ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ሉዓላዊነት መከበርና ለህዝበቿ ዴሞክራሲያዊና ፍትሓዊ አንድነት ይበልጥ መጠናከር ቃል ኪዳናችንን እናድሳለን፡፡

 

ከትግራይ ተወላጆች ማህበር በሰሜን አሜሪካ

ዋሽንግተን ዲሲ

 

እኛ በሰሜኑ የዓለም ዋልታ የምንገኝ በሰሜን አሜሪካ የትግራይ ተወላጆች ማህበር አባላት በአሁኑ ወቅት በምስራቁና በሰሜኑ የአገራችን ድንበር በለየላቸው ጠላቶቻችን አማካኝነት የተደቀነብንን እጅግ አሳሳቢ አደጋን አስመልክቶ የኢትዮጵያ የተወካዮች ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ በስፋትና በጥልቀት መክሮና ዘክሮ ያሳለፈውን ውሳኔ የተከታተልነው በፅሞናና በፅኑ ሃገራዊ ወኔ ነው፡፡በመሆኑም ይኸንን ወቅታዊና ሃገራዊ ጉዳይ አስመልክቶ የሚቀጥለውን የአቋም መግለጫ አውጥተናል፡፡

 

  1. ፓርላማው በአክራሪው የሶማሊያ እስላማዊ ሸንጎ ፅንፈኛ አመራር ፊታውራሪነት፣በኤርትራው የሻዕቢያ እብሪተኛ መንግስት ያዥ ገራዥነት፣በታሪካዊ ጠላቶቻችን አይዞህ ባይነትና በውስጥ ምንደኛ ሰርጎ ገቦች ጉዳይ ፈፃሚነት በአገራችን ሉዓላዊነት፣ ብሄራዊ ደህንነትና ክብር እንዲሁም በህዝቦቿ ነፃነት ላይ በማነጣጠር ያንዣበበብን ወረራ የሰላም አማራጭን አሟጦ እስከ መጠቀምን ጨምሮ አስፈላጊው ህጋዊና ተመጣጣኝ የመከላከል እርምጃ ይወሰድ ዘንድ ያስተላለፈውን ውሳኔ ትክክለኛነትንና ወቅታዊነትን በአርምሞ እያደነቅን ለተግባራዊነቱ ከኢትዮጵያ ህዝቦች፣መንግስትና ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን ጎን በፅናት መቆማችንን እናረጋግጣለን፣

 

   2. የኢትዮጵያ ህዝቦች በመከባበርና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ፍትሃዊና

      ዴሞክራሲያዊ ኣንድነት እየጎለበተ መሄድ የእግር እሳት ሆኖ እንቅልፍ

      የነሳቸው የሩቅና የቅርብ ጠላቶቻችን በዓለም አቀፍ የሽብርተኝነት ኣውሎ

      ነፋስ እየተነዱ የሚረጩብንን በጎሳ፣በቋንቋና በሃይማኖት ካባ የታጀለውን

      የጥላቻ መርዝ ለማጨናገፍ የሚደረገውን ፊልሚያ ለማገዝ ትግላችንን

      ከምልኣተ ህዝቡ ትግል ጋር ለማነባበር ቆርጠን መነሳታችንን

      በአፅንኦት እንገልፃለን፣

 

  1. የመራጩን ህዝብ ይሁንታ አግኝተው የተጣለባቸውን የሃገርና የወገን ደህንነት አደራን በእጅጉ የሚፈትሽ ጉዳይ በተነሳበት በአሁኑ ፈታኝ የታሪክ ወቅት፣ ከህዝቡ ጎን ቆመውና እጅ ለእጅ ተያይዘው የውጭ ጠላትንና ጋሻ ጃግሬዎቻቸው የሆኑትን የናት ጡት ነካሽ የውስጥ ከሃዲዎችን ፊት ለፊት ከመመከት ይልቅ በመለሳለስ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች የወሰዱትን ፓርላማው ያሳለፈውን ውሳኔ የሚቃረን አቋም የሰማነው በትዝብትና በግራሞት ሲሆን ኣሁንም እነኝህ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አቋማቸውን ዳግም በመመርመር ሰለፋቸውን እንዲያሳምሩ በህዝቡ የሰጣቸውን ታሪካዊ ዕድል እንዲጠቀሙበት አበክረን እንጠይቃለን፣

 

  1. በውጭ ሃገር ነዋሪ የሆኑት ራሳቸውን በተቃዋሚነት ፈርጀው የተኮፈሱት ጥቂት ሟርተኞችና የስልጣን ሱሰኞች በአሁኑ ወቅት በአገራችን ላይ ላጠላው የጦርነት ዳመና የክህደት አሳሳች ትርጉም ሆን ብለው በመስጠት እነሱ ለሚንደላቀቁበት የስደት ኑሮ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ታጋችና ገባሪ ሆኖ ይጋልቡት ዘንድ እንዲመቻቸው የሃገር ፍቅር ወኔውን በመስለብና የጥላቻና የቁርሾ ፕሮፖጋንዳ ባለማባራትና ባለመታከት በመመገብ በሃገሩ ጉዳይ ላይ ትክክለኛ ግንዛቤና አቋም እንዳይዝ የሚፈጥሩበትን ጋሬጣ እንዲመክት ከብዙሃኑ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ጎን ቆመን ትግላችንን በማስተባበር በቁርጠኝነትና በአለኝታኝነት እንሰለፋለን፣

 

  1. የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ጎረቤት የሆኑት የኤርትራና የሶማሊያ ህዝቦች የወል ጠላቶቻቸው በሆኑት ኋላቀርነት፣ድህነት፣ድንቁርናና በሽታ ላይ የጋራና የህብረት ክንዳቸውን በማንሳት ፊታቸውን ወደ ዘለቄታዊ ሰላም፣ መረጋጋት፣ ልማትና ዴሞክራሲ እንዲያዞሩ መንግስት የዘረጋውን የዘወትር የውጭ ፖሊሲና መተክላዊ አቋም በፅናት እንዲገፋበት እያሳሰብን እኛም በዚህ ረገድ የድርሻችንን ለመወጣት ዝግጁነታችንን በአንክሮ እናድሳለን፣

 

  1. ሃገር ተረካቢ የሆነው አዲሱና ወጣቱ የኢትዮጵያ ትውልድ ዛሬ በኤርትራና በሶማሊያ ግንባሮች የተቃጣብንን ወረራ እጅግ በሚያቃጥልና በሚያንገበግብ የሃገር ፍቅር ወኔ በመነሳሳት የአበውን የታሪክ ቅርስና ውርስ የሆነውን ለሃገር ቀናኢነት፣ለነፃነት ተጋዳይነትና የአርበኝነት ገድል ደግሞ ደጋግሞ ለማደስ የሚያሳየውን እልህ፣ፅናት፣ቆራጥነትና ቁርጠኝነት በእጅጉ የምንመካበትና የምንኮራበት እሴት መሆኑን በአድናቆት እንገልፃለን፡፡

 

 

 

 

 

                              የትግራይ ተወላጆች ማህበር በሰሜን አሜሪካ

                              ዋሽንግተን ዲሲ

                              ዲሴምበር 12/2006