፣ ትግራዋይ ግን አለ፣ ሃድያ ፣ ከምባታ . . . አለ ለማለት የሚያስችል ስነ-አመክንዮ ምን ያክል ጠማማና ያልተገራ ምክንያት ቢሆን ነው?! እስከ አሁን ኢትዮጽያ ውስጥ አዲስ እውቅና የሚሰጠው ማንነትና ብሄር እንጂ ፣ የለህም የተባለ ማንነትም ሆነ ሌላ ብሄር የለም። በንጉሶች ግዜም ቢሆን ፣ በወታደራዊ መንግስት ግዜም ፣ በኢህአዴግ ግዜም የለህም እየተባለ ያለው አማራ ብቻ ነው። ለምን? ማንስ ነው አማራ የለም እያለ ያለው?።

ነገሩ ወዲህ ነው. . .

በአማራ ህዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለው የተቀናጀ የማንነት ግድያ አማራ ጠል በሚል ፍርጃ በተቀቡ ሀይሎች ሳይሆን እየተፈፀመ ያለው ፣ በአማራ ስም ምለው በሚገዝቱ አማራዎች ነው። እየፈፀሙት ስላለው የማንነት ግድያ እየደረሰባቸው ያለ አንዳች አይነት ውግዘት አለመኖሩ ደግሞ ግርታን መፍጠሩ አይቀርም። ይህንን ተግባር ሌላ ሰው ቢፅፈውና ቢናገረው ምን ያክል ውግዘትና እርግማን ሊደርስበት እንደሚችል ለመገመት ፥ ጃዋር መሃመድ ይህን ቢል ግብረመልሱ ምን ሊሆን እንደሚችል ብቻ መገመት ነው። አማራ ነን የሚሉ ወገኖችስ አማራ የሚባል ህዝብ የለም የሚሉትን ወገኖቻቸውን ማውገዝ እንኳ ባይችሉ ፣ ለምን በግልፅ መድረክ ወጥተው አለን አይሉም? አላማው ግን ምንድ ነው? ለምንስ እነዚህ ሰዎች ውግዘት አልደረሰባቸውም?

አላማው አንድና አንድ ነው። አማራን ገድሎ የማዳንና ዘላለማዊ የማድረግ ሙከራ ነው። አማራ ማንነትን በመግደል ፥ የኢትዮጽያዊነት ቅብ ማንነት ማንግስ የሚል ተመኩሮ የከሸፈ ፕሮጀክት ለማስቀጠል የተወጠነ ሴራ ነው። ኢትዮጽያዊነት የሚለው ማንነት በዋናነት አማራን ተጠቃሚ ማድረግ የሚችል ድንቅ ፈጠራ አድርጎ ከመቁጠር የሚመነጭ የተሳሳተ የስስታሞች ምኞት የተነሳ ነው የአማራን ብሄርተኝነት ለማላሸቅ እየተሞከረ ያለው። እነዚህ ሀይሎች በአማራ ህዝብ ላይ ይህን መሰል ቁማር ሲጫወቱ ሀይባይ መጥፋቱ ደግሞ በአማራ ኤሊቶች ዘንድ በፕሮጀክቱ ዙርያ ስምምነት ለመኖሩ ማሳያ ነው።

ከዝምታው በላይ ደግሞ ፣ በአማራ ኤሊቶች ዘንድ አማራን ገድሎ የማስነሳት ያልተፃፈ ወይም ድብቅ ስምምነትና መግባባት ለመኖሩ ተግባራዊ ማሳያዎችን ማስቀመጥ ይቻላል። ለምሳሌ ፥ ስለ ኢትዮጽያዊነት ነጋ ጠባ የሚሰብኩን ሰዎች ፣ ኦሮሞው ፣ ቅማንቱ ፣ ሲዳማው ፣ ትግሬው፣ አፋሩ ፣ ሶማሌው ፣ ጌድኦው . . . ወዘተ ሲጨፈጨፍና ሲፈናቀል ልሳናቸው ተዘግቶና ብእራቸው ደርቆ ፤ ራሳቸው በፈጠሩት ቀውስ የኛ የሚሉት ወገን ተጎዳ በሚል ተግተልትለው በመውጣት ስለ ህግ መከበርና ሰብአዊ መብት ይደሰኩርልናል። ላንቃቸው እስኪቀደድ ስለ ኢትዮጽያዊነት የሰው ጀሮ እስኪደነቁር ድረስ ሲዘምሩ ከርመውና ፣ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የደረሰውን የከፋ በደልና ግፍ ሲደርስ ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው ቆይተው ሲያበቁ (ሲላቸውም ኢትዮጽያዊነትን ለማንገስ መከፈል ያለበት ተገቢ ዋጋ እንደሆነ አድርገው ሲያቀርቡት ቆይተው) ፣ የለም የሚሉት ወገን ተጎዳ ብለው ያዙኝ ልቀቁኝ ማለታቸው ፍርደ ገምድልነታቸው የሚያሳብቅ ከመሆኑም በላይ ፥ መልእክቱ ግልፅ ነው። መልእክቱ ኢትዮጽያዊነት አማራነት ፣ አማራነት ኢትዮጽያዊነት ነው የሚል ነው። አማራ እስካልተጎዳ ድረስ ኢትዮጽያም ደህና እኛም ጤና ነው ነገሩ።

ከሰሞኑ በኦሮምያ ክልል የተፈጠረውን ግርግርና ሁከት ተከትሎ የኢትዮጽያዊነት ተሟጓቾ ፖለቲኬኞች እየሰጡት ያለው መግለጫ ለትዝብት የሚዳርግ ነው። ለነገሩ ፥ ማፈርያቸውን ሸጠው የበሉ ሰዎች ቢሆኑ እንጂ ሁሉም ከጥቂት ወራቶች በፊት ሲዘረግፉት የነበረውን ውዳሴና አድናቆት በተናገሩበት ምላሳቸው ፤ ተመልሰው ምሬትና እሪታ ስያሰሙበት እሬት እሬት ሊላቸው ይገባ ነበር። ይሉኝታ ቢስነታቸው የሚያሳየው ደግሞ ፣ ወደፊት መጥተው በተለያዩ መንገዶች እኡታቸውን እያሰሙ ያሉት ሰዎች ብዙዎቹ ገለልተኝነትና ኢወገናዊነት በሚጠይቁ የተለያዩ የፌዴራል ተቋማት ውስጥ ስልጣን ተቆናጥጠው የሚገኙ መሆናቸው ነው።

እነዚህ ሰዎች አማራ የሚባል ህዝብ የለም ሲባል ቃል ሳይተንፍሱ ቆይተው ፣ አማራ የሚባል ወገናችን ተጎዳ ብለው አደባባይ መውጣታቸው የሚያመላክተው ነገር ቢኖር አማራን ገድሎ የማዳን ፕሮጀክት ላይ ተሳታፊ መሆናቸውን ነው። የአማራ ጠበቃ ለመሆን መጀመርያ የአማራን ህልውና መቀበልና ማራጋገጥ ያስፈልጋል። አማራው በአሁኑ ወቅት በላስቬጋስ የካዚኖ ቁማር ተረክዘዋል። አሁንም እንደቀደሙ የኢትዮጽያ ፖለቲካ ነጋዴዎች ፣ የቅዠት ኢትዮጽያዊ ማንነትን በዚህ ህዝብ ስምና ኪሳራ ለመገንባት እየተሯራጡ ይገኛሉ።

አማራው አተርፍ ባይ አጉዳይ እንዳይሆን እነዚህን ሀይሎች በግልፅ ወጥቶ ቢታገላቸው ይበጃል። የቆጡን አወርድ ብላ የብብትዋን ጣላች እንደሚባለው ፣ በጠቅላይና ተስፋፊ ምኞት ተገፋፍቶ ከሁለት ድስት እያጣቀሱ ለመብላት መሞከር የማይሽር የቃር ምንጭ እንዳይሆን ቢታሰብበት ጥሩ ነው። ሁለት እግር አለኝ ተብሎ ሁለት ዛፍ ላይ አይወጣምና።

Videos From Around The World

አማራው ፥ አማራዊ ማንነቱን ማስጠበቅና ማስቀጠል ፍላጎት ካለው እነዚህን ሀይሎች ያለማቅማማት በግልፅ ወጥቶ መታጋል ግዴታው ነው። አማራን አጥፍቶ ኢትዮጽያዊነትን መገንባት ይበልጥኑን አማራን ተጠቃሚ ያደርጋል የሚለው መከራከርያ ቅዠት ነው። ለአማራ ጠብ የሚልለት ነገር የለም። ከዚህ በፊት በነበሩት ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች አማራ እንዲቆረቁዝና እንዲደሀይ ከማድረግ ውጭ የፈየዱለት ነገር የለም። አሁንም አማራነትን ቀብሮ በኢትዮጽያዊነት ስም እናስነሳዋለን የሚለውን ቁማርን በአሸብራቂና አስጎምጂ ተስፋዎች ተደልሎ ባላየ ከማለፍ ዝምታውን በመስበር ለእርድ ከመቅረብ ራሱን መታደግ አለበት።

በአብን ስም ተደራጅቶ የነበረው የአማራ ሀይል የተመታበት ዋናው ምክንያት ለዚህ ፕሮጀክት እንቅፋት ነው ከሚል እሳቤ ነው። የአብን አስተሳሰብና እምነቶች የፈለገው ያህል የተንሸዋረሩና ጠማማ ቢሆኑ ፣ በሀሳብ ገበያ እየተገሩና እየተቃኑ የሚሄዱ ከመሆናቸውም በላይ በዴሞክራስያዊ መድርክ ለውድድር ቀርበው ጥራታቸውና ጥንካሬያቸው የሚፈተንና የሚፈተሽ ነው መሆን ያለበት። እንደ ድርጅት አብንና መሰሎቹን የአማራ ብሄራዊ ድርጅቶችን በተለያዩ ዘዴዎች ለማክሰም የሚደረገው ሙከራ ግን አማራን ገድሎ የማዳን የቅዠት ፕሮጀክት የመጀመርያው ምእራፍ መሆኑን መታወቅ አለበት። አብኖች ይህን አካሄድ በፈቃደኝነትም ይሁን ተገደው ወደዚህ ሂደት ለመቀላቀል ዳርዳር ማለታቸውን ሊያስቡበት ይገባል። አደገኛ ቁማር ነው።

ይህ የዶሮና የቢላ ጨወታ እጅግ በተወሰኑ አጋጣሚዎች ካልሆነ በስተቀር ሁሌም ቢላው ዶሮውን በመብላት እንደሚጠናቀቅ ለማንም የተስተካከለ አስተሳሰብ ላለው ሰው ግልፅ ነው። በተአምር በሚባል አጋጣሚዎች ካልሆነ በስተቀር ዶሮው ቢላውን ሊበላ አይችልም። አማራን ገድሎ የማዳን ጨዋታ የዶሮና የቢላው ጨዋታ አይነት ነው። እድሉ ተመሳሳይ ነው። ሞቶ የመዳን ጨዋታ አማራዎች እንሞክረው ካሉ ሜዳውም ይሀው ፈረሱም ይሄው።

እንደ እኔ ግን ፥ አማራ አለ!። ለወደፊቱም ይኖራል!። በዴሞክራስያዊትና ህብረ ብሄራዊት ኢትዮጽያም እየተሸረበበት ያለውን የአዛኝ መሳይ ቅቤ አንጓቾች የተቀነባበረ ሴራ በጣጥሶ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር አብሮ ይኖራል።

ህብረ ብሄራዊነት ይለምልም!

መልካም ሳምንት።

 

Back to Front Page